የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ቴድሮስና ባለቤታቸውን ጨምሮ 6 ተከሳሾች እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ

የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ቴድሮስ በቀለ እና ባለቤታቸው ወ/ሮ ሩት አድማሱን ጨምሮ 6 ተከሳሾች በተከሰሱበት የሙስና ወንጀል እንዲከላከሉ ብይን ተሰጠ።

ሌላ በ7ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሰ ተከሳሽ ደግሞ በሌለበት በሁለተኛው ክስ ጥፋተኛ ተብሏል። ብይኑን የሰጠው የፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ልደታ ምድብ 5ኛ የሙስና ጉዳዮች ወንጀል ችሎት ነው።

አጠቃላይ ተከሳሶቹ 1ኛ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳሪክተር የነበሩት አቶ ቴድሮስ በቀለ፣ 2ኛ ተከሳሽ የአቶ ቴድሮስ ባለቤት ወ/ሮ ሩት አድማሱ፣ 3ኛ የወ/ሮ ሩት እህት የሆነችው ቤተልሄም አድማሱ እና በግል ስራ ይተዳደራሉ የተባሉት መርሀዊ ምከሰረ ወ/ፃዲቅ፣ ራሄል ብርሀኑ፣ ፀሀይ ደሜ እና ጌታቸው ደምሴ ናቸው።

የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት አጠቃላይ ሁለት ክሶችን የመሰረተ ሲሆን አንደኛው ክስ በአቶ ቴድሮስ በቀለ ላይ ብቻ የቀረበ ሲሆን በሁለተኛው ክስ ደግሞ ከ1ኛ እስከ 7ኛ ተራ ቁጥር በተጠቀሱ አጠቃይ ተከሳሶች ላይ በዝርዝር ቀርቧል።

በአንደኛው ክስ ላይ እንደተመላከተው የሙስና ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9(1) (ሀ) እና (3) ላይ የተመለከተውን በመተላለፍ አቶ ቴድሮስ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሲሰሩ የተቋሙን አሰራር ባልተከተለ መልኩ አስፈላጊው የደህንነት ይለፍ (secuirty clearance) ያልተደረገለትን የትምህርት ዝግጅቱ ብቁ ያልሆነ በሌላ የሙስና ወንጀል መዝገብ የተከሰሰ አቤል ጌታቸው የተባለ ግለሰብን በታህሳስ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በተቋሙ የተደራጁና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳት ወንጀሎች ፍተሻና ትንተና ከፍተኛ ኤክስፐርት ሆኖ እንዲሰራ ወደ ተቋሙ እንዲቀላቀል አድርገዋል በሚል ዐቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሶ ነበር።

በዚህም በሰኔ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ ደግሞ አቤል ጌታቸው የተባለውን ግለሰብ የፋይናንስ መረጃ ክትትል እና ቅበላ ቡድን መሪ አድርገው ባልተገባ መንገድ መመደባቸው በክሱ ተዘርዝሯል።

የተቋሙን የቀደመ የመረጃ ሚስጥራዊነት የጠበቀ እና ተጠያቂነትን ያማከለ የመረጃ ቅበላ እና ትንተና አሰራርን በመለወጥ በተቋሙ ውስጥ ስልጣንን ተገን በማድረግ የባለሀብቶችንና የድርጅቶችን የባንክ ሂሳብ አስቀድሞ በማጥናትና መረጃ በመውሰድ በተለያዩ ጊዜያት ለባለሀብቶች ስልክ በመደወል በአካል በማግኘት ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እንዲከፍሉ በመጠየቅ የማይከፍሉ ከሆነ ደግሞ የፋይናንስ እንቅስቃሴያቸውን በተመለከተ ምርመራ አድርጎ ለፖሊስ በማስተላለፍ የወንጀል ምርመራ እንዲጀመርባቸው ይደረግ ነበር በማለት ዐቃቤ ሕግ በክሱ ጠቅሷል።

See also  የአርሂቡ ሪል ስቴት ግንባታ ታገድ፤ በስራ ላይ እያሉ በሞቱት ሶስት ሰራተኞች ሳቢያ በህግ ሊጠየቅ ነው

አጠቃላይ ተከሳሹ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ውስጥ የነበረውን ኃላፊነትን በመጠቀም የፋይናንስ ትንተና በመስራት ውጤቱን ለፍትህ አካላት የሚተላለፍ ስልጣንን አላግባብ በመጠቀም ገንዘብ ያላቸው ባለሀብቶችን አስቀድሞ በማጥናትና በመምረጥ በ2013 ዓ.ም እና በ2014 ዓ.ም በተለያዩ ጊዜያት ባለሀብቶች የባንክ ሒሳባቸው እንደሚታገድ እና በፖሊስ ምርመራ እንደሚደረግባቸው በመግለጽና በማስፈራራት ከ3 ግለሰቦች በአጠቃላይ 3 ሚሊዮን 470 ሺህ ብር ገንዘብ በፋፋ ዳባ በተባለ ስም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገቢ እንዲሆን በማድረግ በዋና ወንጀል አድራጊነት ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ ሙስና ወንጀል ተከሷል።

ሁለተኛ ክስ በሁሉም ተከሳሾች ላይ የቀረበ ሲሆን በዚህም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1/ሀ እና በወንጀል ድርጊት የተገኘ ገንዘብን ወይም ንብረትን ህጋዊ አድርጎ ማቅረብና ሽብርተኝነትን በገንዘብ መርዳትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣውን አዋጅ ቁጥር 780/2005 አንቀጽ 29 (1) (ሀ) (ለ) እና (ሐ) ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ተከሳሾቹ ከላይ በተጠቀሰው መልኩ በወንጀል የተገኘ 3 ሚሊዮን 470 ሺህ ብር የወንጀል ፍሬ መሆኑን እያወቁ የገንዘቡን ምንጭ ለመደበቅ በማሰብ ግብረአበር ነው የተባለ ፋፋ ዳባ እየተባለ የሚጠራ ግለሰብ ስም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በተከፈተ ሒሳብ ገቢ እንዲሆን በማድረግና ከዚሁ ከተጠቀሰው ገንዘብ በተለያዩ መጠን በመጠቀም ህገ ወጥ ገንዘብን ህጋዊ አስመስሎ ማቆረብ ወንጀል ተከሰዋል።

ከ1ኛ እስከ 6ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ተከሳሾቹ ከጠበቆቻቸው ጋር ቀርበው ክሱ እንዲደርሳቸው ከተደረገ በኋላ በችሎት ክሱ በንባብ ከተሰማ በኋላ ወንጀሉን አለመፈጸማቸውን ጠቅሰው የዕምነት ክህደት ቃላቸውን ሰጥተው ነበር።

ከሳሽ ዐቃቤ ሕግ ከአምስት በላይ ምስክሮችን አቅርቦ አሰምቶ ነበር።

ፍርድ ቤቱ የዐቃቤ ሕግ ምስክር ቃልን መርምሮ ዛሬ በዋለው ችሎት ብይን ሰጥቷል።

በዚህም አንደኛው ክስ የቀረበባቸው አቶ ቴድርሮስ ላይ የተሰሙ ምስክሮች ቃል ተመርምሮ ወንጀሉ መፈጸሙን በምስክር ተረጋግጧል በማለት ፍርድ ቤቱ እንዲከላከሉ ብይን ሰጥቷል።

ይከላከሉ የተባሉት በሙስና አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 ንዑስ ቁጥር 1 እና በንዑስ ቁጥር 2 ስር ነው።

በሁለተኛው ክስ ደግሞ ማለትም በቀረበው በህገወጥ መንገድ የተገኘ ገንዘብን ህጋዊ አድርጎ ማቅረብና መገልገል ወንጀል የተከሰሱት ከ2ኛ እስከ 6ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሱት ተከሳሾች የወንጀል ድርጊቱ ስለመፈጸመ በዐቃቤ ሕግ ምስክር የተረጋገጠ መሆኑን ተጠቅሶ እንዲከላከሉ ብይን ተሰጥቷል።

See also  በሙስና ወንጀል የተከሰሱት ሁለቱ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኞች የክስ መቃወሚያቸውን አቀረቡ

በዚሁ ክስ 7ኛ ተራ ቁጥር የተጠቀሰው ተከሳሽን በሚመለከት በሌለበት ጥፋተኛ ተብሏል።

አቶ ቴድሮስ በቀለን በዚሀ ሁለተኛ ክስ የወንጀል ተግባሩ ስለመፈጸማቸው በሰው ማስረጃ አለመረጋገጡ ተገልጾ ነጻ ተብለዋል።

ተከሳሾቹን የመከላከያ ማስረጃ ለመጠባበቅ ለህዳር 20 እና ህዳር 21 ቀን 2016 ዓ.ም ተቀጥሯል።

በታሪክ አዱኛ – FBC


Leave a Reply