ኢትዮጵያን እያመሳት ያለው የ”ገፊና ጎታች ሤራ” ሲገለጥ

እዚህ ላይ ከጎጃም በሚዋሰነው ወለጋ ውስጥ በሸኔ የሚፈጸመውን መፈጠርን የሚያስጠላ ግፍ መጥቀስ የግድ ይላል። ማንም ይሙት የሚገደለው ሁሉ አማራ፣ ገዳዩ ደግሞ ሸኔ ብቻ እንዲባል ለምን ተፈለገ? የሸኔ የፖለቲካ ፕሮግራምና ዓላማ ምንድነው? ሸኔን በፋይናንስ የሚደጉመው ማነው? ሸኔ ወለጋ ላይ በተለይ ያተኮረው ለምንድነው? ሸኔ ሲገድል የአማራ ተቆርቋሪዎች በምን ግንኙነትና ፍጥነት እየተቀበሉ ነው የፎቶና የቪዲዮ መረጃ የሚለቅቁት? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። በወለጋና ዙሪያው ስለ ተፈጸመውና እየተፈጸመ ስላለው መረጃ እንዲሰጡ ጎልጉል የጠየቃቸው የኦፌኮ ከፍተኛ አመራር የሰጡት ምላሽ “እነሱ አብረው ላለመሥራታቸው ምን ማስረጃ አለ?” ብሎ መልሶ በመጠየቅ ነበር።

በገፊና ጎታች ሤራ ከመፈንቅለ ሲኖዶስ እስከ መፈንቅለ መንግሥት

ካለፉት አራት ወይም አምስት ዓመታት ጀምሮ በኢትዮጵያ የሚታየው የፖለቲካ መካረርና ጡዘት የሁለትዮሽ የተናበበ የገፊና ጎታች ሤራ (Pull and Push Conspiracy) ነው ለማለት የሚያስችሉ በርካታ ጠቋሚዎች አሉ። የዚህ ሤራ ዓላማ ሕዝብን መስዋዕት በማድረግ መስዋዕትነቱ በሚፈጥረው ቁጭትና ሐዘን ሕዝብን ስሜት ውስጥ በማስገባት ሥርዓት አፍርሶ ሥልጣን ባቋራጭ ለመጨበጥ ያለመ ነው። ለነገሩ ይህ ዓይነት የፖለቲካ አካሄድ አመጽ በተቀላቀለበት መልኩ ሁልጊዜ ባይታይም ሠለጠነ በሚባለው ዓለም የተለመደ አካሄድ ነው። ፓርቲዎች ጎራ ለይተው ይናቆራሉ፣ ይሰዳደባሉ፤ ሚዲያው ጉዳዩን የተካረረ ፖለቲካ ያደርገዋል፤ ደጋፊዎች በስሜት በመነዳት ብዙ ርቀው ይሄዳሉ፤ አታጋይ የተባሉት ፖለቲከኞች ግን አብረው ሲበሉ፣ ሲጠጡ፣ ሲሳሳቁ ይገኛሉ። “የሠለጠነ ፖለቲካ” በማለት ይህንን ድራማ ሚዲያው ሌላ ቅኝት ሲሰጠው ተመልካቹ አብሮ ይደንሳል፤ እኛ ዴሞክራሲ ያልገባን ነን የምንል ደግሞ እንደነሱ ባደረገን ብለን እንመኛለን። አሁን ግን ከምኞት አልፈን ትወናውን በአገራችን የራሳችን ያደረግነው ይመስላል። 

የቅርብ ጊዜ ማስረጃ እንጥቀስ፤ የመረጃው ባለቤት ነኝ የሚለው ሰው ቀን ጠቅሶ፣ ማስረጃ አስደግፎ እንደጻፈው “ጃዋር መሐመድ ከኦህዴድና ከኦነግ ሰዎች ጋር በጥምረት ይሠራ ነበር። ይህ የአደባባይ ምሥጢር ቢሆንም የሚገርመው ግን ጃዋር “ነፍጠኛ አማራ” እያለ ቀን ከሌሊት ከሚሰድባቸው ቡድኖችም ጋር የሚሠራ መሆኑን ራሱ በነገረኝ ጊዜ ነው፤ የዚያን ቀን በጣም ነበር የደነገጥኩት (ዕለቱ ህዳር 7/2006 ነው)” ይላል ባለ መረጃው።

የወቅቱ ፖለቲካ ጦዞ ሲረግብና ጃዋር እስርቤት በነበረበት ወቅት ልትጠይቀው ለሄደች “ጋዜጠኛ” ከተናገረው መካከል የአንድነት ኃይሎች ከዱኝ የሚለው ተጠቃሽ ነው። ጎልጉል በዘገበው በዚህ የዜና ዝርዝር ውስጥ ይህ ጃዋር የተናገረው መረጃ ይገኛል፤ “እስክንድር ምን እንደሚፈልግ አውቃለሁ፤ የእርሱ ጉዳይ አያሳስብም” የሚል ነበር። በወቅቱ የነበረው ዕቅድ ባልደራሶች ኢትዮጵያዊ የሆነ ተቆርቋሪ አጀንዳ ያቀነቅናሉ፤ እነ ጃዋር በዚያኛው ጽንፍ የኦሮሞን ጥያቄዎችን ያከርራሉ፤ በዚህ ገፊና ጎታች ትንቅንቅ መንግሥት ላይ ከባድ ጫና ያሳድራሉ፤ ሕዝብ በቃኝ ይላል፤ በውጤቱም አይቀሬው የሸግግር መንግሥት ይመሠረታል። በመጨረሻም እንደ ፖለቲካዊ መዋጮው የአዲስ አበባ ከንቲባም ሆነ የጠቅላዩ ቦታዎች በስምምነቱ መሠረት ይፈጸማሉ። እስከዛሬዋ ቀን ድረስ የዘለቀውም ይኸው ምኞት አዘል የፖለቲካ አስተላለፍ ነው። 

ይህ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገራችንን ሲያተራምስ የቆየው የገፊና ጎታች  ሤራ በሁሉም መስክ ተከስቷል። እጅግ ዘግናኝ የሆኑ ብሔር ተኮር ግድያዎች፣ አቅርቦትና ምርትን በመነጣጠል የተፈጸሙ የንግድ አሻጥሮች፣ የፖለቲካው ዐውድ ጭር እንዳይል ማድረግ፣ በሰበር ዜና ሕዝብን ማስደንበር፣ ማስመረር፣ የሕዝብን ሕይወትና የአገርን ገጽታ የቀየሩ በርካታ ሥራዎችን ዕርባና ቢስ ማድረግ፣ ሕዝብንና መንግሥትን ማቃቃር፣ ጥላቻና አለመተማመን ማስፈን፣ ሕዝብን ስሜታዊ በማድረግ በአመክንዮ ሳይሆን በደመ ነፍስ እንዲመራ መንገድ መክፈት፣ በሒደትም ወደ ዓመጻዊ እንቅስቃሴ መቀየር፣ በመጨረሻም ሕዝባዊ ዓመጽ ማስነሳትና ሥርዓት መቀየር ነው።

ይህ ሁሉ የገፊና ጎታች ሤራ ዋና የትኩረት ማዕከል የሚያደርገው በሥልጣን ላይ ያለውን መሪ ነው፤ ለግቡ መዳረሻ ተጠንቅቆ ዝንፍ ሳይል የሚተገብረው መርህ ደግሞ እረኛውን መምታት ከዚያ መንጋውን በቀላሉ መበተን የሚለው ነው። በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ጎልጉል የዘገበው እዚህ ላይ ይገኛል “እረኛውን ግደል፣ መንጋው ይበተናል”። 

በቀጣይ በተለያዩ መስኮች ሲከናወን የቆየው ተጻራሪ የሚመስሉ ኃይሎች ተናብበው የሚሠሩ ሸፍጥ የመጨረሻው ሊባል የሚችለውን ቃታ ዓልሞና ዐቅዶ የሳበው በሃይማኖት ላይ ነው። ከሙስሊሙ የመጅሊስ ጉዳይ ቀጥሎ በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ ያነጣጠረው ጥቃት ሃይማኖታዊ ብቻ እንዳልሆነ እጅግ በርካታ ማሳያዎች አሉ። አሁን ላይ የታየው ውጤቱ ቢሆንም ዘሩ ከተዘራ ግን ትንሽ ሰንበት ብሏል።

ከምርጫው በፊት የትኛውንም መንገድ ተጠቅሞ ሥልጣን ለመያዝ የቋመጠው የጃዋር ቡድን በአስፈጻሚነት መረራ ጉዲናን እና ለማ መገርሣን የራሱ አድርጓል። በቀጣይ ፖለቲካን ከሃይማኖት እና ከብሔር ጋር በመቀየጥ ሲሻው ሙስሊሙን ለማነሳሳት “የ21ኛው ክፍለ ዘመን አህመድ ግራኝ ነኝ” በማለት በሌላ በኩል በእነ ቀሲስ በላይ ሽፋን የሸዋን ኦሮሞን ድጋፍ ለማግኘት ብዙ ርቀት ሄዶ ነበር። ሁሉም ሲከስር ለመጨረሻ ጊዜ በመናበብ በተለይ አዲስ አበባ ላይ የደረሰው ውድመትና የሃጫሉ ግድያ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ይህም ዕቅድ ሲከሽፍ በሌላ ሰይጣናዊ ሃሳብ እንደሚመለሱ የበፊት ታሪካቸው ሕያው ምስክር ነበር።  

ያሁኑ ጊዜ ለምን ተመረጠ?

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ዲ. ሩዝቬልት በአንድ ወቅት የተናገሩትና የሚጠቀስላቸው አባባል “በፖለቲካው ዓለም በድንገት የሚከሰት ነገር የለም፤ ካለም ድንገት የተከሰተ እንዲመስል ስለተደረገ ነው ብሎ መወራረድ ይቻላል” ብለው ነበር። ይህ ጊዜን፣ ሁኔታን፣ አጋጣሚን ወዘተ ጠብቆ በሲኖዶስ ስም የተነሳው ውዝግብ በዚህ ወቅት የተከሰተው በድንገት ነው ብሎ ማሰብ ፖለቲካን በቅጡ ካለመረዳት የሚመነጭ ደካማነት ነው።

See also  "ወርቅ ያበደረ ሰራዊታችን ጠጠር እየሰበሰበ መኖር የለበትም"

በአንድ በኩል አማራ ተበደለ በሚል በተለይ በወለጋ በሸኔ ስም አማራን በመናበብ ካስገደሉ በኋላ “የአማራ የመከላከያ ኃይል (Amhara Resistance Force) መመሥረት አለበት” የሚል እንቅስቃሴ የነበረ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ለኢትዮጵያ የሚያስፈልጋት የሽግግር መንግሥት ነው በሚል ለዓመታት ሲወተውት የነበረ በአገር ውስጥና በውጪ የሚንቀሳቀስ ቡድን አለ (ሥልጣን በእጅጉ ተመኝቶ የከሸፈበትና የበርካታ ፖለቲካዊ ቀውሶች ስውር መሪ የሆነውን ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስን እዚህ ላይ አለመጥቀስ አይቻልም)።

እዚህ ላይ ከጎጃም በሚዋሰነው ወለጋ ውስጥ በሸኔ የሚፈጸመውን መፈጠርን የሚያስጠላ ግፍ መጥቀስ የግድ ይላል። ማንም ይሙት የሚገደለው ሁሉ አማራ፣ ገዳዩ ደግሞ ሸኔ ብቻ እንዲባል ለምን ተፈለገ? የሸኔ የፖለቲካ ፕሮግራምና ዓላማ ምንድነው? ሸኔን በፋይናንስ የሚደጉመው ማነው? ሸኔ ወለጋ ላይ በተለይ ያተኮረው ለምንድነው? ሸኔ ሲገድል የአማራ ተቆርቋሪዎች በምን ግንኙነትና ፍጥነት እየተቀበሉ ነው የፎቶና የቪዲዮ መረጃ የሚለቅቁት? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። በወለጋና ዙሪያው ስለ ተፈጸመውና እየተፈጸመ ስላለው መረጃ እንዲሰጡ ጎልጉል የጠየቃቸው የኦፌኮ ከፍተኛ አመራር የሰጡት ምላሽ “እነሱ አብረው ላለመሥራታቸው ምን ማስረጃ አለ?” ብሎ መልሶ በመጠየቅ ነበር።

በገፊና ጎታች ሤራ ሕዝብ ከሚጨፈጭፈው ሌላ በመንግሥታዊ ሥርዓቱ ውስጥ በተሃድሶ (reform) ስም በደምሳሳው ይቅርታ ተሰጥቶት የተደመረ የካድሬ ስብስብና ከዚሁ ካድሬ ቡድን ጋር በቅንጅት የሚሠራ በዘመነ ትህነግ በሌብነት ሃብት ያካበተ በተለይ የአንድ አካባቢ ተወላጆች ያሉበት የባለሃብቶች ክንፍ አለ። የእነዚህን እና ሌሎች አገርን የማፍረስ ምኞት ያላቸው ኃይሎችን አስተሳሰቦች እየቀመመና እያቀናበረ ለሕዝብ የሚያቀርብ የሚዲያ እና አክቲቪስት ቡድን አለ። በአንዱ ወገን ያለው ሚዲያ ወይ የብሔር ወይም የሃይማኖት ጽንፍ ይዞ ያከርራል። ሌላኛውም እንዲሁ በዚያኛው መስመር በተጻራሪው ያከርራል። በዚህ ውስጥ በየፊናው የተሰማራ ተከታይ እርስ በርስ ይናቆራል፤ ስሜት ውስጥ ይገባል፤ በቀላሉ መፈታት የሚችሉ ጉዳዮች ይከርራሉ፣ ይጦዛሉ፣ አገር ልትፈነዳ ትደርሳለች።

ከዚህ በፊት እንዲሁ በመናበብ ከተደረጉት በርካታ ሙከራዎች በኋላ በቅርቡ ሲኖዶሱን ለመክፈል የተሄደበት መንገድ ከዚህ በፊት ከተከሰተው የገፊና ጎታች ሤራ ብዙም የተለየ አይደለም። የኦርቶዶስክ ቤተ ክርስቲያን ቋንቋን በተመለከተ ለሁሉም ተደራሽ አለመሆኗን አሁንም በአመራር ላይ ያሉት አምነው የሚቀበሉት ሐቅ ነው። ነገር ግን ይህንን ሽፋን በማድረግ ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ሲሠራበት የነበረው የገፊና የሳቢ ሤራ ከውጪ እስከ አገር ውስጥ በተናበበ መልኩ ቤተ ክርስቲያን ላይ ክንዱን አሳረፈ።

ለረጅም ጊዜ በዕቅድ ሲከርር የቆየው ፖለቲካ አሁንም “እረኛውን ምታና መንጋውን በትን” በሚል እሳቤ ብሔርና ሃይማኖትን ቀላቅሎ ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ ብቅ አለ። የተመቻቸ ጊዜ ብቻ ነበር የሚጠበቀውና የአፍሪካ ኅብረት ስብሰባ ወቅት ተመረጠ። ይህም ለመበጥበጥም ሆን ስብሰባውን ተከትሎ የሚመጡት ጋዜጠኞች በቀላሉ እንዲዘግቡና ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ችግሩን ለማቅረብ ፍጹም የተመቻቸ ሆነ። ሌላው ኢትዮጵያ በመዝገበ ቃላት ጭምር የችጋር መጠሪያ ስሟን በዳቦ ቅርጫት አድሳ ስንዴን ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ውጪ በመላክ የታሪክን ማርሽ የምትቀይርበት ሰሞን መሆኑ ሌላው ተደራቢ ምክንያት ነው። እንደ አለመታደል ሆኖ ይህ የአገራችንን ስምና ታሪክ የቀየረ ኩነት በቂ ትኩረት ሳይሰጠውና እንደሚገባው ሳይዘገብ ሳምንቱ አልፏል።

ከዚህ ሌላ በትዕቢት ተወጥሮ የነበረው ትህነግ ወታደራዊ ሽንፈት ከተጎናጸፈ በኋላ ወቅቱ በትህነግን ላይ ከፍተኛ የፖለቲካ ውድመት የሚያመጣ ሕዝባዊ ማዕበል በትግራይ ውስጥ ይከሰታል እየተባለ የሚጠበቅበት ነበር። የአፍሪካ ኅብረትን ከኢትዮጵያ ለማስነሳት የሚፈልጉ እንደ ግብፅ ያሉ ኃይሎች አገር በጥብጠው ዓላማቸውን ለማሳካት ሌላ ሙከራ ለማድረግ የተመኙበትም ነው። በዚህ መልኩ የተለያየ ዓላማና ግብ ያላቸው ኃይሎች የጠላቴ ጠላት ወዳጄ በሚለው በመስማማት ኃይላቸውን አስተባበሩ (እንደ ማሳያ ልደቱ አያሌውና በቀለ ገርባ በቅርቡ በዩትዩብ ሲያደርጉ የነበረውን ውይይት መጠቅስ ይቻላል)። በምኞት አቅሉን ያጣውንና በአካሄድ የተጋመደውን ክርናቸውን በቤተ ክርስቲያን ላይ አሳረፉ። ሲኖዶሱም ብሔርን ከሃይማኖት በቀላቀለ እኩይ መብረቅ ተመታ። በታቀደው መሠረት ነገሮች በፍጥነት በማኅበራዊ ሚዲያ እንደ አሜባ መባዛት ጀመሩ። ሕዝብ መዋከብ፣ በመንግሥት መዋቅር የተሸሸገው መሣሪያውን መምዘዝ፣ የሃይማኖት አባቶች ማልቀስ ጀመሩ። “ሲኖዶሱ ይህን ማድረግ፣ ይህንን መወሰን” አለበት የሚሉ እጅ ጠምዛዥ የፖለቲካ ድምፆች በፍጥነት ተበራከቱ። 

በሳዊሮሳዊ የገፊና ጎታች ሤራ ወደ ቤተ መንግሥት

አቡነ ሳዊሮስ የሚመሩትና በእነርሱ አጠራር “የኦሮሚያና ብሔር ብሔረሰቦች ሲኖዶስ” የተቋቋመበት ዋንኛ ምክንያት ዜጎች በቋንቋቸው መገልገል አልቻሉም የሚል ነው። ከስሙ ብንነሳ ኦሮሚያን ለብቻው ሌሎችን ግን በብሔር ብሔረሰብ ስም መጠቅለል የፖለቲካ ዓላማ ከሌለው በስተቀር አሰያየሙ ራሱ ከመንፈሳዊ ይልቅ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ነው። ሌላው ጥያቄያቸው ሲኖዶሱ በሰሜን ሰዎች በአብዛኛው የተያዘ ነው የሚል ሲሆን ይህንን ሐቅ በርካቶች በጭፍን ለመካድ የሚሞክሩት ቢሆንም የደቡብ ካሊፎርኒያ አገረ ስብከት ሊቀጳጳስ የሆኑት አቡነ በርናባስ ትክክል ነው በማለት ምስክርነታቸውን የሰጡበት ነው። እንደ ምክንያትም አድርገው የሚጠቅሱት አቡነ መርቆሪዮስ የሚመሩት የውጪው ሲኖዶስ ወደ አገር ሲገባ ከእርሳቸው ጋር አብረው ሲያገለግሉ የነበሩት ጳጳሳት ወደ ሲኖዶስ መቀላቀላቸው እንደሆነ ይናገራሉ።

የሕገ ወጡ ቡድን መሪዎች የሆኑት በድብቅ ወሊሶ አካባቢ ለ26 ሰዎች የኤጲስቆጶስነት ማዕረግ ከሰጡ በኋላ ወደዚህ ውሳኔ ያደረሳቸው ምክንያት በቋንቋ የመገልገልን ጉዳይ በተደጋጋሚ ለሲኖዶስ አቅርበው የሚሰማቸው በመታጣቱ መሆኑን ይናገራሉ። ሆኖም ግን የሲኖዶሱን አሠራር ጠንቅቀው የሚያውቁ እንደ መልአከ ሕይወት ቆሞስ አባ ወልደኢየሱስ ሰይፉ ያሉ የሚናገሩት ከዚህ የተለየ ነው። የቋንቋ ጉዳይ ቤተክርስቲያኗ እየሠራችበት ያለ ጉዳይ መሆኑን ራሳቸው ኦሮሞ መሆናቸውን በመጥቀስ የሚናገሩት አባ ወልደ ኢየሱስ፤ የሥራ ውድድርና ቅጥር ሲደረግ እንኳ እኩል ብቃት ካላቸው ተወዳዳሪዎች መካከል የተጨማሪ ቋንቋ (በተለይ ኦሮሚኛ) ችሎታ ያላቸው ቅድሚያ እንደሚያገኙ ይናገራሉ። ከዚህ ሌላ ወደ ካህናት ትምህርት ቤትም ሆነ ሌሎች ትምህርት ቤቶች ለመግባት ከሰሜን ለሚመጡት የከረረ የመግቢያ መሥፈርት እንደሚጠበቅባቸው፤ ከሌሎች የአገሪቷ ክፍሎች ለሚመጡ ግን ይህ መሥፈርት እንደሚለዝብ አባ ወልደ ኢያሱ ይናገራሉ።

ውሳኔ አሰጣጥን በተመለከተ፤ እንደ አሠራሩ ከሆነ ሲኖዶስ የሚሰበሰበው በዓመት ሁለት ጊዜ ነው – ጥቅምት እና ግንቦት ወራት። የጥቅምቱ ጉባዔ ከተካሄደ በኋላ ለሲኖዶሱ አንድ ከማን እንደሆነ ያልታወቀ ደብዳቤ ይመጣል። በዚህ ደብዳቤ ላይ የተጠቀሰው ሃሳብ እነ አባ ሳዊሮስ በኋላ ከዋናው ሲኖዶስ ለመለየት ያበቃቸው ምክንያት አድርገው የጠቀሱት ነው – በቋንቋ የመገልገል ጉዳይ። ደብዳቤውን የጠቅላይ ቤተክህነት ምክትል የሆኑት ቀሲስ በላይ ወዲያውኑ ወደሚመለከተው ክፍል ከመሩት በኋላ ምላሽ የሚሰጠው ቀጣዩ ሲኖዶስ በግንቦት ወር ሲሰበሰብ መሆኑ እየታወቀ ነው ሕገወጡ የጳጳሳት ሹመት በወሊሶ የተካሄደው። ስለዚህ ጉዳዩን አቅርበን የሚሰማን አጣን ወይም ምላሽ አላገኘንም የሚለው ሐቅን የጣሰ እንደሆነ አባ ወልደ ኢየሱስ ይናገራሉ። ለውሳኔው እስከ ግንቦት መጠበቅ ያልተፈለገውም ጉዳዩ ፖለቲካዊ ምክንያት ስላለው መሆኑን የጠቀሱት አባ ወልደኢየሱስ ከቤተክህነት ውስጥ የሕገወጡ ቡድን ደጋፊች ሊኖሩ እንደሚችሉ አልሸሸጉም። 

See also  ሠላም አስከባሪ ወደ ወልቃይት? አውሮፓ ሕብረት ምን እየወጠመደ ነው?

በቤተክርስቲያናዊ ቀኖና እና ሕገ ቤተክርስቲያን ጉዳይ በቅጡ ዕውቀትም መረዳትም የሌላቸው ፖለቲከኞች እንደሚሉት ሳይሆን ይህ በአባ ሳዊሮስ የቀረበው ምክንያት ለመለያየት የሚያበቃ አልነበረም። ነገር ግን ይህ የገፊና ጎታች ሤራ ስለሆነ መለያየቱ በጣም የሚፈለግ ነበር። በውዝግቡ መካከል ለቀናት ምንም ዓይነት ነገር ያልተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የካቢኔያቸው የስድስት ወር ስብሰባ ሲያጠናቅቁ የ37 ደቂቃ ሐተታ ሰጡ

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አንኳር ሃሳብ መንግሥት ለቤተ እምነቶች በተለይም ለኦርቶዶክስ የተቻለውን ጥረት የሚያደርግ እንጂ በመከፋፈላቸው የሚያተርፍ አይደለም የሚል ነበር። ሆኖም በፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ሲናወጡ የነበሩት ጳጳሳት ይህንን ንግግር በተባለበት ዐውድ እንዳይወስዱት ተደረጉ። በቀጣይም ሲኖዶሱ ከዚህ በፊት አድርጎ በማያውቀው መንገድ የጠቅላዩን ንግግር መስመር በመስመር፤ ቃል በቃል በመሄድ የሤራ ትንታኔ ሰጠበት። አሁን ሁለቱም ወገኖች ተነጋግረው ሰላም ሊመጣ የዚያን ጊዜ ግን ጠቅላዩ ሁለታችሁም ተግባቡ፣ ተነጋገሩ ብለው የጠቀሱት ምክረ ሃሳብ እንደ ወንጀል ተቆጥሮባቸው የሤራ ትንታኔው አካል ተደረገ።

ትንታኔው ከሃይማኖቱም ሆነ ከፖለቲካው ሰፈር ያሉ ሰዎች እንደተናገሩት በሲኖዶሱ የተዘጋጀ ነው ለማለት የሚያስቸገር፤ የሲኖዶሱን አሠራር የሚያውቅ ጥሩ ፖለቲከኛ የጻፈው የሚመስል፤ እንዲያውም አንድ የሃይማኖት አባት እንዳሉት አቡነ ጴጥሮስ ለማንበብ እስኪቸግራቸው በሌላ የተጻፈ ነው የሚመስለኝ ብለዋል። በመጨረሻም ይህ የሲኖዶሱ ምላሽ ሕዝበ ክርስቲያኑን አነቃነቀ፤ ቤተ ክህነት ከቤተ መንግሥት ጋር በኃይለኛው ተፋጠጠ። ቤተክርስቲያን የተቃውሞ ሰልፍ እንደምትጠራና እጅግ አደገኛ የሆነና ኦርቶዶክሳዊ ነው ለማለት የሚቸግር ዓርፍተ ነገር የተጨመረበት መግለጫ ሰጠች። ከትህነግ ጋር በተደረገው ጦርነት ዓለምአቀፉ ሚዲያና ማኅበረሰብ በቅንጅት በአገራችን ላይ ያደረሱት ተዘነጋና “የሰላማዊ ሰልፉ ዓላማ የዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ እንዲያይልን ነው” የሚል በሲኖዶሱ መግለጫ መጠቀሱ ጉዳዩ በፖለቲካ ኃይሎች የታነቀ ለመሆኑ ሌላው ማሳያ ነበር። በቀጣይ አስቀድሞ የተጠራው ሰልፍ የአፍሪካ ኅብረት በሚጀመርበት ሳምንት እሁድ ቀን እንዲደረግ ተላለፈ።

ከዚህ ውጥረት በኋላ የአባ ሳዊሮስ ቡድን በኦሮሚያ ክልል የጸጥታ አካላት እየታገዘ ወደተለያዩ ቤተክርስቲያናት በመግባት መቆጣጠሩን ያዘ። ለምሳሌ በወለጋ አስቀድሞም ከጠቅላይ የቤተክርስቲያን አስተዳደር የተገነጠለች የማርያም ቤ/ክ እነ አባ ሳዊሮስ ሄደው ተዋወቁ፤ ይህም ለትልቅ የፖለቲካ ዓላማ ፍጆታ ዋለ። በሌላ በኩል የወሊሶውን ሲኖዶስ አካሄድ የተቃወሙ ደግሞ ካህናትን ጨምሮ መታሰር፣ ሰብዓዊ መብታቸው መገፈፍ ቀጠለ። ሚዲያውና አክቲቪስቶችም ይህንን ሰከንድ በሰከንድ እየተከታተሉ ዘገቡ። እንደ ኦ.ኤም.ኤን. ያሉ የአባ ሳዊሮስን ቡድን በመደገፍ ባልተለመደ መልኩ በአማርኛ ተከታታይ ዘገባዎችን ሲለጥፉ በገፊና ጎታች ሤራ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ሌሎች እንደ ኢትዮ 360 ያሉ ደግሞ በዚያኛው ቡድን ዙሩን ማክረር ገፉበት።

ወቅቱ ጾመ ነነዌ የሚደረግበት በመሆኑ ሲኖዶሱ ቤተክርስቲያኗ እየተጋፈጠች ያለውን ፈተና አስመልክቶ ምዕመናን ማቅ እንዲለብሱ፣ ከጸሎት መጽሐፍና ከመጽሐፍ ቅዱስ በስተቀር ምንም ነገር እንዳይዙ አስጠነቀቀ። የሦስት ቀኗ ጉዳይ ለሤራ ቀማሚዎቹ ምቹ ጊዜ ፈጠረች፤ ሕዝቡን ለማሟሟቅና ለሰላማዊው ሰልፍ ለማዘጋጀት በጣም የተመቻቸ አጋጣሚ እንደተፈጠረ በየሚዲያቸው እያፈተለከ ከሚወጣው መረጃ ለመገንዘብ ተቻለ። በተለይ በጾሙ ማገባደጃ ቀን ረቡዕ በምሸት ጧፍ እያበራ የወጣው ሕዝብ ለሤረኞቹን እና ሕዝባዊ ዓመጽ ሲመኙ ለነበሩት አራት ኪሎን ከሚገምቱት በላይ አቀረበባቸው።        

See also  ከመጋረጃ ጀርባ የሚሰጥ ምስክርነት የህግ መሰረቱ እና ሀገ-መንግስታዊነቱ

የጾመ ነነዌ ጥቁር መልበስ መርሐ ግብር እንደተጠናቀቀ፤ ከመንግሥት በኩል እሁድ የካቲት 5 ምንም የተጠራ ሰልፍ እንደሌለና ዜጎች ራሳቸውን የፖለቲካ መጠቀሚያ ከመሆን እንዲጠብቁ ተነገረ። ወዲያው የወሊሶው ሲኖዶስ ለየካቲት 5 ደርቦ ጠርቶ የነበረውን ሰልፍ ሰረዘ። ከመንግሥት ለተሰጠው መግለጫ በአጸፋው ሲኖዶሱ ልክ የጠቅላዩን ንግግር በመስመር እንደተቸው ይህንንም እንዲሁ በመስመርና በቃል በታትኖ መግለጫ ሰጠበት። ከሲኖዶሱ የወጣው መግለጫ ጉዳዩ በእርግጥ ሊፈነዳ የደረሰና አገሪቷ ልትበጠበጥ መሆኑን በቀጥታ ያሳየ ሆነ።

በቀጣይ ሲኖዶሱ መንግሥት የቤተክርስቲያኗን ጥያቄ በ48 ሰዓት ውስጥ የማይመልስ ከሆነ የየካቲት 5ቱ ሰላማዊ ሰልፍ እንደሚደረግ አሳሰበ። በሚዲያ ፕሮፓጋንዳና በአክቲቪዚም ውስጥ የተሰገሰጉት ሲኖዶሱ ከውሳኔው በምንም መመለስ እንደሌለበት ከፍተኛ ጫና ማሳደራቸውን አጠናክረው ገፉበት፤ “አባቶችን ብቻ እንስማ” የሚለው ድምፅ ከምንጊዜውም በላይ አየሩን ሞላው። ጥቂት ተመልካች የነበራቸውና ለቤተክርስቲያኗ የቆምን ነን የሚሉ ዩትዩቦች በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ተመልካች በማግኘት ሰከሩ። በገፊና ጎታች ሤራ የሚደረገው ድራማ ቀጥሎ የሕገወጡን ቡድን ከመንግሥታዊ መዋቅር (በተለይ ኦሮሚያ) በሚያገኘው ድጋፍ የሚፈጽማቸውን የወንጀልና ቤተክርስቲያንን የመድፈር ተግባር በጽናት ገፋበት። ከዚሁ ሤራ ጋር ተባባሪ የሆኑ የፕሮቴስታንት ሰባኪያን አንደኛው ወገን ትልቅ ዐለት ለሁለት ሲከፈል ራዕይ አይቻለሁ ሲል ሌላኛው ደግሞ “ከመቅደስ ውጣ” በማለት ጉዳዩን በገፊና ጎታች ሤራ ሲያከርሩት ቆይተዋል። የቤተክርስቲያኗን አስተምህሮ በመቃወም የተለዩ የተሃድሶ አራማጆችም በዚሁ ውስጥ እንዳሉበት ይታመናል።

የእሁዱ የካቲት 5 ሰላማዊ ሰልፍ ይጨናገፍ ይሆናል በማለት የሰጉት የጉዳዩ ባለቤቶች “በሰልፍ አሊያም በሰይፍ” እያሉ በመፎከር ሲኖዶሱ ያወጣውን መግለጫ ወደ ሰማዕትነት ጥሪ በመቀየር ቤተመንግሥቱን እንደ ስሪላንካ አማጺያን የሚቆጣጠሩበት የቁርጥ ቀን መሆኑን አወጁ። ፖለቲካው በእጅጉ ያዋከባቸው አባቶች ነገሩን ረገብ አድርገው በመያዝ ወደ ዕርቅ የሚመራውን መንገድ ገፉበት። በውጤቱም አባቶች ያልተጠበቀ መንገድ ላይ ፍሬቻ ሳያሳዩ በድንገት ወደ ጎን ታጠፉ፤ የሤራ ተስፋውን አስቦ “አባቶችን ብቻ እንስማ” ሲል የነበረውም እጥፋቱ የሤራው መጥፊያ መጀመሪያ ሆነበት። ከመንግሥትም በኩል በተለይ ከጠቅላዩ ከሃይማኖት አባቶች ጋር ያደረጉት ውይይት አቅጣጫ የሚያስቀይር ሆነ።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ የሆነውና በስብሰባው የነበረው ዳንኤል ክብረት ከአርብ የካቲት 3 ስብሰባ በኋላ በጻፈው ትዊት “እስከ ዛሬ ስለ ክርስቶስ አስተምሬአለሁ። ተምሬያለሁ። ዛሬ ግን ክርስቶስን ራሱን አይቼዋለሁ” አለ። ይህም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የቤተክርስቲያን አባቶች ያደረጉት በለቅሶ ይቅር የመባባልና ሐቅን በገሃድ የመነጋገር ስብሰባ በኢትዮጵያ የሃይማኖትና ፖለቲካ ታሪክ እንደ አንድ ታላቅ ክስተት የሚጠቀስና ወደፊት በመጽሐፍ የሚሰነድ ሆኖ አለፈ። የሃይማኖቱ አባቶችም የቤተክርስቲያናችን የእኛ ጉዳይ ነውና ለእኛ ተውልን ሲሉ ፖለቲከኛና አክቲቪስቶችን ከቤተ ክህነታችን ውጡ በማለት የገፊና ጎታች ሤራውን አረገቡት። በውጤቱም የእሁዱ ሰላማዊ ሰልፍ ተሰረዘ! “አባቶችን ብቻ እንስማ” በሚል ሤራ ሕዝብን ሲያስተባብር የነበረው ቡድን ከባድ የተረከዝ ጅማት ጉዳት (Achilles injury) ምት ደረሰበት።

የሰላማዊ ሰልፉ መሰረዝ ሃይማኖትን ሽፋን ያደረገው የፖለቲካውን ካምፕ አፍረከረከው። “የሃይማኖት አባቶች ካዱን” እንዳይል አስቀድሞ በሠራው የገፊና ጎታች የሤራ ሥሌት ውጤት እርግጠኛ ስለነበር “አባቶችን ብቻ መስማት አለብን” ሲል ስለነበር ሲኖዶሱ ያደረገው ድንገተኛ እጥፋት ቅርቃር ውስጥ ከተተው። በተለይ ከእሁዱ ሰልፍ በፊት በነበረው አርብ ቤተክርስቲያኗ ለፍርድ ቤት ያስገባቸው የዕግድ ጥያቄ በፍርድ ቤቱ መጽደቁ ጉዳዩን እጅግ አወሳሰበው። የሤራው ሰፈር ከጠበቆች መካከል ዋነኛ የሆነውን አንዱዓለም በዕውቀቱ ገዳን (Andualem Buketo Geda) በማንነቱ ላይ በግልጽ ዘመቻ ከፈተበት፤ “የዐቢይ ወኪል ነህ፤ ኦነግ ነህ፤ ልቀቅ” የሚሉ ድምፆች ቢበራከቱም ፖለቲካው የገባቸው አባቶች የቤተክርስቲያናችን ጥያቄ ሙሉ በሙሉ ተፈረደልን በማለት ጠበቆቹን በአደባባይ አመሰገኑ።

“አባቶችን ብቻ እንስማ” የሚለው ከልብ ያልነበረ ፖለቲካዊ ሤራ ሌላ ያልታቀደ ትልቅ ኪሣራ ደረሰበት። ከጉዳቱ ሳያገግም ረቡዕ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአቡነ ማቲያስ ጋር በመሆን ታላቅ የዕርቅ መርሐ ግብር በጠቅላይ ቤተ ክህነት አካሄዱ። ያፈነገጡት ሦስት ጳጳሳት (አቡነ ሳዊሮስ፣ አቡነ ኢዮስጣቴዎስና አቡነ ዜና ማርቆስ) ከአቶነት ወደ ቀድሞው ብጹዕ አባትነት ቦታቸው ተመለሱ። ይህ በርካታ ጥናትና ምርምር የሚደረግበትና ታሪክ ሲያወድሰው የሚኖር ወደፊት ከአርዮስ፣ ንሥጥሮስ፣ ወዘተ ክህደት ባልተናነሰ መልኩ የሚጠቀስ ኩነት የገፊና ጎታች ሤራውን አሸንፎ በድል አድራጊነት ወጣ። ሲኖዶሱ፣ ፓትርያርኩ፣ ሊቃነ ጳጳሳት በተደጋጋሚ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ቃላት እስኪያጥራቸው አመሰገኑ። በገፊና ጎታች ሤራ ወደ ድል ተቃርቤአለሁ ሲል የነበረው ከመንግሥት መዋቅር እስከ ባለሃብት፣ ቤተ ክህነት፣ ሚዲያና አክቲቪስት በአገር ውስጥና በውጪ ተሰናስሎ እየተናበበ የተተበተበው ሤራ በአስደናቂ መልኩ ተበጣጠሰ። ሆኖም ጥቂት ዕረፍት አድርጎ እንደገና በተመሳሳይ ገፊና ጎታች ሤራ (Pull and Push Conspiracy) ነገርግን በሌላ አጀንዳ ሰሞኑን ብቅ እንደሚል ይጠበቃል።

ማሳሰቢያ፤ በዚህ ጽሑፍ “ገፊና ጎታች ሤራ (Pull and Push Conspiracy)” በማለት የሰየምነው በጎልጉል የጥናትና ምርምር ክፍል ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት የወጣ ስያሜ መሆኑ እንዲታወቅልን እንወዳለን። እሳቤው በመጠኑ ከሔግል ዳያሌክቲክ ጋር የውጤት ሳይሆን የአካሄድ ተዛምዶ አለው።

ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ©

Leave a Reply