Site icon ETHIO12.COM

በአማራ ክልል የሸኔ ፖለቲካ ኮፒ፤ አድፍጦ መግደል በርክቷል

” አባ ቶርቤ” የሚባለው የሸኔ አንድ ክፍል የመንግስት መዋቅር ሃላፊዎችን እየመረጠ ይገድል ነበር። አድፍጦ ብቻ ሳይሆን ቤታቸው ዘንድ እየሄደ የገደላቸውን ቤተሰቦቻቸው መስክረዋል። ይህ ሃይል ሲገድል ኦነግም ሆነ ኦነግ ሸኔ ሃላፊነት አይወስዱም። በማህበራዊ መገናኛዎች ግን “ዋጋውን አገኘ” የሚል መረጃ ከምስል ጋር ይበተናል።

አሁን ላይ በኦሮሚያ የባለስልጣናት ግድያ ጋብ ሲል በኦሮሚያ ሲሆን እንደነበረው ዓይነት በአማራ ክልል እየታየ ነው። የዋናው ኦነግ ሸኔ አካል ሆኖ እንደ አንድ የትግል ስልት ርሱን ” አባ ቶርቤ” እንደሚለው አካል ስም ባይሰጠውም አምራ ክልልም በተመሳሳይ የምንግስት የመዋቅር ሰዎችንና የአካባቢ የጸጥታ ሃላፊዎችን መግደል እየተለመደ ነው።

ከተገደሉ በሁውላ አየር ላይ የዋሉት በርካታ ንግግሮቻቸው ከተገደሉም በሁዋላ ቢሆን አቶ ግርማ የሺ ጥላ ምን ዓየነት ሰው እንደነበሩ ለማወቅ ዕድል ሰጥቷል። ” ሃፍ ካስት ናቸው” ተብለው ተፈርጀው እንዲገደሉ ከተደረጉ በሁዋላ ግድያውን አስመልክቶ የወጡ መረጃዎች የግድያውን አቀነባባሪዎች ማንነት የሚያጠቁሙ ቢሆንም አሁን ድረስ ጉዳዩ በሚመለከተው አካል በይፋ ባለመገለጹ ወይም “እኔ ነኝ” ብሎ ሃላፊነት የወሰደ ስለሌለ በድርጅት ደረጃ በስም ለመጥራት ገና ነው።

ይህ በንዲህ እንዳለ ነው በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደጀን ወረዳ እና በሰሜን ሸዋ ዞን ሸዋ ሮቢት ከተማ የአካባቢ የፀጥታ ኃላፊዎች መገደላቸው ይፋ የሆነው። ሌሎችም ቀደም ሲሉ የተገደሉ አሉ። ቦንብ መጣልና ተቋማትን ለማፍረስ የሚደረግ ሙከራም መኖሩን የክልሉን ሁኔታ እንከታተላለን የሚሉ ሲዘግቡ ይሰማል። ባለፈው ሰኞና ማክሰኞ የተፈጸመውን ግድያ አስመልክቶ ዜናውን በድል አጅበው ያቀረቡ በራሳቸው ገጽ ብዙ ብለዋል። አካሄዱ እንደማይጠቅም ስጋት የገባቸውም ስጋታቸውን በሃዘን ገልጸዋል። የተጎጂዎች ቤተሰቦችን ጠይቆ የዘገበ አልተደመጠም።

“ፋሽስታዊው የኦሮሙማ መንግሥት ፣ የአማራን ህዝብ ለማንበርከክ State-Initiated brute force እንዲጠቀም በዋና ተላላኪነት እያገለገለ የሚገኘው የጠላት ብ.አ.ዴ.ን. የፖለቲካና የፀጥታ መዋቅር በመሆኑ ይህንን የባንዳ ሀይል ማፅዳት፥ ጦርነቱን ከ80% በላይ በድል የማጠናቀቅ ያህል ነው” ሲል የግድያውን አስፈላጊነት ጠቅሶ ሄኖክ አምሃራ ፊርስት የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በሌላ የፓርላማ ዜና ስር በአስተያየት መስጫ ሳጥን ውስጥ አስቀምጧል።

ድርጊቱ ኦነግሸኔ ሞክሮት ያልተሳካለትና ማህበራዊ ተቀባይነቱን ያጣበት፣ ዘግይቶም ቢሆን “እኔ የማወቀው አደረጃጀት አይደለም። እንዲህ የሚያደርጉትን ባገኝ እቀጣቸዋለሁ” ሲል ማስተባበያ ያቀረበበት መሆኑ ይታወሳል። ከዚህም በላይ አልፎ ሄዶ “ይህን የሚያደርጉ ክፍሎች ወደ አካባቢያችሁ ሲመጡ አሳውቁን” በሚል ስልክ ሰጥቶ እንደነበር ይታወሳል። ነገሩ ግራ የሚያጋባ ቢሆንም ድርጊቱ ምን ያህል ከህዝብ እንደነጠለው ማሳያ ስለመሆኑ በርካቶች ይስማማሉ። የምስል ማረጋገጫ ባይቀርብም አምቦ አካባቢ ኦነግ በስሜ ወንጀል ይፈጽማሉ ያላቸውን ይዞ ህዝብ ፊት እርምጃ መውሰዱም የአንድ ሰሞን መነጋገሪያ ነበር። ዜናውን የተከታተሉ “ረፈደ” ሲሉ ድርጅቱ ስሙ ከሚነሳበት ሰፊ ወንጀል አንሳር አካሄዱን “ቀልድ” ብለውትም እንደነበር ይታወሳል።

አሁን በአማራ ክልል የተጀመረው አዲሱ ትግል የመንግስትን የመዋቅር ሰዎችን በመግደል ምን ያህል ወደፊት እንደሚራመድ ባይታወቅም፣ ብዙዎችን የኢህአፓን ነጭ ሽብርና የደርግን ቀይ ሽብር ያስታወሰ ሆኗል።

የፖለቲካ ልዩነትን ተቀምጦ በመነጋገር ማስታረቅ እንኳን ቢቸግር፣ ማቻቻል እየተቻለ ወንድም ወንድሙን አድፍጦ መግደሉ ለክልሉም ሆነ ለአገሪቱ እንደማይጠቅም ከአቶ ግርም ግድያ በሁዋላ በስፋት ሲገለጽ ነበር። የአማራ ክልል መሪ ዶክተር ከፋለ “አማራን ለማወክና ማህበራዊ እረፍት ለመንሳት የተሰጠ አጀንዳ ነው” ሲሉ በስፋት በዚሁ ጉዳይ ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወሳል። በዚሁ መግለጫቸው የሌሎችን አሳብ አክብሮ መወያየት እንደሚቻልም ጠቁመው ነበር።

ይህ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየሰፋ የመጣው የክልሉ ችግር በቀና ውይይት ዕልባት ካልተገኘለት ክልሉን ለባስ ችግር፣ ህዝቡን ለመረረ ድህነት የሚዳርግ እንደሆነና ጊዜ ለሚጠብቁ አድፋጭ ጠላቶች ጥሩ አጋጣሚ እንደሚሆን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ማሳሰባቸው የሚዘነጋ አይደለም።

የሸዋ ሮቢት ከተማ ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ የሆኑት የአቶ አብዱ ሁሴን ግድያን ተከትሎ የከተማዋ አስተዳደር አሉ ያላቸውን የፀጥታ ችግሮች ለመቆጣጠር በከተማዋ ውስጥ የሰዓት ዕላፊ እና የእንቅስቃሴ ገደብ ጥሏል። በዚሁ መሰረት ከሰኔ 28 ጀምሮ ላልተውሰነ ጊዜ ማንኛውም የሰውም ሆነ የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ ገደብ ተጥሎባቸዋል። ባለፈው ዓመት የከተማዋ ከንቲባዋ መገደላቸው ይታወሳል። ከንቲባው አቶ ውብሸት አያሌው ነሐሴ 26/2014 ዓ.ም. ምሽት ሦስት ሰዓት ግድም ቤታቸው አቅራቢያ ለጊዜው ባላታወቁ ሰዎች ነበር በጥይት ተደብድበው የተገደሉት።

የደጀን ወረዳ አስተዳደር እንዳስታወቀው ሰኞ ሰኔ 26/2015 ዓ.ም. የወረዳው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር ዘውዱ ታደለ እና የወረዳው ፖሊስ ጽ/ቤት የወንጀል መከላከል ክፍል ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ወርቁ ሽመልስ በጥይት ተደብድበው ተገድለዋል። አብሯቸው የነበረ የፖሊስ አባል ሹፌር ቆስሏል።

የደጀን ወረዳ ሰላም እና ፀጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ካሳው አስፋው፣ ለቢቢሲ “በሁለቱ የፖሊስ ኃላፊዎች ላይ ግድያውን የፈጸመው የቀድሞ የልዩ ኃይል አባል ነው” ብለዋል። ገዳዩ ስለሚታወቅ በቁጥትር ስር ለማዋል እየተሰራ መሆኑንንም አምልክተዋል።

ይህን ግድያ ተከትሎ ክልሉ ለጊዜው ያለው ነገር የለም። የተቀናቃኝ ፓርቲዎችም ይህ እስከታተመ ድረስ ያሉት ነገር የለም። ግድያውን እንደፈጸመና ግድያውን ለምን ሲል እንደፈጸመ ሃላፊነት ወስዶ በገሃድ ያስታወቀም የለም።

ፎቶ ቢቢሲ

Exit mobile version