Site icon ETHIO12.COM

የጠፈር ሽርሽር በረራ ሊጀመር ነው

በጠፈር ቱሪዝም ላይ የተሰማራው የእውቁ ባለሃብት ሰር ሪቻርድ ብራንሰን ቨርጅን ጋላክቲክ ኩባንያ ከሁለት ሳምንታት በኋላ ለጉብኝት የሚደረገውን የመጀመሪያውን የጠፈር በረራ እንደሚጀምር አስታወቀ።

ኩባንያው ጋላክቲክ 01 ሲል የጠራውን በረራ ከሰኔ 20 እስከ 23 2015 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ለማድረግ መወሰኑን ገልጿል። ይህን ውጥን ይፋ ሲያደርግ የቨርጅን ጋላክቲክ የገበያ ድርሻው 40 በመቶ ተመንድጓል። ባለፈው ወር የዩኬው ባለሀብት ሪቻርድ ብራንሰን ቨርጅን ኦረቢት የተባለ ሌላ ኩባንያ ተልዕኮዎቹ ከተጨናገፉ ከወራት በኋላ ተዘግቷል።

ቨርጅን ጋላክቲክ ኩባንያ በመጀመሪያ በረራ ሳይንሳዊ ጥናት የማድረግ ተልዕኮ አለው። በዚህ በረራ የሚካተቱት የቡድን አባላት ከጣልያን አየር ኃይልና ከጣልያን ብሄራዊ ጥናት ማዕከል የሚመጡ ተጓዦች ሲሆኑ ‘ማይክሮግራቪቲን’ ያጠናሉ ተብሏል።

ኩባንያው ከዚህ የመጀመሪያ ጉዞ በኋላ ቀጣዩ በረራ ሃምሌ ላይ የሚደረግ ሲሆን፤ ከዚያም በኋላ በየወሩ በረራ እንደሚደረግ ይጠበቃል። ይህ የጠፈር በረራ 19 ዓመታትን ላስቆጠረውና በቴክኒክ ችግሮች እንዲሁም ተከታታይ አደጋዎች ላጋጠሙት ቨርጅን ጋላክቲክ ጉልህ ለውጥ ይሆናል።

ባለፈው ወር የኩባንያው ‘ዩኒቲ’ ተብሎ የተጠራ የሮኬት አውሮፕላን ከሁለት ዓመታት በኋላ ወደ ስራ ተመልሷል። ሁለት ፓይለቶችን እና አራት ተሳፋሪዎችን ይዞ የነበረው ሮኬት ከአሜሪካዋ ኒው ሜክሲኮ በርሃ ተወንጨፎ ተመልሷል። ይህ በረራ ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው የንግድ አገልግሎት ከመጀመሩ በፊት የተደረገ ሙከራ ነው።

ቨርጅን ጋላክቲክ እስካሁን ከምድር 80 ኪሎ ሜትር ከፍ ብለው መብረር ለሚፈልጉ ከ800 በላይ ሰዎች ትኬት ሸጧል። በዚህ በረራ የሚካተቱ ተጓዦች ምድርን ከላይ ሆነው የሚመለከቱ ሲሆን፤ ለጥቂት ደቂቃዎች የመሬት ስበት በሌለበት ቦታ ደርሰው ስሜቱን ይጋራሉ። ይህ ጉዞ በአንድ ሰው 450 ሺህ የአሜረካ ዶላር ይከፈልበታል።

ቨርጅን ጋላክቲክ የጠረፍ ቱሪዝም ላይ ቢያተኩርም የሰር ሪቻርድ ኩባንያ በቨርጅን ኦርቢት አማካኝነት የሳተላይት ሮኬት የማስወንጨፍ እቅድም ነበረው። ሆኖም ቨርጅን ኦርቢት ባለፈው ወር ባጋጠመው የተልዕኮ መጨናገፍ ምክንያት ተዘግቷል። ይህም በዩኬ የጠፈር ዳሰሳ ትልቅ ለውጥ ሆኗል። በዚህ ዓመት መግቢያ ላይ ኩባንያው ሳተላይት እንደሚያመጥቅ ሲጠበቅ የነበረ ቢሆንም የገንዘብ አቅሙን ለማሳደግ ስራዎቹን አቁሞ ቆይቷል።

ሰር ሪቻርድ ባለፈው ወር ለቢቢሲ በሰጠው ቃለ መጠይቅ በግሉ የ1.9 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ እንደገጠመው ገልጿል። ባለሀብቱ የዚህ ኪሳራ መነሻ በኮቪድ 19 የእንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት የአየር መንገድና የመዝናኛ ንግዶቹ ያጋጠማቸው ኪሳራ እንደሆነ አመላክቷል።

“ሁሉንም ነገር እናጣለን ብዬ ያሰብኩበትም ጊዜ ነበር” ሲልም አክሏል። ሆኖም ሰውዬው ቢሊየነር ሆኖ መቆየት ችሏል። ባለፈው ዕሁድ የወጣው የታይምስ ባለጸጎች ዝርዝር ሰር ሪቻርድ ብራንሰን 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር የተጣራ ሀብት አለው ሲል የዘገበው ቢቢሲ አማርኛ ነው።

Exit mobile version