ETHIO12.COM

ዕርዳታ – ኢትዮጵያ ጊዜ እየተጠበቀ የምትደቆስበት የስንዴ ፖለቲካ

የስንዴ ወይም የችጋር ጣጣ ብዙ ነው። መራብ ብቻ ሳይሆን ከዛም በላይ መከራ አለው። ኢትዮጵያ በችጋርና “ችጋርን እንታደግ” በሚሉ አገራት ደባ በተደጋጋሚ ተደቁሳለች። ስንዴ በጆንያ ለኢትዮጵያ እርዳታ ብቻ ሳይሆን መከራዋም ጭምር ነው። ይህ እየታወቀ አንዳቸውም መንግስታት በኢትዮጵያ በምግብ ምርት ራስን ለመቻል ሌት ተቀን ህዝብ አነሳስተው አልሰሩም። ሙከራዉ ግን ነበር።


ከኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር የተሰጠ መግለጫ
ሰኔ 03/2015 ዓ.ም
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ቁልፍ እሴት ከሆኑት ቀዳሚውና ዋናው ከራስ በፊት ለህዝብና ለሃገር ጥቅም መቆም ነው፡፡
ዩኤስኤአይዲ (USAID) ሰሞኑን አጣርቻለሁ ብሎ ባወጣው መግለጫ ለሰብአዊ እርዳታ የመጣን እህል ከሌሎች መንግስታዊ አካላት ጋር በመሆን መከላከያ ሰራዊታችንም እንደተጠቀመ አድርጎ ያቀረበውን ሪፖርት የተለያዩ ሚዲያዎች ሲዘግቡት አስተውለናል፡፡
የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በጥብቅ ድስፕሊን የሚመራ ዘመናዊ ሰራዊት ነው፡፡ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚደረግላቸውን ወገኖቹን ቀለብ ሊቀማ ቀርቶ፤ ከቀለቡ ቀንሶ የሚያካፍል ሰራዊት መሆኑን የሃገሩ ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ በአጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ሰላም ማስከበር በተሰማራባቸው ቦታዎች ሁሉ የዕለት ከዕለት ተግባሩ መሆኑን የደረሰላቸው ህዝቦች፤ መንግስታት እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሁሉ የሚያውቁት ሰመ ጥር ህዝባዊ ሰራዊት ነው፡፡
አገራችን ኢትዮጵያ ለሰራዊቷ ደመወዝና ቀለብ መስጠት ከጀመረች፤ ቀዳሚ ነን ከሚሉ ሃገራት ተርታ የምትሰለፍ ነፃ እና ታሪካዊት ሃገር ናት፡፡
ሰራዊታችን ዘመናዊ ነው ከሚያስብሉት አንዱ ደግሞ ይኸው ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የሎጅስቲክ ግዥ እና አቅርቦት ጉዳይ ነው፡፡ የሰራዊታችን ቀለብ ለሃገር ውስጥ ነጋዴዎች እድሉን በመስጠት በግልፅ ጨረታ ተወዳድረው ስንዴም ሆነ ሌሎች ምግብ ነክ ፍጆታዎች የሚቀርብለት በተሟላ አሰራር እና አመራር የሚመራ ሰራዊት ነው፡፡
የኢፌዲሪ መከላከያ ሰራዊት፡-
1ኛ/ ሠራዊታችን በቂ ሎጄስቲክ ያለው በዓለም አቀፍና በአገር ውስጥ ለተፈናቀሉትና በድርቅ ለተጎዱት በዓይነትና በገንዘብ የሚረዳ እንጂ ተቸግሮ ከአሰራር ውጭ የሚጠቀም አይደለም።
2ኛ/ ሠራዊታችን ማንኛውንም ዓይነት ምግብ በበጄቱ በሕግና በግልፅ ጫረታ ገዝቶ የሚጠቀም እንጂ ተቸግሮ የሕዝብ እርዳታ አካባቢ ሄዶ እርዳታ ላይ የሚሻኮትበት ዓይነት ድህነት የለበትም። ጥቆማ የሰጠ አካል እንኳ ቢኖር እስኪጣራ ሳይጠበቅ፤ እንደ ተቋምና እንደ ሠራዊት ስም የሚያጠፋ የሚዲያ ሽፋን መስጠት የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት ክብር ይነካል።
3ኛ/ ምንም እንኳ አገራችን በሚሊዮን የሚቆጠር እርዳታ ጠባቂ ሕዝብ ቢኖራትም ሠራዊቷን መመገብ የምትችልና በቂ ምግብና በጄት በመመደብ ሠራዊቱ ራሱ በሕግና በተቋም ሎጄስትክ አማካኝነት የምትመግብ አገር ናት። ሠራዊታችንም ኩሩና የችግረኞችን ስንዴ የማይሻማ ፕሮፌሽናል ሠራዊት ነው። ስለሆነም የእርዳታ ስንዴ የሚጠቀም ተቋም ወይም ዩኒት ወይም ወታደር የለንም።
4ኛ/ ዩኤስኤአይዲ (USAID) በሠጠው መግለጫ መሠረት ምናልባት የመከላከያ አባል የሆነ ወታደር በማይመለከተው ገብቶ ከመዋቅር ውጪ ሕግ የማስከበር ሥራውን ተጠቅሞ ከሌቦች ጋር በመተባበር እርዳታ ተሰርቆ እንዲወጣ በግል የተባበረ ካለ እና ተጣርቶ ከተገኘ የአገር መከላከያ ሠራዊት አመራር የማያዳግም እርምጃ ይወስዳል።
መከላከያ ሰራዊት ለሃገሩም ሆነ ለዓለም አቀፍ ሰላም መከበር መሰዋትነት የሚከፍል ምስጉን ሰራዊት ሆኖ እያለ፤ በአገራችን ውስጥና በውጪ አገር ያሉ ጥቂት የአገር መከላከያ ሠራዊት ጥላቻ ያላችው ፅንፈኞች እንዳሉ እናውቃለን። መካላከያን የማጠልሸት ሥራ የቆየና የለመድነው ነው።
የመከላከያ ሠራዊታችንን ህዝባዊ ተፈጥሮ፣ አሰራርና ሥርዓት ሳይታወቅና መረጃ እንኳ ቢመጣ፤ አጣርቶ ሳይታወቅ፤ መረጃ የቀረበበት አካል ሳይጠየቅ፤ የሚዲያ ሽፋን መሰጠት ትክክል አይደለም ብለን እናምናለን። የሚመለከታቸው የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶችና የኢትዮጵያ መንግሥት እንዲያጣሩ እንተባበራለን። ከተጣራ በኋላ ሁሉንም ለሕዝብ ይፋ እናደርጋለን።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር


በርካታ አዋቂዎች እንደሚሉት ኢትዮጵያን ጨምሮ አንዳንድ አገራት በቀለብ የራሳቸውን ከርስ እንዲችሉ አይፈለግም። ይህ ቢሆንማ ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራና በስንዴ ምርት እያሳየች ያለቸውን ጥረት እውቅና በመስጠት መርዳት ቀዳሚ ይሆን ነበር። አፋርና ሶማለኤ ክልል ስንዴ ሲያመርቱ አድንቆ ድጋፍ የደረግ ነበር። ዓላማው በሰብአዊ እርዳታ ስም ሰላዮች መንግስትን ለማፍረስ፣ ያሻቸውን ተላላኪ ለማንገስ፣ ለበለጸጉ ማዕድናት ዝርፊያና ወዘተ ስለሚጠቀሙበት ችጋርን ያበረታቱታል። ይህ ሲባል ከረሃብተኞች ዜጎቻቸው የሚዘርፉ የሉም ማለት ግን አይደለም።

በኢትዮጵያ ታሪክ ከረሃብተኞች ጉሮሮ በመዝረፍ የዛሬ የአማራ ግንባር መሪ ናቸው የተባሉት የ86 ዓመቱ ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ ቅድሚያ የሚጠቀሱና ምን አልባትም በኢትዮጵያ ከረሃብተኞች መንጋጋ ዘርፎ በመኮበለል ቁጥር አንዱ ሌባ ሳይሆኑ አይቀርም። ይህን ዝርፊያቸውን እሳቸው፣ ዘመዶቻቸው፣ ወዳጆቻቸውማ ሆነ የትኛውም በስለላና ኢትዮጵያን ባምፈራረስ የቀጠራቸው ተቋም ሊያስተባበለው የማይችል በሰነድ የተደገፈ ሃቅ ነው።

ዕርዳታ ሰጪ አገሮች በተለይም አሜሪካ ረሃብን የሚታደግ ደግ መስላ ወያኔን ኢትዮጵያ ላይ ተክላለች። በዕርዳታ ዕህል ሽያጭ መሳሪ የመሸመቺያ ብር አግኝቶና ነጻ ኮሪዶር ተከፍቶለት ራሱን መንግስት ለማድረግ የበቃው ትህነግ “የስንዴ ልጅ” በሚል በታሪክ ሲዘከር የሚኖረው አመጣጡ ስለሚታወቅ ነው። ይህም በበቂ መረጃ በራሱ ሰዎች ምስክርነት የተሰጠበት ጉዳይ ነው።

በቅርቡ በተጠናቀቀው የትግራይ ጦርነት ዕርዳታ ሰጪ መስለው የሎጅስቲክና የውጊያ እቅድ ከማዘጋጀት ጀምሮ ለትህነግ ድጋፍ ሲያደርጉ የነበሩ፣ ትግራይ ሆነው ከሚዲያዎች ጋር በመናበብ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ ሲያፋፍሙ የነበሩ ከተሸነፉ በሁዋላ፣ የተያያዙት የጀመሩትን የኢኮኖሚ ማሽመድመድ ዘመቻ ማጠናከርና የስንዴን ፖለቲካ ማቀጣጠል እንደሆነ ሲነገር ሰንብቷል።

ትህነግ ከደሃ ጉሮሮ ስንዴና ዱቄት፣ ከህጻናት ላንቃ አልሚ ምግብ እየዘረፈ መንጋ ሰራዊቱን ሲቀልብ ያልተነፈሱ፣ በየምሽጉ ሊጥ ከሚያገናፋበት ድስትና የብስኩት እሽግ ጋር እንጅ ከፍንጅ በማስረጃ ተያዞ ዝምታን የመረጡት አሜሪካኖች በዚህ ደረጃ አዲስ ዘመቻ መክፈታቸው ሳይሆን አስገራሚው ይህን ዘመቻ በማራገብ አገራቸው ላይ በላ የሚያውጁ ወገኖች ናቸው።

ዩኤስ ኤይድና የዓለም የምግብ ድርጅት ተናበው የአገር መከላከያን ጨምሮ ስሙን በማጠልሸት ” ስንዴ ስለሚዘረፈ አንረዳም” ማለታቸውን ተከትሎ መንግስት ” ውሳኔው ፖለቲካዊ ነው” ሲል ያስታወቀው አካሄዱን ስለሚያውቀው፣ የወልቃይት ኮሪዶርን ባለ በሌለ አቅሙ ጠርቅሞ በመዝጋት ድል እንዴት እንዳደረገ ስለማይዘነጋ ነው።

እነዚህ አካላት በጦርነቱ ወቅት አይናቸውን ታጥበው ኢትዮጵያ ላይ በገሃድ ዘመቻ ሲያካሂዱ እንደነበር አይዘነጋም። በተለይ የዩኤስ አይዲዋ ሳማንታ ፓዎር ከአንድ የትህነግ ስራ አስፈጻሚ በላቀ ደረጃ ስታካሂድ የነበረውን አቋም ለሚያስታውሱ ዛሬ ለምን መከላከያን ማጠልሸት እንደተፈለገ ግልጽ ነው።

ከውስጥ ባንዳዎች ጋር በመናበብ የአገር መከላከያን ለማጠልሸት እየተካሄደ ያለው ዘመቻ ዳግም ይህንኑ ሰራዊት እንዲበተንና አገሪቱ እንደ አገር እንዳትቆም የማድረግ ህልም ካልሆነ በቀር ሌላ ዓላማ እንደሌለው ዜጎች ሊረዱት ይገባል። መከላከያ ለኢትዮጵያዊያን ቀይ መስመራቸው መሆኑ ተረስቶ ከሃጂዎች ከውስጥ፣ የስንዴ ፖለቲከኞች ከውጭ ተናበው የሚያካሂዱትን ዘመቻ መመከት አገራዊ ሃላፊነት ነው።


የሁመራ ኮሪደር ድብቅ አጀንዳ “አሸባሪና የሽብር ትጥቅ ይግባና ፈራርሱ እያሉን ነው”

የዩ.ኤስ.ኤይድ ዳይሬክተር ሳማንታ ፓወር በሱዳን እና ኢትዮጵያ እያደርጉት ያለው ጉብኝት በኢትዮጵያን ላይ ጫና በማድረግ እየሆነ ያለው ሴራ አካል


ሌቦች የሉም የሚል የጅል መከራከሪያ ለማቅረብ ሳይሆን መከላከያ ላይ ለምን ተነጣጠረ? የሚለውና ዝርዝር መረጃው ሳይቀርብ በቅብብል ውሳኔውን ተከትሎ ” ወፏ ነገረችን” በሚል ሚዲያዎች እያቀጣጠሉት ያለው ይኸው ጉዳይ ማረፊያው የት ነው? የሚለውን መመርመር አስፈላጊ ስለሚሆን ነው። ብሉምብረግና ሮይተርስ ከዜናው ስርስር እየሄዱ ” እንቶኔ” እያሉ መከለካያን ለማጨቅየት የሚዘግቡት፣ እነሱኑ እንደ መረጃ እያጣቀሱ ጭቃውን ጭቃውን ወደ አማርኛ መስልሰው የሚያሰራጩት ሁሉም ዓላማቸው ምን እንደሆነ ያለፉት ዓመታቶች በይፋ ስላስተማሩን ቆም ብሎ መመረመር ግድ ይሆናል።



ቢቢሲ የሁሉንም አካል መረጃ ሰስቤ አዘጋጀሁ ሲል በራሱ ቅጭት ውስጥ ሆኖ የሰራጨውን ከስር ያንብቡ።

የኢትዮጵያ መንግሥት እርዳታ ማቋረጥ ‘ፖለቲካዊ’ እርምጃ ነው ሲል ተቃወመ

የኢትዮጵያ መንግሥት በአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት – ዩኤስኤአይዲ የተወሰደውን የእርዳታ አቅርቦትን የማቋረጥ ውሳኔ ‘ፖለቲካዊ’ ነው ሲል ተቃወመ።

ዩኤኤአይዲ በአገሪቱ ለተረጂዎች የሚያቀርበው የምግብ እርዳታ ከታለመለት ዓላማ ውጪ ጥቅም ላይ መዋሉን በመግለጽ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚያሂደውን የእርዳታ አቅርቦት ማቋረጡን ከቀናት በፊት አሳውቆ ነበር።

የኢትዮጵያ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጽህፈት ቤት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ዛሬ ቅዳሜ ሰኔ 03/2015 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ ላይ፣ ውሳኔው በመንግሥት ተቀባይነት የሌለው መሆኑን በመግለጽ ተችተውታል።

ሚኒስትሩ እርምጃው “የጅምላ ውሳኔ” መሆኑን በመግለጽ፣ በዚህም ሚሊዮኖችን መቅጣት “ፖለቲካዊ እንጂ ሰብአዊ ገጽታ የለውም” ብሎ መንግሥታቸው እንደሚያምን አመልክተዋል።

በተጨማሪም የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤአይዲ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መንግሥት ተቋማትን መልካም ስም አጉድፏል ሲሉ ዶክተር ለገሰ ወቅሰዋል።

የአሜሪካ መንግሥት የእርዳታ ድርጅት ለተረጂዎች የታለመውን የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት ከታለመለት ዓላማ ውጪ በማዋሉ በኩል የፌደራል እና የክልል መንግሥታት ተቋማትን እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊቱ ተሳታፊ መሆናቸውን አመልክቶ ነበር።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ የምግብ እርዳታ አቅርቦት ያላግባብ ጥቅም ላይ መዋሉን በተመለከተ የሚደረገውም ምርመራ ሳይጠናቀቅ ዩኤስኤአይዲ ያወጣው መግለጫ የፌደራል፣ የክልል መንግሥታትን እንዲሁም የመከላከያ ሠራዊቱን “መልካም ገጽታን የሚያጠለሽ ነው” ብለዋል።

ሚኒስትሩ ጨምረውም ምርመራ በተደረገባቸው ቦታዎች የእርዳታ አቅርቦቱ እና ሥርጭቱ በራሱ መዋቅር የሚከናወን ሆኖ ሳለ “ዩኤስኤአይዲ መንግሥትን ብቻ ተጠያቂ ለማድረግ የተጓዘበት ርቀት ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም” በማለት ተቃውመውታል።

የአሜሪካ መንግሥት የእርዳታ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው “ለኢትዮጵያ ሕዝብ መቅረብ የነበረበት የምግብ እርዳታ በከፍተኛ መጠን እና በተቀናጀ ሁኔታ ከታቀደለት አላማ ውጪ ጥቅም ላይ በመዋሉ” መሆኑን ገልጿል።

የአሜሪካ መንግሥት የተራድኦ ድርጅት ውሳኔውን ባሰወቀበት ጊዜ “የተደረገውን አገር አቀፍ ቅኝት ተከትሎ ዩኤስኤአይዲ፣ በእርዳታ አቅርቦቱ ላይ ለውጥ እስኪደረግ ድረስ በዚህ ሁኔታ መቀጠል ስለማይቻል፣ አስቸጋሪ ነገር ግን አስፈላጊ ውሳኔ አሳልፈናል” ማለቱ ይታወሳል።

የሰብአዊ እርዳታ ምግብ ከታለመለት አላማ ውጪ “በፌደራል እና በክልል የመንግሥት አካላት ተባባሪነት በመላው አገሪቱ ላሉ ለኢትዮጵያ ሠራዊት ክፍሎች ቀርቧል” ብሎ የአሜሪካው የተራድኦ ድርጅት እንደሚያምን ሮይተርስ ተመለከትኩት ያለው አንድ ሰነድ ማመልከቱን ዘግቦ ነበር።

ባለፉት ሁለት ወራት የተካሄደ ምርመራ በለጋሾች የተገዛ የምግብ እርዳታ ከታለመለት አላማ ውጪ መዋሉን እና ለገበያ መቅረቡን እንዲሁም በአንዳንድ ሁኔታዎችም ወደ ውጪ አገራት ጭምር መላኩን ብሉምበርግ ተመለከትኩት ያለው ሰነድ አሳይቷል።

ይህንንም ተከትሎ ዩኤስኤአይዲ በመላው ኢትዮጵያ በግጭት እና በድርቅ ምክንያት በእርዳታ ጥገኛ ለሆኑ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች የሚያቀርበውን የምግብ እርዳታ መቋረጡን ያሳወቀ ሲሆን፣ መንግሥት ግን ውሳኔውን ተቃውሞታል።

በተመሳሳይ ከዚሁ የእርዳታ ምግብ አቅርቦትን ከታሰበለት ዓላማ ውጪ ተጠቅሟል በሚል ስሙ የተነሳው የመከላከያ ሠራዊትን በተመለከተ የኢትዮጵያ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ የቀረበበትን ክስ አስተብብሏል።

ሚኒስቴሩ እንዳለው ሠራዊቱ አስፈላጊው አቅርቦት እና ድርጅት ያለው መሆኑን አመልክቶ፣ በመሆኑም በውስጡ “ለእርዳታ ተብሎ የቀረበን ስንዴ የሚጠቀም ተቋም ወይም ዩኒት ወይም ወታደር የለም” ሲል ተቃውሞውን አሰምቷል።

የእርዳታ ምግብ አቅርቦትን አላግባብ ከመጠቀም ጋር በተያያዘ የአሜሪካ መንግሥት የተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) አቅርቦቱን ማቋረጡን ተከትሎ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራምም ተመሳሳይ እርምጃ መውሰዱን አርብ ዕለት አሳውቋል።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከአንድ ወር በፊት ለተረጂዎች የቀረበ ከፍተኛ መጠን ያለው የምግብ እርዳታ ለሌላ ዓላማ ውሏን በሚል በትግራይ ክልል ውስጥ ሲያካሂድ የነበረውን የምግብ አቅርቦት ማቋረጡ ይታወሳል።

ይህ በእንዲህ እናዳለ የሰብአዊ እርዳታ ተቋሙ ‘ሪፊዩጂ ኢንተርናሽናል’ ለቢቢሲ በላከው መግለጫ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ “የእርዳታ አቅርቦት በከፍተኛ መጠን በተቀናጀ ሁኔታ ለሌላ አላማ መዋሉ” መታወቁን ተከትሎ፣ የአሜሪካ መንግሥት “ይህ አይነቱ ድርጊትን እንደማይታገስ” በግልጽ ማሳየት አለበት ብሏል።

የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን በበኩሉ የእርዳታ አቅርቦት እንዲቋረጥ መደረጉ ሚሊዮኖችን ለችግር የሚዳርግ እና ለቀውስ የሚያጋልጥ በመሆኑ “እንደማይቀበለው” በመግለጽ ውሳኔው መለስ ተብሎ እንዲጤን ጠይቋል።

እንዲሁም በዚህ የእርዳታ አቅርቦትን ከታለመለት ዓላማ ውጪ እንዲውል በማድረግ በኩል የተሳተፉ አካላት በምርመራ በማስረጃ ተረጋግጦባቸው ሲገኝ እርምጃ ለመውሰድ መንግሥት ዝግጁ መሆኑንም ገልጿል።

በኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ በግጭት እና በድርቅ ምክንያት የእርዳታ ድጋፍን የሚሹ ወደ 20 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች እንዳሉ ይነገራል።

የአሜሪካ መንግሥት በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚሊዮኖች ከፍተኛውን ሰብአዊ እርዳታን በማቅረብ ዋነኛው ሲሆን፣ የእርዳታ አቅርቦቱ ሥርዓት አስተማማኝ መሆኑ ከተረጋገጠ እርዳታውን መልሶ እንደሚጀመር ገልጿል።

Exit mobile version