Site icon ETHIO12.COM

ሰላሳ ሚሊዮን የሚሆነው የኢትዮጵያ አምራች ኃይል በጀርባ ህመም ይሰቃያል

በኢትዮጵያ 46 በመቶ (30 ሚሊዮን) ያህሉ አምራች ኃይል ስር በሰደደ የጀርባ ሕመም ምክንያት የማምረት አቅሙ የተዳከመ እንደሆነ በዘርፉ ጥናት ያደረጉት ዓለም አቀፍ የአከርካሪ አጥንት ቀዶ ጥገና ሐኪም ዶክተር ሰይድ ዑስማን ገለጹ፡፡

ዶክተር ሰይድ ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ልዩ ቆይታ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ ከሌሎች ዓለማት የተሻለ የሰው ኃይልና ርካሽ ጉልበት ያለባት ሀገር በመሆኗ የማምረት አቅም ያለው 65 ሚሊዮን ሕዝብ አላት፡፡ ሆኖም ስር በሰደደ የጀርባ ሕመም ምክንያት ይህ አምራች ኃይል የማምረት አቅሙን 70 በመቶ አጥቷል፡፡

በዚህም 46 በመቶ ወይም 30 ሚሊዮን የሆነው አምራች ኃይል ሠርቶ እንዳይለወጥ፤ ሀገሩን በኢኮኖሚ እንዳይደግፍ ሆኗል፡፡

ስር በሰደደ የጀርባ ሕመም ምክንያት አሁን ላይ አንድ ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰው ቀዶ ሕክምና እንደሚያስፈልገው የገለጹት ዶክተር ሰይድ፤ ይህም አምራች ኃይሉን በጤና ቀውስ ውስጥ ከመክተቱም በላይ ለከፍተኛ ወጪ ዳርጎታል፡፡

ጥናቱ ባሳየው ልክ አስቦና አጢኖ መሥራት እንደሚያስፈልግ የጠቆሙት ዓለም አቀፉ የአከርካሪ ቀዶ ሐኪም ዶክተር ሰይድ፤ የአከርካሪ አጥንት ቀዶ ሕክምና አገልግሎትን በሀገሪቱ ውስጥ ማስፋፋት አምራች ኃይል ወደነበረበት ጤናማ ሕይወት ከመመለሱ ባሻገር የሀገሪቱን የሕክምና ቱሪዝም ያሳድገዋል ነው ያሉት፡፡

ከምዕራቡም ሆነ ከምስራቁ ዓለም ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው ታካሚ ስለሚበራከትም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከማሳደግ አኳያ የማይተካ ሚና እንዳለው አመልክተው፤ የመንግሥት እና የግሉ ሴክተር በሕክምና ተቋሙ እና በአገልግሎቱ ላይ ሰፊ ኢንቨስትመንት ማድረግ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡

በአከርካሪ አጥንትን ቀዶ ሕክምና በውጭ አገር ለብዙ ዓመታት የሠሩበት የሙያ ዘርፍ እንደሆነና አሁን ደግሞ ኢትዮጵያ ላይ ማዕከል ከፍተው መሥራት እንደሚፈልጉ የገለጹት ዶክተር ሰይድ፤ በሀገር ውስጥ ይህ ተግባር እውን መሆኑ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው አስገንዝበዋል፡፡

ከአሁን በፊት ወደ ሀገር ቤት በመጡበት ወቅት እንደ አለርት የመሳሰሉ ትልልቅ ሆስፒታሎች የአከርካሪ አጥንትን ቀዶ ሕክምና ሥልጠና ለዶክተሮች መስጠታቸውን አውስተው፤ አሁን በኢትዮጵያ በአከርካሪ አጥንት ቀዶ ጥገና ሕክምና አሰጣጥ ረገድ ብዙ ለውጦች ማየታቸውን ተናግረዋል፡፡

እንደ ዶክተር ሰይድ ገለጻ፤ የፈጠራ ሥራቸውን ባለፉት ሳምንታት በጤናው ዘርፍ በሳይንስ ሙዚዬም በተዘጋጀ አውደርዕይ ላይ ቀርቦ እንደነበረና ከጎብኝዎችም ጥሩ ምላሽም ያገኙበት ነው፡፡ ይህን ተከትሎ ለማቋቋም ያሰቡት ኢንስቲትዩት ለታካሚዎች ሕክምና ከመስጠቱ ጎን ለጎን የአከርካሪ አጥንት ቀዶ ሕክምና ሐኪሞች፣ የሕመም ማስታገሻ አቅራቢዎች፣ የተለያዩ ቴራፒስቶችና ነርሶች ማሰልጠኛ ማዕከል ሆኖ የሚያገለግል ነው፡፡

ኢንስቲትዩት የማቋቋም ጅምር እንቅስቃሴያቸው ጥሩ ምላሽና ተስፋ የተገኘበት መሆኑን ጠቁመው፤ አሁንም የመንግሥትንና በዘርፉ የሚሰሩ አካላትን እገዛን እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡

በጽጌረዳ ጫንያለው (ኢ.ፕ.ድ)

Exit mobile version