Site icon ETHIO12.COM

የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት – የአክሲዮን ግዢን ጨምሮ ህዝብ እንዳይጭበረበር አሳሰበ – የገንዘብ ዝውውርን እየመረመረ ነው

ተቋማችን የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ፣ ሽብርተኝነትንና ጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎችን ብዜት በገንዘብ የመደገፍ ወንጀሎችን መከላከልና መቆጣጠር እንዲቻል ከተለያዩ አካላት የፋይናንስ ወንጀል ነክ መረጃዎች በመቀበል፣ በመሰብሰብና በመተንተን ውጤቱን ለሚመለከታቸው አካላት በማሰራጨት እንዲሁም በመሰል ጉዳዮች ላይ ከህግ አስከባሪ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ላይ ይገኛል

በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በመሰማራት ራሳቸውን፣ ህብረተሰቡንና አገርን ተጠቃሚ የሚያደርጉበት የህግና የአሰራር ስርዓት ያላት ከመሆኗም በተጨማሪ ለኢንቨስትመንት ከፍተኛ ፍላጎትና ዕድል ያላት አገር መሆኗም ይታወቃል። የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴዎች ለአገር ከፍተኛ እና የማይታካ አዎንታዊ ፋይዳ እንዳላቸው ማንም የሚገነዘበው ነው።

ሆኖም አንዳንድ ግለሰቦች እና ድርጅቶች በኢንቨስትመንት እና በአብረን እንስራ ስም ተጨባጭና የተሟላ መረጃ ሳይሰጡ ከፍተኛ ገንዘብ ከህብረተሰቡ እየሰበሰቡ መሆናቸውን ለአገልግሎቱ የደረሰው መረጃ ያመለክታል።

ገንዘብ ከህብረተሰቡ ለመሰብሰብም እጅግ አትራፊ የሆነ የግብርና እና የሪል ስቴት ኢንቨስትመንት ላይ መሰማራታቸውን በመግለፅ ቅንጡ የመኖሪያ አፓርትመንቶችን በዝቅተኛ ዋጋ መግዛት እንዲሁም አክሲዮን በመግዛት በአጭር ጊዜ ውስጥ ትርፋቸውን በእጥፍ ማሳደግ እንደሚችሉ በተለያዩ መንገዶች እያስተዋወቁና ገንዘብ እየሰበሰቡ መሆናቸው መገንዘብ ተችሏል።

ጤናማ የፋይናንስ እንቅስቃሴ እና ኢንቨስትመንት በእጅጉ የሚደገፍ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በኢንቨስትመንት ስም የሚፈፀሙና ሊፈፀሙ የሚችሉ ወንጀሎችንም መከላከል በዚያው ልክ አስፈላጊ ይሆናል። ስለሆነም ህብረተሰቡ ከመሰል ድርጊቶች ጋር ተያይዞ ሊፈፀም ከሚችል መጭበርበር ራሱን እንዲጠብቅ፣ የጥንቃቄ እርምጃም እንዲወስድ አገልግሎቱ ያሳስባል።

ተቋማችን የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብ ወይም ንብረት ህጋዊ አስመስሎ ማቅረብ፣ ሽብርተኝነትንና ጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎችን ብዜት በገንዘብ የመደገፍ ወንጀሎችን መከላከልና መቆጣጠር እንዲቻል ከተለያዩ አካላት የፋይናንስ ወንጀል ነክ መረጃዎች በመቀበል፣ በመሰብሰብና በመተንተን ውጤቱን ለሚመለከታቸው አካላት በማሰራጨት እንዲሁም በመሰል ጉዳዮች ላይ ከህግ አስከባሪ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ላይ ይገኛል።

ህብረተሰቡም ከወንጀሎቹ ጋር በተያያዘ በአንድ በኩል ራሱን ከወንጀል በመጠበቅ አጠራጣሪ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ ደግሞ እንደተለመደው ለተቋማችን ጥቆማ በመስጠት የድርሻውን እንዲወጣ በዚሁ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።

የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት
ሰኔ 06 ቀን 2015 ዓ.ም

Exit mobile version