ETHIO12.COM

የትግራይ ክልል የአማራ ክልልን አለመረጋጋት ተንተርሶ ፍላጎቱን ይፋ አደረገ፤”መከላከያ ከአማራ ክልል ይውጣ” የማን አጀንዳ?

“አማራ ክልል እንዳይረጋጋና ጥያቄዎቹን በአግባቡ ተደራጅቶ እንዳያቀርብ የሚነዱት የውክልና ጦርነት አራማጆች መሆናቸው አሁን ላይ በግልጽ እየታየ ነው “

የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር በአማራ ክልል የተቀሰቀሰውን ጦርነትና አለመረጋጋት ተከትሎ ሁሉም ወገን ከመከላከያ ጋር እንዲያብር ጥሪ አቀረበ። የትግራይ ክልል ከጦርነቱ በፊት ወደነበረበት ይዞታ ለመመለስ ያለውን ምኞትም በይፋ በመግለጫው አመክቷል። ይህንኑ መግለጫ ተከትሎ የአማራ ህዝብ ወኪልና ተቆርቋሪ ነን የሚሉ ” መከላከያ ከአማራ ክልል ይውጣ የሚሉበት ምክንያት ግልጽ ሆነ” ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች አመልክተዋል።

መንግስት ያወጀውን አስቸኳይ አዋጅ ተከትሎ ክልሎች በሙሉ የፌደራል መንግስትን አቋም በመደገፍና የአገር መከላከያን መተንኮስን “ቀይ መስመር ነው፤ ቀልድ የለም” የሚል መግለጫ ሲያወጡ ዝምታን መርጦ የነበረው የትግራይ ክልል፣ አማራ ክልል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ፍጹም የማይሳካ፣ የጽንፈኞች ስብስብ ዋጋ ቢስ ሩጫ እንደሆነ ጠቅሶ ዛሬ መግለጫ አሰራጭቷል።

ትህነግ በመላው ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ፣ በመከላከያና አጋር አደረጃጀቶች ፋኖን ጨምሮ ባሳደሩበት ዱላ ሲሸነፍ በአጋሮቹ ድጋፍ ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ የሰላም ስምምነት መፈረሙ አይዘነጋም።

ፕሪቶሪያ ላይ በተደረገው “የሰላም አማራጭ” የተባለ ስምምነት መሰረት የተረፈው ትህነግ ዛሬ ባወጣው መግለጫ ራሱን የሰላም አባትና የሰላም አራማጅ አድርጓል። በወረራ አፋርና አማራ ክልልን ይዞ መንግስት ሊንድ የዘመተው ትህነግ ” ጽንፈኞች” ያላቸውን ሃይሎች ” የፕሪቶሪያ ስምምነት የትግራይን ህዝብ ለማጥፋት የነበራቸውን ዕቅድ የዘጋባቸው” ሲል ወቅሷል። በተለያዩ አክቲቪስቶችና የዩቲዩብ አውዶች “የትግራይ ህዝብ ላይ ዘመቻ ከፍተዋል” ሲሉም አመልክቷል።

በተያያዘው መግለጫ እንደተመለከተው የትግራይ ክልል ራሱ ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሁሉ መተባበር እንዳለባቸው ጥሪ አድርጎ እንዳቀረበው ከሆነ ” ጽንፈኛ” ሲል የጠራው ቡድን የህዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን እያበላሸ እንደሆነ አመልክቶ ኮንኗል። የመከላከያን እርምጃ እንደሚደግፍ አመልክቷል። ቀደ ሲል ልክ ዛሬ እንደሚባለው “የአብይ ጦር” እያለ የሚጠራውን የኢትዮጵያ ህዝብ አለኝታ አክብሮ ድጋፍ እንደሚያደርግ የገለጸው የትግራይ ክልል ቁጥርና አንቀጽ ሳይጠቅስ የፕሪቶሪያው ስምምነት እንዳይተገበር የሚደረግ ማናቸውም ቀውስ በተሸናፊነት እንደሚጠናቀቅ አመልክቷል።

ትህነግ ቀደም ሲል ከአማራ ክልል በጉልበት የወሰዳቸውን አካባቢዎች በጦርነት ተሸንፎ መልቀቁ ይታወሳል። ይህንኑ በሃይል ወስዶ በህግ አስደግፎ የራሱ አድርጎታል የተባለውንና የሚከሰሰበትን የአማራ ክልል መሬት መልሶ ለመጠቅለል፣ ክልሉ እንዳይረጋጋ በተዘዋዋሪ ወይም በውክልና ትህነግ እንደሚነቀሳቀስ መረጃ ጠቅሰው የሚናገሩና የሚመክሩ በርካታ መሆናቸውም አይዘነጋም።

በቅርቡ እንኳ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮን ” የይዛነውን እንዳያሳጣን” ሲሉ የጦርነቱን ወላፈን ለሚያጋግሙ እርጋታ እንደሚሻል መክረው ማስጠንቀቂያ ማስታወሻ በማህበራዊ ገጻቸው ማካፈላቸው አይዘነጋም።

የህን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር መግለጫ ያዩ ” መከላከያ ከአማራ ክልል ይውጣ የሚሉት ክፍሎች የማን ወኪልና ዓላማ አራማጆች እንደሆኑ የሚመሰክር ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። “አማራ ክልል እንዳይረጋጋና ጥያቄዎቹን በአግባቡ ተደራጅቶ እንዳያቀርብ የሚነዱት የውክልና ጦርነት አራማጆች መሆናቸው አሁን ላይ በግልጽ እየታየ ነው ” ያሉ ወገኖች ህዝብ፣ ልሂቃን፣ ይመለከተናል የሚሉ፣ እዛና እዚህ እየረገጡ ህዝቡን መዥጉርጉር ትግል የሚያጨርሱና ሃብታቸውን የሚገፈግፉ ሊያስቡበት ይገባል” ብለዋል።

አሁን ላይ የአማራ ክልልን ውስጥ እየተካሄደ ያለውንና ወጥ መርህ እንደሌለው፣ አንዳንድ ቦታዎች ላይ ዝርፊያና ንብረት ማውደም ላይ የተሰማራ እንቅስቃሴ እንደሚመሩ የሚገልጹና በማህበራዊ ሚዲያዎች መከላከያ ላይ ዘመቻ የከፈቱ ሃይሎች ቀደም ሲል ትህነግ እንዲመታ የአገር መከላከያን ልብስ ለብሰው ጦር ሜዳ ሳይቀር ሲቀሰቅሱ የነበሩት ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጥቅም እንደሆነ በበርካታ መረጃ ዜናዎች እየወጡ ነው።

የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ሰራዊት የፐሬዚዳንት ኢሳያስ ዋንኛ ስጋት በመሆኑ፣ መከላከያን በክህደት አርዶ በገባበት ጦርነት ሻዕቢያ ትህነግን የመብላት ዕድል እንደተመቻቸለት የሚገልጹ፣ በግንቦት ሰባት፣ በአርበኞች ግንባርና በሚዲያ ስም አስመራ ሲመላለሱ የነበሩ ወገኖች ሙሉ በሙሉ ጦርነቱን በመደገፍ ከመከላከያ ጋር የቆሙት በፕሬዚዳንት ኢሳያስ በኩል ካለ የግንኙነት መስመር እንደሆነ አሁን ላይ በስፋት ይገለጻል።

አንዳንዶቹ በሚገርም እጥፋት ትህነግ ተሸንፎ የሰላም ስምምነት ሲባል የማጥላላቱን ዘመቻ የገፉበት መከላከያ ሲጠናከር፣ በተለይም የባህር ሃይሉና የአየር ሃይሉ ግዙፍ መሆን ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ ስጋት ስለሆነባቸው እንደሆን እየተጠቆመ ነው። ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ እንደሚሉት እነዚህ ወገኖች ለመከላከያ በጮሁበት አንደበታቸው ሳይውል ሳያድር ” መከላከያ ወራሪ ነው፣ አሸባሪ ነው፣ ከአማራ ክልል ይውጣ” በሚል ዘመቻ የጀመሩት ቀደም ሲል በሻዕቢያ መሪነት “የደርግ” ተብሎ እንደፈረሰው የአገር መከላከያ አሁንም ፈርጆ ለማፍረስ በተሰጣቸው የቤት ስራ ነው።

ከዛም ከፍ ሲሉ ትህነግ ዓላማውን እንዲያስፈጽም በሁለት ማንነት የሚጫወቱ” በገፊና ጎታች ፖለቲካ” አማራ ክልልን ውልና ወጥ መዋቅር በለሌላው አመጽ ለማተራመ ሃላፊነት የወሰዱ እንዳሉበት የሚገልጹ ጥቂት አይደሉም።

አማራ ተፈርጆ ቢዘርዝሩት የማያልቅ በደል እንደደረሰበት፣ እንደተገደለና እንደተፈናቀለ ማንም ሊክደው እንደማይችል የሚናገሩት እነዚህ ወገኖች፣ አማራ ክልል ተረጋግቶ በሰከነና በተደራጀ መልኩ እጁ ላይ ያለውን ሳያጣ በጥበብ የሚያታግሉ መሪዎች እንደሚያስፈልጉት ይጠቁማሉ። አያይዘውም “ይህ ሳይሆን ቀርቶ ንብረት በማውደም፣ ባልተጠና ምሪት፣ ዝርፊያ ላይ በማተኮር የሚደረግና ህዝብን ለጎስቁልና የሚዳርግ ትግል ላደፈጡ የውስጥ ሃይሎች፣ በውጭ ላሉ ታሪካዊ ጠላቶችና በስጋት ሊያፈርሱን ለሚያሴሩ ወጥመድ በመመቸት ማለቂያ የሌለው ትርምስ ውስጥ አንወድቃለ” ሲሉ ያስጠነቀቃሉ። የትግራይ ክልልን መግለጫ በማንበብና “መከላከያ ከአማራ ክልል ይውጣ፣ የአብይ ጦር፣ የኦሮሞ ጦር…” የሚሉ ወገኖችም የቅርብ ሩቅ ጠላት አጀንዳ ተሸካሚ መሆናቸውን መረዳት አግባብ እንደሆነ ያመለክታሉ።

ይህ በንዲህ እንዳለ ነገ ለፓርላማ የሚቀርበውን የአስቸኳ ጊዜ አዋጅ አስመልክቶ የፓርላማ አባላት ውድቅ እንዲያደርት በግል ስልክ እየተደወለና ስማቸው እየተጠራ ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው መሆኑ ተሰማ። በተለያዩ የማህበራዊ ገጾች እንደታየው የፓርላማ አባላቱ አስቸኳይ አዋጁ እንዳይጸድቅ የፓርላማ አባላቱ እንዲቃወሙት በስምና በአድራሻ እየተጠቀሱ ማስጠንቀቂያ እየደረሳቸው ነው።

አማራ ክልል ላይ የታወጀውን የአስቸኳይ አዋጅ አስመልክቶ ኮማንድ ፖስቱ የሰዎችን መብት እንዳይጥስ፣ ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወስድ የሚጠይቁ ተቋማትና ግለሰቦች አሉ። በተቃራኒ ደግሞ በአማራ ክልል የታየው ቀውስና ስርዓት አልበኛነት ያሳሰባቸው አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ረዥም ጊዘ ባይቆይም፣ ለጊዜው ግን ህግና መብት ባከበረ መልኩ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ረብሻ ያሰላቻቸው ጥቂት አይደሉም።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ ላይ ባለ ጊዜ የታወጀ ከሆነ በ48 ሰዓታት ውስጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚቀርብ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሁለት ሦስተኛ ድምፅ ተቀባይነት ካላገኘ ወዲያውኑ እንደሚሻር የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 ንዑስ አንቀጽ ሁለት (ሀ) ይደነግጋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሥራ ላይ ባልሆነበት ወቅት የታወጀ እንደሆነ በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቅረብ እንዳለበት፣ የምክር ቤቱን ሁለት ሦስተኛ ድምፅ ተቀባይነት ካላገኘም ወዲያውኑ እንደሚሻር የሕገ መንግሥቱ ቀጣይ አንቀጽ ይደነግጋል። ምክር ቤቱ 547 መቀመጫዎች ቢኖሩትም በተለያዩ ምክንያቶች ምርጫ ተሟልቶ ባለመካሄዱ 427 መቀመጫዎች ብቻ አሉት። አዋጁን ለማጽደቅ 285 ወይም በቂ ነው። ኢዜማ፣ አብንና ሌሎች የግል በትቅሉ ዘጠኝ የሚሆኑ ተመራጮችን ከአማራ ብልጽግና 125 ወንበር ጋር በመድመር 142 ድምጽ በተቃውሞ ከተመዘገበ የአስቸኳይ አዋጁ ሊሰረዝ እንደሚችል ፍላጎት አሳይተው የሪፖርተርን ስሌት ያሰራጩም ጥቂት አይደሉም።

ሪፖርተር ሂሳቡን አስልቶ ሲያበቃ “የሁለት ሦስተኛ ድምፅ ሥሌቱ ከላይ የምክር ቤቱን ጠቅላላ አባላት መሠረት በማድረግ ከተገለጸው ውጤት ያነሰ የድጋፍ እና ተቃውሞ ድምፅ የመከሰት ዕድሉ ሰፊ ነው” ሲሉ የግምት አቅጣጫ አመላክቷል።

ምንም እንኳን አምራ ብልጽግና 125 ወኪሎች ቢኖሩትም ሙሉ በሙሉ አስቸኳይ አዋጁ እንዲነሳ እንደሚፈልጉ በትንተናው ውስጥ የቀረበ ነገር የለም። ይህን ትንተና ያዩ እንደሚሉት ሁሉም ቢቃወሙ እንኳ ድጋፍ ማግነቱ እነደማይቀር ጠቁመው ” አማራ ክልል እረፍት እንዲያገኝ የሚፈልጉ የፓርልማ አባላት እንዳሉ ሊታወቅ ይገባል” ይላሉ። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዲነሳ የሚፈልጉ ትጥቅ ያልያዙና ውጊያ ያልገቡ ሃይሎች አላማቸውና ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ ግን በይፋ አላስቀመጡም።


Exit mobile version