ETHIO12.COM

በአማራ ክልል ዝርፊያ እየተፈጸመ ነው፤ ሙስሊሞች “ተገደናል” አሉ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቶ ክርስቲያን ታደለ ” የአብይ አስተዳደር” በሚል አዲስ ስያሜ ሰጥተው አማራ ክልል ላይ የሚወሰደውን ህግ የማስከበር እርምጃ ካወገዙ በሁዋላ ” ወራሪ” በሚል ሲወገዝ የነበረውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በስም ጠርቶ ማጠልሸት እንደቀነሰ ጉዳዩን የሚከታተሉ ይገልጻሉ። ራሱን “የፋኖ ህብረት” የሚለው ታጣቂ ቡድን እንዳወጣው ተቅሶ መሳይ መኮንን ያነበበው መግለጭ ላይም የአገር መከላከያ በስሙ ተጠርቶ እንዳይተኩስ ጥሪ ቀርቦለታል። በየአቅጣጫው የተሰማውን ግጭት ተከትሎ አማራ ክልል ታጣቂዎች ዝርፊያ እየፈጸሙና ተቋማትን እያወደሙ እንደሆነ፣ ሙስሊሞችም ተገደው “የጥይት መግዣ አዋጡና አስገቡ” መባላቸው ተሰምቷል።

ቀደም ሲል “አማራ ሆይ ትግልህን አራት ኪሎ ላይ ብቻ አነጣጥረህ ታገል። ያን ጊዜ ሰላም ታገኛለህ። ያን ጊዜ እጅግ አነሰ ቢባል ሳትጠየቅ ምላሽ ታገኛለህ። ከፍ ሲል ጠያቂ አትሆንም” ሲሉ የትግሉንና የትግሉን አቅጣጫ ያመላከቱት አቶ ክርስቲያን፣ በተለያዩ ወቅቶች እንቅስቃሴዎች የሚመሩበትን አቅጣጫ እንደሚሰጡና ኮድ እንደሚያኖሩ የገለጹ፣ አሁንም መከላከያን መስደብና ማጠልሸት አዋጪ ሆኖ ባለመገኘቱ ዘመቻው ” የአብይ አስተዳደር” በሚል የፕሮፓጋንዳ ቅጭት እንዲመራ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን የሚከታተሏቸው አመልክተዋል።

ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች እጅግ ነቅተውና ራሳቸውን አዘጋጅተው እንዲጠባበቁ የሚያደርግ መልዕክት በማሰራጨት የሚታወቁት አቶ ክርስቲያን ” ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን ስልታን ልቀቁ” በሚል ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ መጠየቃቸውን ተከትሎ ” ጥያቄያቸውን በኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ስም ሁሉ ከሚያደርጉት በወከላቸው የቋሪት ህዝብ ወይም በፓርቲያቸው ቁመና ልክ ቢያደርጉት” በሚል በጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋፊዎች ይተቻሉ።

“የዐቢይ አሕመድ አስተዳደር በአማራ ሕዝብ ላይ እየፈፀመ ያለውን ወረራና የንፁኃን ግድያ በአስቸኳይ እንዲያቆም እያሳሰብሁ፤ የሰብአዊ መብት ተቋማት፣ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ እንዲሁም ሚዲያዎች መንግስት የቴሌኮም አገልግሎቶችን በመዝጋት ጭምር በአማራ ክልል በከባድ መሣሪያ ታግዞ በንፁኃን ዜጎች ላይ እየፈፀመ ያለውን ጭፍጨፋ እንድታወግዙና አገዛዙ ላይ ጫና እንድታሳድሩ ጥሪዬን አቀርባለሁ።” ሲሉ ጥሪ ያሳለፉት አቶ ክርስቲያን በክልሉ እየተፈጸመ ያለውን የንብረት ውድመት፣ የመሰረታዊ እንቅስቃሴ መገደብ፣ የመንግስት ተቋማት ዝርፊያን እንደ ህዝብ ተወካይነታቸው አላወገዙም። የሰላም ጥሪም አላቀረቡም።

ከተለያዩ አካባቢዎች የሚወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በጎጃም ብቸናና ደብረማርቆስ የመንግስት ንብረት ወድሟል። ተዘርፏል። በተለያዩ አካባቢዎችም በተመሳሳይ ዝርፊያ እየተፈጸመ መሆኑንን ነዋሪዎች እያመለከቱ ነው። ከሁሉም በላይ አሳሳቢ የሆነው የሙስሊም እመነት መሪዎችን በማስገደድ “የጥይት መግዣ ብር አዋጡ” የመባሉ ዜና ነው።

እንቅስቃሴው ላይ ከእመነት ጋር በተያያዘ ጥያቄ ያላቸው ሙስሊም ወገኖች በሚደርስባቸው አስገዳጅ መመሪያ በፍርሃቻ ቢተባበሩም አካሄዱ ስጋት ላይ እንደጣላቸውና ” አንድ አገር፣ አንድ እምነት” የሚለው መፈክር የሚያሰሙ ብቻ የሚመሩት ይህ እንቅስቃሴ ውሎ አድሮ መልኩን እንዳይቀይር መምከር መጀመራቸውንና በሰላማዊ ክልሎች ለሚኖሩ ጉዳዩን በንቃት እንዲከታተሉ እያሳወቁ መሆኑ ተመልክቷል።

ዋሱ የሚባለው የቴሌግራም ገጽ ላይ ስጋት የገባቸው እንደላኩት ገልጾ የቀረበው ማስረጃ ” … ያሳዝናል። ዕምነትና ፖለቲካ የተቀላቀለበት ጉዳይ ነው” የሚል ስጋት ቀርቦበታል። ሃይማኖት ሲል የትኛው እንደሆነ ይፋ ባይደረግም በኦርቶዶክስ ስም የሚደረገውንና እየተደረገ ያለውን እምነቱ ላይ የተተከለ ቅስቀሳ እንደሆነ ያመልክታል።

ይህ በንዲህ እንዳለ ዝርፊያ ያበሳጫቸው ወገኖች ምላሽ የሰጡባቸው አካባቢዎች መኖራቸው ተመልክቷል። በአንዳንድ አካባቢዎች ህዝብ ራሱን መከላከል መጀመሩም ተሰምቷል። በአማራ ክልል ዘርፈና ህገወጥነት እንዳይስፋፋ ክልሉን የሚመሩት ዶክተር ከፍ ያለ ማስታወቃቸውና መማጽናቸው ይታውሳል።

በአማራ ክልል በአብዛኛው ኢንተርኔትና የመብራት እንዲሁም በከፊል የስልክ አገልግሎት የተቋረጠ መሆኑ ታውቋል። መከላከያም ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ እርምጃ እየወሰደ መሆኑ ተሰምቷል። አንዳንድ አካባቢዎች የነበሩ ግጭቶች መክሰማቸውና መቀዛቀዛቸው ታውቋል።

ይህ ሁሉ ሃይል የት ሰልጥኖ፣ ማን አስታጥቆት፣ እንዴትና ማን ስልት ነድፎለት በአንድ ጊዜ በተለያዩ አቅጣጫዎች ጥቃት ለመክፈት ቻለ የሚለው ጉዳይ በስፋት እያነጋገረና ችግሩ ከስሩ ሊቀርፍ እንደሚገባ አቋም እንዲያዝበት እያስገደደ መሆኑ ተሰምቷል። ኢትዮጵያ ላይ ችግር የሚጠምቀውን ክፍል ማስወገድ ካልተቻለ ኢትዮጵያ ሰላም ልታገኝ ስለማትችል ይህን ቀውስ ተከትሎ በቀጣዩ የመንግስት አቋም ምን ሊሆን እንደሚችል በርካቶች በጉጉት የሚጠብቁት ጉዳይ ነው።

ይህ እስከታተመ ድረስ በወልቃይት፣ ጠገዴና ሁመራ አካባቢ ፍጹም ሰላም መሆኑ መረጃው ያላቸው አስታወቀዋል።

Exit mobile version