የአማራና የትግራይ ህዝብ ወደ ሰላማዊ ግንኙነት

  • የአማራና የትግራይ ክልል ህዝቦች የእርስ በእርስ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር እንሰራለን-የሁለቱ ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች

አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል መሪ ከሆኑ በሁዋላ መግለጫ ሲሰጡና ቃለ ምልል ሲያደርጉ አይናቸውን የሚሸፍን መነጥር ያደርጋሉ። ይህ ለምን ሆነ በሚል አስተያየት የጠየቅናቸው ” አይናቸውን የሚሸፍኑት ደፍረው ህዝብን የማየት አቅም ስለሌላቸው ነው” ብለዋል። ሲያስረዱም ” አቶ ጊርታቸው በጦርነቱ ወቅት በጣም እላፊ ይናገሩና ይፎክሩ ስለነበር አፍረታቸውን ለመሸፈን የግድ መነጽር መጠቀም አለባቸው። በሚገርም የቃላት ጋጋታ ሳያቋርጡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለፍርድ ጆሮውን ይዘው እንደሚያቀርቡት ሲምሉ የነበሩ አቶ ጌታቸው ዛሬ ጥሩ ታዛዥ ሆነ ትግራይ ህዝብ ዘንድ ሲቀርቡ አይናቸውን ከመሸፈን ውጪ ሌላ አማራጭ የላቸውም” ብለዋል። ዛሬም ባህር ዳር የሆነው ይህ ነው።

የአማራና የትግራይ ክልል ህዝቦችን የእርስ በእርስ ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከርና ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት እንደሚሰሩ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለና የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ ገለጹ።

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ የተመራ ልዑክ በባህርዳር ከተማ በመገኘት የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ማጠናከር የሚያስችል ውይይት ከአማራ ክልል አመራሮችና የህዝብ ተወካዮች ጋር አካሂደዋል።

በዚሁ ጊዜ የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጌታቸው ረዳ በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት በሁለቱ ህዝቦች መካከል የወንድማማችነት ስሜት ማስቀጠል እንደሚገባ ገልጸዋል።

“የህዝባችን ፍላጎት ሰላም ነው፣ የህዝባችን ፍላጎት ተከባብሮ መኖር ነው፣ አብሮ መነገድ ነው” ያሉት አቶ ጌታቸው፤ የህዝቦች የቀደመ ግንኙነት እንዲመለስ የመሪዎች ቁርጠኝነት ያስፈልጋል ብለዋል።

“ባህር ዳር መገኘታችን የተከፈተውን በር አስፍተን፣ ሁሉም አይነት ሰላማዊ እንቅስቃሴ በሁለቱም ወገን የሚካሄድበት ሁኔታ ለመፍጠር ነው“ ብለዋል።

የመገናኛ ብዙሃንም ጥላቻን ሳይሆን ሰብዓዊነትን መሰረት አድርገው መስራት እንዳለባቸው ያሳሰቡት አቶ ጌታቸው የአማራ ክልል አመራሮችም የሁለቱ ክልል ህዝቦች ወደ ቀደመ ግንኙነታቸው እንዲመለሱ እያደረጉ ላለው እንቅስቃሴ ምስጋና አቅርበዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው ህዝብ ሰላምን አጥብቆ እንደሚፈልግ ገልጸው ለሁሉም ነገር መሰረቱ ሰላም መሆኑን ተናግረዋል። የአማራ ክልል አመራር ከህዝቡ ጋር በመሆን የሁለቱ ክልሎች ህዝቦች ሰላምና በጋራ አብሮ ማደግ በትኩረት እንደሚሰራ አስረድተዋል። በሁለቱ ክልሎች መካከል ትራንስፖርት ተጀምሮ ህዝብ ለህዝብ መገናኘትና አስፈላጊው የንግድ ልውውጥ መካሄድ እንደሚገባው አስረድተዋል። ይህ እንዲፋጠን ደግሞ አሁን ላይ ህዝብን እየመሩ ያሉ የሁለቱ ክልል አመራሮች ከፍተኛ ሃላፊነት እንዳለባቸው ገልጸዋል።

See also  Amid war and instability, why the Ethiopian election matters

ዛሬ የተደረገው ግንኙነት የመጨረሻ ሳይሆን በየደረጀው መውረድ የሚገባውና ለዘመናት በጋራ የኖሩትን የሁለቱን ክልል ህዝቦች ግንኙነት ወደ ነበረበት ለመመለስ ያለመ ነው ብለዋል። በአማራ ክልል በኩል የህዝቦች ግንኙነት ወደ ነበረበት እንዲመለስ አስፈላጊው ስራ ሁሉ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች የሁለቱ ክልል ህዝቦች ግንኙነት ወደነበረበት እንዲመለስና የተጀመረው የሰላም ግንኙነት የፀና ለማድረግ ባህር ዳር መጥተው ውይይት በማድረጋቸው ምስጋና አቅርበዋል። የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው የክልሎቹ አመራሮች የተጀመረውን ሰላም ማጽናትና ለህዝቦች አንድነት መትጋት አለባቸው ብለዋል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል ወይዘሮ የህዝቡ ጥላካሳ ለህዝቦች በጋራና በሰላም አብሮ መኖር በክልል መሪዎች የተጀመረው ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከልብ በመነጨ መንገድ መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የአማራና የትግራይ ህዝብ በዘርፈ ብዙ መስተጋብሮች ለዘመናት ተሳስሮ የነበረና ወደ ፊትም አብሮ የመኖር እጣ ፈንታ ያለው እንደሆነ የገለጹት አቶ ስማቸው ንጋቱ ናቸው።

”ለዘመናት ተሳስሮ የኖረን ህዝብ መበጠስ አይቻልም” ያሉት አቶ ስማቸው መሪዎች የህዝቡን ፍላጎት መሰረት ያደረገ ስራ መስራት እንዳለባቸው ገልጸዋል። ዘገባው የኢዜአ ባህር ዳር ነው

Leave a Reply