Site icon ETHIO12.COM

አዲስ በሚጀመረው የካፒታል ገበያ – ከወዲሁ ፈላጊዎች በርክተዋል

በኢትዮጵያ በቀጣዩ አዲስ ዓመት የሚጀመረው የካፒታል ገበያ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች ፍላጎት የሳበ እንደሆነ ተመለከተ። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ለፓርላማ በአደረጉት ንግግር በይፋ ” በካፒታል ገበያ ተሳተፉ፣ ኢንቨስት አድርጉ” ሲል መናገራቸውን ተከትሎ ነው ይህ የታወቀው።

በኢትዮጵያ ቴሌኮሙኒኬሽንን ዘርፍ የግል ባለሃብቶችና የውጭ ኩባንያዎች መሳተፍ መጀመራቸው፣ ለተወሰኑ የውጭ ባንኮች ፈቃድ መሰጠቱ መንግስት ለግሉ ኢንቨውስትመንት መነቃቃት ከፍተኛ ዕድል እንደሚፈጥር ማስታወቁ አይዘነጋም። በዚህ ሳያበቃ በአገሪቱ ታላላቅ አትራፊ ተቋማት ላይ ስቶክ መግዛትና መሳተፍ እንዲቻል መፍቀዱን ተከትሎ ሃላፊዎች እንዳሉት ሰፊ ፍላጎት አለ።

የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶች በ2016 በጀት ዓመት በሚጀመረው የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ውስጥ ለመሳተፍ ከወዲሁ ፍላጎታቸውን እያሳዩ መሆኑን ያስታወቀው የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ነው።

የካፒታል ገበያ ባለሃብቶች፣ ድርጅቶች፣ ግለሰቦች ወይም መንግስት ለሚያስፈልጋቸዉ ኢንቨስትመንት ካፒታል በጥሬ ገንዘብ አሊያም በአይነት የሚያሰባስቡበትና የሚያገኙበት ገበያ ነዉ፡፡

ይህም ካፒታል በማሰባሰብ፣ የገንዘብ ሥርዓቱን በአዲዲስ ፈጠራዎች በመደገፍ እና ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት የአገሪቱን ኢኮኖሚ ልማት ያግዛል፡፡

በተጨማሪም በቀላሉ ቢዝነስ ለመጀመር፣ ለማስፋፋት እና የሚያስፈልጉ ጥሬ እቃዎችን በአፋጣኝ ለማግኘት እንዲሁም የዉጭ ኢንቨስተሮችን በቀላሉ ለመሳብና ከትናንሽ ቢዝነሶች እስከ ትላልቅ ኮርፖሬሽኖች ለመመስረት እድል ይፈጥራል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ትናንት ለሕዝብ ተወካዩች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ፤ በቀጣይ ዓመት የሚጀመረው የካፒታል ገበያ ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እድገት ሚናው የጎላ መሆኑን መናገራቸው ይታወሳል፡፡

በተለይም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ባሉበት ሆነው በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች እንዲሳተፉ ሰፊ እድል እንደሚፈጥር ነው የገለጹት።

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን ከፍተኛ የሕግ አማካሪ ሰለሞን ዘውዴ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የካፒታል ገበያን በሚመለከት በአገር ውስጥ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል፡፡ በዚህም በኀብረተሰቡ ዘንድ በዘርፉ የመሳተፍ ፍላጎት መጨመሩን ተናግረዋል፡፡

ከአገር ውስጥ በተጨማሪ የውጭ ኩባንያዎች ከወዲሁ ፍላጎት ማሳየታቸውን ጠቅሰው፤ ለአብነትም በቅርቡ ኬንያ የሚገኝ አንድ ባንክ በዘርፉ ለመሳተፍ ያለውን ፍላጎት መግለጹን አንስተዋል።

በኢትዮጵያ በ2016 በጀት ዓመት ለሚጀመረው የካፒታል ገበያ የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውንም ገልጸው፣ በውጭ አገራት ከሚገኙ ተቋማት ጋር በመቀናጀት በዘርፉ አገልግሎት መስጠት የሚችሉ አካላትን በመለየት የአቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠቱንም ጠቁመዋል።

የካፒታል ገበያው በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንትና ቁጠባን ከማሳደጉ ባሻገር የዲጅታል ግብይትን በማፋጠን በኩል ሰፊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም አስታውቀዋል። ይህም አዳዲስ የስራ እድሎች እንዲፈጠሩ ያደርጋል።

በቀጣይም በመላ አገሪቱ የካፒታል ገበያውን ተደራሽ ለማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራዎችን እንደሚከናውኑ ጠቁመዋል።

All reactions:

9696

Exit mobile version