ያላገገመው አማራ ክልል ዳግም ጦርነት፤ የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ ተጠየቀ፤ ” ሁሉንም እንዳናጣ” ደመቀ መኮንን

” … በሶስተኛ ቀን የባለቤቴን አስከሬን ላነሳ ተፈቅዶልኝ ስሄድ ጉንዳን ወሮት …. እያለቀሱ ” ይህ ተሰምቷል። የተናገሩት ሚስት ናቸው። በሰላም በተቀመጡበት በቤታቸው ሙሉ ቤተስባቸውን ተነጠቀው ብቻቸውን የቀሩት አዛውንት ” እንዴት ልሁነው? ” እያሉ ሃዘን እየናጣቸውና ቁጭት እንደ ረመጥ አንጀታቸውን እየላጠው የሆኑትን ሲናገሩ ስምተናል። አይተናቸዋል። በየሰፈሩ አስከሬን ተቀብሯል። መኖሪያ ቤት ውስጥ ቀብር ተፈጽሟል። የጅምላ ጭፍጨፋ ተፈጽሟል። በጋሸና አስከሬን በድብረብርሃን ልብስ ተጠቅልሎ በየሜዳው ቤተስብ እያነባ አይተናል። ይህን ሁሉ ያደረገው በስም የሚታወቅ ወራሪ ሃይል ነው። እንዲህ ያለው ተግባር የትም ስፍራ፣ በማንኛወም የህብረተሰብ ክፍል ላይ ሊሆን የማይገባ ሃፍረት ነው። አሳፍሪ ብቻ ሳይሆን አውሬነት ነው። ይህ የትናንት ጠባሳ ተረሳ

ሸዋ ሮቢት የሰማኒያ ዓመት መነኩሴ በቡጢ ተመቱና ወደቁ ከዛ ተደፈሩ ” ረክሼ አልኖርም” ብለው ራሳቸውን አጠፉ። ” ከእነዚህ ሴቶች መካከል አስሩ አሁንም ህክምና እየተከታተሉ መሆናቸውንና ከእነዚህ ውስጥም የ80 ዓመት አዛውንት ሴት እንደሚገኙ አመልክተዋል። ይህን ጊዜ ዘገባው የናዳ ያህል ለልቡና ውርጂብኝ ሆነ። ዘጋቢዋ አቅፋ ስማቸው ሪፖርቷን ስታቀርብ አይኗ ላይ የሚነበበው ሃዘን እንዴት አድራጊ ወገኖች ላይ ቅንታጥ ያህል ሊፈጠር አልቻለም? ምን አይነት የጥላቻ ስብከት? ምን ያህል አጥንት የዘለቀ የክፋትና የጭካኔ ትምሀርት ይሆን የ80 ዓመት እድሜ ባለጸጋ ላይ ዘሎ ጉብ የሚያስብል? ምን የሚሉት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ኪኒን ይሆን እንዲህ ልቡናና ህሊናን የሰለበው? ይህን ትውልድስ እንዴት ወደፊት ማረቅ ይቻላል?” ይህም ተረሳ

አማራ ክልል ምን ያልሆነ፣ ያልተሰማ፣ ያልተፈጸመ አለ። የሚሰማው፣ የሚታየው ሁሉ መፈጠርን የሚፈታተን ነበር። ወልቃይት ተገዴ፣ ጠለምት፣ ራያ… ከተፋው ህይወት፣ ከተሰደዱት በላይ እዛው እየኖሩ አማርኛ እንዳይተነፍሱ፣ እስክስታ እንዳይወርዱ፣ አማርና እንዳይዘፍኑ፣ ባንዲራቸውን እንዳይዙ… በቋንቋቸው እንዳይማሩ የተፈረደባቸው ዜጎች ነጻ ወጥተው እስኪናገሩ ይህ ሁሉ ኢትዮጵያ ምድር ላይ በወገን ይፈጸማል ብሎ ማን አስብ ያውቃል። ያ ሁል አፈና የተሰበረው እንዴት ነው? የመከላከያ ውለታ “ወራሪ፣ የጋላ ጦር” የሚል? ታሪክ ይፈርዳል የሚሉ ብዙ ናቸው። ለዚህ ነው በርካቶች አሁን ሻለቃ ዳዊት የሚመሩት ንቅናቄ ዓላማውና ቁልፍ ተግባሩ መከላከያን ማፍረስ የሆነበትን ምክንያት አጉልተው የሚያሳዩት። የሚያስጠነቅቁት። በተለይ ሻለቃ ዳዊት ማንነታቸው፣ ምንነታቸውና ያላቸው የባንዳነት ስረ መሰረት ስለሚታወቅ አካሄዱ ሁሉ ፍንትው ብሎ እንደሚታይ የሚያመላክቱት።

በአማራ ክልል ያጋጠመውን የፀጥታ መደፍረስ በመደበኛ የህግ ማስከበር ስርአት ለመቆጣጠር አዳጋች ሆኖ በመገኘቱ የፌደራል መንግስት አስፈላጊውን የህግ ማዕቀፍ እንዲተገብር የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ህገመንግስቱን ጠቅሶ ጥያቄ አቀረበ። ለአገር መከላከያና የጸጥታ ተቋማት መመሪያ መሰጠቱ ታውቋል። ደመቀ መኮንን ” የዚህ መጨረሻ በግራም በቀኝም ከውጭም ከውስጥም ላሰፈሰፉ ኃይሎች ሰርግና ምላሽ ሆኖ አቅም የሚያሳጣ፣ ክብራችንን የሚጎዳ፣ ተጋላጭነታችንን የሚያሰፋ በአጠቃላይ ሁሉንም የሚያሳጣ እንዳይሆን ያሰጋል” ሲሉ ሰላም እንደሚሻል የሚያሳስብ አሳብ አሰራጭተዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ከቀም ሲል “ሁሉም ነፍጥ ያነሳ አካል ነፍጡን አውርዶ ለሰላማዊ ንግግር ፈቃደኛ ይሁን” ሲሉ ተማጽነው ነበር። ከአንድ ምንጭ የማይወጣውና ከየአቅጣጫው በማህበራዊ ” ጥሪው ጊዜ ያለፈበት ነው” ያልፈበት እንደሆነ ሲገለጽ ውሎ አድሯል። “መከላከያ ከአማራ ክልል ለቆ ይውጣ” የሚለው ጥያቄ ዓላማውና ምንነቱ ያልገባቸው ወገኖች በበኩላቸው ” ምን እየሆነ ነው” በሚል እየጠቁ ባለበት ሰዓት በአንዳንድ አካባቢዎች ግጭት መቀሰቀሱ ተሰምቷል።

See also  "ደሴ እንገናኝ" አቶ ጌታቸው፤ ሰቆጣ ነጻ ወጣ

በአንዳንድ የማህበራዊ ገጾች ” ፋኖ አይሸነፍም” የሚሉ ድምጾች ትግሉ በድል ታጅቦ በርካታ ከተሞችን ነጻ ማውጣታቸውን እያስታወቀ ባለበት ሰዓት ክልሉ ባደረገው ህጋዊ ጥሪ መሰረት መከላከያ የህግ ማስከበር ስራ የተባለውን ዘመቻ በይፋ ጀምሯል። መከላከያ እንቅስቃሴ ከጀመረ በሁዋላ በይፋ የተገለጸ ሪፖርት ባይኖርም ” ኢንተርኔት ይከፈት፣ ስልክ ይለቀቅ፣ መከላከያ የሚወስዳቸው ርምጃዎች በቪዲዮ ይቀረጹ፣ የፋኖ ሃይል የሚወስደውን እርምጃና ድል በቪዲዮ አታሰራጩ፣ ቴሌ ብር አትጠቀሙ …” የሚሉ የትግል አቅጣጫዎች በስፋት በማህበራዊ ገጾችና “የትግሉ አካል ነን” በሚሉ አካላት እየተላለፈ ነው።

“በአማራ ክልል ያጋጠመውን የፀጥታ መደፍረስ በመደበኛ የህግ ማስከበር ስርአት ለመቆጣጠር አዳጋች ሆኖ በመገኘቱ የፌደራል መንግስት አስፈላጊውን የህግ ማዕቀፍ እንዲተገብር የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጥያቄ ያቀርባል” የሚለውና በክልሉ መሪ ፊርማ ወጪ የሆነው ደብዳቤ መከላከያ ” ለሁሉም ልክ አለው” በሚል ወዳጅ ዘመድ እንዲመክር ካስጠነቀቀ በሁዋላ ነው።

በአማራ ክልል የተከሰተው የሰላም መደፍረስ በክልሉ ከፍተኛ ሰብአዊ፤ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እያደረሰ መሆኑን የክልሉ መንግስት በደብዳቤ ቢያስታውቅም መጠኑንን አላስታወቀም።

አማራ ክልል በተለያዩ ጊዜያት መንገድ መዝጋትና ማህበራዊ አገልግሎቶችን ማስተጓጎል የተለመደና ምክንያት የማይቀርብለት የክልሉን ሕዝብ የሚጎዳ ተጋባር እንደሆነ ነዋሪዎች በየጊዜው ሲገልጹ ነበር። “የአማራ መብት ተጣሰ ለሚል ጥያቄና ትግል፣ ሰዎች በነጻነት ወደ ደሴ ወይም ጎንደር እንዳይጓዙ ማገድ፣ የንግድ ፍሰትን ማስተጓጎል ፖለቲካዊ ፋይዳውን ደፍሮ የሚያስረዳ አካል ማን ነው? ድርጊቱን የሚፈጽሙስ ትዕዛዝ የሚሰጣቸውን አካል ያውቁታል?” የሚል ጥያቄም የሚያነሱ አሉ።

የተከሰተውን የፀጥታ ችግር በቁጥጥር ስር ለማዋል እስካሁን በክልሉና በፌደራል የፀጥታ ሃይሎች በኩል በርካታ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸው ያስታወሰው የዶክተር ይልቃል ደብዳቤ ” በክልሉ ያለው የፀጥታ መደፍረስና ጥቃት በንፁሃን ዜጎች ላይ እያደረሰ ያለውን ጉዳት በአስቸኳይ ለማስቆም የፌደራል መንግስት ከመደበኛው የህግ ማስከበር ስርአት ባሻገር በኢፌዴሪ ህገ መንግስት መሰረት አስፈላጊውን የህግ ማዕቀፍ በአፋጣኝ እንዲተገበር ነው የአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ይጠይቃል” ማለታቸውን ተከትሎ ” ጠቅላይ ሚኒስትር አብይን በጄኖሳይድ እንከሳለን” የሚሉ ማስታወቂያዎች በማህበራዊ ሚዲያዎች ልክ ትህነግ ሲመታ እንዳደረገው በተመሳሳይ መሰራጨት ጀምሯል።

ክልሉ ወደ ቀደመ መረጋጋቱ እንዲመለስ ዜጎች ሰላማቸው ተመልሶ አርሶአደሩ ወደ እርሻው ክልሉም ወደ ልማት ስራዎች ፊቱን እንዲያዞር ለማድረግ መንግስት ያለበትን ሃላፊነት በአግባቡ ሊወጣ ይገባልም በሚል የፌደራል መንግስትን ከማሳሰቢያ ጭምር እርምጃ እንዲወስድ የጠየቀው ደብዳቤ ተከትሎ በላሊበላ ደሴና ጎንደር የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ማቆሙ ታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ” አማራ ያገኘውን እንዳያጣ” ሲሉ ማስጠንቀቂያ መልዕክት አስተላለፈዋል። እንደሚከተለው ይነበባል።

በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚታዩ የፀጥታ ችግሮች አሳሳቢ እየሆኑ መጥተዋል::

በመሰረቱ ብዙ ምላሽ ያላገኙ ጥያቄዎች ይኖራሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ግን ጠቃሚው መንገድ ሰላማዊና የውይይት አግባብ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ ያለው አካሄድ

See also  «ቃል ማክበር ካለ የድል ብሥራት አለ» አብይ አህመድ የድል ብስራት ፍንጭ ሰጡ

1. የጥያቄዎችን መፍቻ መንገድ የሚያደናቅፍ

2. ያለንን የሚያሳጣ

3. በዘላቂነት ሊታዩ ይገባቸዋል የምንላቸውን ጉዳዮች እንዳይፈቱ የሚያወሳስብ አካሄድ ነው፡፡

‘ሰላም ከሌለህ ሁሉን ታጣለህ’ የሚባለውን እውነታ ከልብ በማጤን በአስተውሎት መጓዝ በሚገባን ታሪካዊ ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡

በየዘመኑ ብዙ ፈተናዎች እና ችግሮች ሲገጥሙ በጥበብ ተሻግረው ያሻገሩንን የአባቶቻችን ጥበብና አስተውሎት ማጥበቅ ይጠይቃል፡፡ የሀገር ሽማግሌ የጠፋበት፣ ታላቅ የሌለበት፣ መካሪ የሃይማኖት አባት የታጣበት ይመስል ሁላችንንም የሚያባላና የሚበላ አካሄድ ይስተዋላል፡፡

የዚህ መጨረሻ በግራም በቀኝም ከውጭም ከውስጥም ላሰፈሰፉ ኃይሎች ሰርግና ምላሽ ሆኖ አቅም የሚያሳጣ፣ ክብራችንን የሚጎዳ፣ ተጋላጭነታችንን የሚያሰፋ በአጠቃላይ ሁሉንም የሚያሳጣ እንዳይሆን ያሰጋል፡፡

ከለውጡ ብዙ የጠበቅናቸው ግን ደግሞ ምላሽ ያላገኘንባቸው ያላረኩንና ሌሎች ችግሮችና ስሜቶች ይኖራሉ፡፡

ለእነዚህ ጉዳዮች ቆም ብለን በማሰብ በሰላሙ መንገድ ዘላቂ መፍተሄ እንዲያገኙ ማድረግ ተገቢ ነው፡፡ ለዚህም የሁሉም ዋስትና የሆነውን ህግና ሥርዓት በተሟላ መልኩ ማክበርና ማስከበር ይገባል፡፡

በሌላ በኩል የቋሪት ጎጃም ህዝብ ወኪል የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ “የዐቢይ አሕመድ አስተዳደር በአማራ ሕዝብ ላይ እየፈፀመ ያለውን ወረራና የንፁኃን ግድያ በአስቸኳይ እንዲያቆም እያሳሰብሁ፤ የሰብአዊ መብት ተቋማት፣ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ እንዲሁም ሚዲያዎች መንግስት የቴሌኮም አገልግሎቶችን በመዝጋት ጭምር በአማራ ክልል በከባድ መሣሪያ ታግዞ በንፁኃን ዜጎች ላይ እየፈፀመ ያለውን ጭፍጨፋ እንድታወግዙና አገዛዙ ላይ ጫና እንድታሳድሩ ጥሪዬን አቀርባለሁ።” ሲሉ በግል የፌስ ቡክ ገጻቸው ጽፈዋል። አቶ ክርስቲያን እስክንድር ነጋ በይፋ “ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ ይመሩታል ” ሲል ይፋ ያደረገው ንቅናቄ እያደረሰ ያለውን ጉዳትና የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ የተከፈተውን የስም ማጥፋት ዘመቻ ” የአብይ መንግስት አስተዳደር በአማራ ህዝብ ላይ ወረራ ፈጸመ” በሚል ስም ቀይረው በማቅረብ በይፋ ድጋፍ ሰጥተዋል። ቀደም ሲል አቶ ዮሐንስ ቧለው መከላከያ ከአማራ ክልል ሊወጣ ይገባል ሲሉ በይፋ እንደ ወራሪና አተራማሽ ሃይል ቆጥረውት መቃወማቸው የሚታወስ ነው።

” ከዚያስ” የሚሉ ታዛቢ ወገኖች፣ አሁን ጠብመንጃ ያነሳው የሻለቃ ዳዊት ሃይል አማራ ክልልን ቢቆጣጠር በቀጣይ አላማው ምን እንደሆነ የማይገባቸው ” በሁዋላ ከምንደናበር አላማችሁን አስቀድማችሁ፣ ጥያቄያችሁንና ፍላጎታችሁን ነገሩን” በሚል ጥያቄ ያነሳሉ። አያይዘውም ” ሻለቃ ዳዊት በይፋ የአማራ ድንበር ወለጋ ነው” ያሉትን በማስታወስ፣ እስክንድር ነጋ ” አስቀድመን አማራ፣ ቀጥሎ ወደ ኢትዮጵያ” ያለውን በማንሳት ይፋዊ ማብራሪያ ይጠይቃሉ።

” የኦሮሞ፣ የጋላ ሰራዊት በሚል ስሙን እያሳነሱ የሚጠሩትን ሃይል በቀላሉ መበተንና ልክ ትህነግ እንዳደረገው ሜዳ ላይ መጣል ይቻላል?” በሚል ጥያቄ የሚያነሱ፣ ይህ ግጭት እየከረረ ከሄድ ምን ሊፈጠር እንደሚችል መረዳት አግባብ እንደሆነ ይጠቁማሉ። የአማራ ህዝብ በተለይም የወልቃይትና ጠገዴ ራያ … ህዝብ የተነፈሰውን የሰላም አየር በድንብርብርና ውርጋጥ አካሄድ በኪሳራ እንዳያባዙት አበክረው የሚገልጹ ” አማራ ክልል ሲወረር ከየአቅጣጫው ዘር ሳይመርጡ ድምና አጥንታቸውን የከፈሉ የኢትዮጵያን ልጆች ወራሪ አድርጎ ማቆሸሽ ለአማራ ህዝብ የማይረሳ የታሪክ ጠባሳ ከማውረስ የዘለለ ትርጉምና ፋይዳ አይኖረውም” ሲሉ ያስጠነቅቃሉ። እነዚህ ወገኖች ” መከላከያ ሙሉ አማራ ክልልን ለቆ ቢወጣ ምን ሊሆን እንደሚችል ለመረዳት ተመራማሪ መሆን አይጠይቅም። እባካችሁን የአማራ ልሂቃን ይህን ጉዳይ እናስብበትና እናምክን” ሲሉ የቀድመውን የኦሮማራ እንቅስቃሴ ማደሱ እንደሚቀል፣ ችግሮችንም በውይይት ለመፍታት መሞከር እንደሚሻል ይመክራሉ።

Leave a Reply