Site icon ETHIO12.COM

“በአማራ ክልል ግድያና በሴቶች ላይ የሚደርስ ፆታዊ ጥቃት ቀጥሏል”፤ መንግስት አሁንም ለንግግር በሩ ክፍት እንደሆነ አስታወቀ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ(ኢሰመጉ) ‹‹ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ማለትም ባህርዳር፣ መራዊ፣ ደምበጫ፣ አማኑኤል፣ ሉማሜ፣ ደብረማርቆስ፣ ፍኖተሰላም፣ ብቸና፣ ደብረታቦር፣ ወረታ፣ አዲስ ዘመን እና ሌሎችም አካባቢዎች ላይ ግድያ፣ እገታ፣ እስር፣ ዘረፋ እንዲሁም በሴቶች ላይ የሚደርስ ጾታዊ ጥቃት መቀጠሉን ›› ካሰባሰብሁት መረጃዎች ለመረዳት መቻሉን ሸገር አመልክቷል። መንግስት ለንግግር በሩ ክፍት እንደሆነ አስታውቋል።

‹‹ ይህ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች ላይ የሚደርስ ሲሆን በተለይ ሴቶችን ተጋላጭ ያደረገ መሆኑን፣ በተጨማሪም ከላይ በተጠቀሱት አካባቢዎች እንቅስቃሴዎች የተገደቡ መሆናቸውንም ›› ኮሚሽኑ አክሏል፡፡ ከሁለት ቀን በፊት የመከላከያ ከፍተኛ መኮንኖች ኤታማዦር ሹሙን ጨምሮ አምራ ክልል የሚነቀሳቀሱ ታጣቂዎችን በዝርፊያና አስገድዶ መደፈር የሚወነጀሉና ህዝብን ያማረሩ መግለጻቸው ይታወሳል።

ኮሚሽኑ ‹‹ በተዘረዘሩት ሁሉም ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ የምርመራ ስራን በመስራት አሕዛዊ መረጃዎችን የያዘ ዝርዝር ዘገባን እንደሚያዘጋጅ ›› ሸገር ጨምሮ አመልክቷል፡፡

ኢሰመጉ ባስቀመጠው ምክረሃሳብ  ‹‹ የፌደራልና የአማራ ክልል መንግስታት በአማራ ክልል በንጹሀን ላይ እየደረሰ ያለውን የሰብአዊ መብት ጥሰት በቂ ትኩረት በመስጠት የሰዎች በህይወት የመኖር መብትን እንዲያከብሩና እንዲያስከብሩ ›› ጠይቋል፡፡

‹‹ በአማራ ክልል እየተስተዋለ ያለውን የንጹሃን እልቂት፣ የንብረት ውድመትና በአጠቃላይ የሰላም እጦት ከዚህ የከፋ ሁኔታ ላይ ከመድረሱ በፊት በጦርነት መፍትሄ ላይ መድረስ እንደማይቻል ታውቆ በመንግስት እና በታጣቂ ሀይሎች መካከል ውይይት በማድረግ ዘላቂ መፍትሄ እንዲሰጠው ›› ኮሚሽኑ አሳስቧል፡፡
ጉባዔው መግለጫውን ሲያጠቃልል ‹‹ በመጨረሻም መንግስት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 6/2015 አፈጻጸምን በቅርበት በመከታተል አዋጁን ያለአግባብ በስፋት በመተርጎም ለሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ምክንያት እንደይሆንና ስልጣንን አላግባብ ለመጠቀም በሮችን እንዳይከፍት ጥብቅ የሆነ ቁጥጥር እንዲያደርግ ›› ጥሪውን አቅርቧል፡፡ ፓርላማው ይህንን የሚያጣራ ኮሚቴ አቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱ የሚታወስ ነው።

በሌላ ዜና መንግስት ለመደራደር ዝግጁ መሆኑን ገለፀ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚታዩ ግጭቶችን የውጭ ጣልቃ ገብነት እስከሌለ ድረስ በሰላማዊ መንገድና በድርድር ለመፍታት መንግሥት ቁርጠኛ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መናገራቸውን የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ገለጸ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን የተናገሩት ለመጀመሪያ ጊዜ ከሠራተኛ ማኅበራት መሪዎች ጋር ረቡዕ ነሐሴ 24 ቀን 2015 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው ባካሄዱት የውይይት መድረክ ላይ መሆኑን፣ የኢሠማኮ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የኢሠማኮ መሪዎች ምላሽ እንዲሰጥበት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቀረቧቸው ጥያቄዎች መካከል ከፀጥታ ችግር ጋር የተያያዘ ጉዳይ አንዱ እንደነበር አቶ ካሳሁን አስረድተዋል፡፡

ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ መፈታታቸው ጠቀሜታ እንዳላቸው፣ የሰሜኑን ጦርነት መንግሥት በሰላም ለመፍታት የወሰደው ዕርምጃ ትክክለኛና ኢሠማኮም የሚደግፈው መሆኑን፣ ይህ ዕድል በሌሎች ክልሎች አሁን የሚታዩ ግጭቶችም በተመሳሳይ እንዲውል ጥያቄ ማቅረባቸውን አስረድተዋል፡፡ በተለይ በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ያሉ ግጭቶችን በምሳሌነት በመጥቀስ በሰላማዊ መንገድ በድርድር ሊፈቱ እንደሚገባ ኢሠማኮ ላቀረበው ጥያቄ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በየትኛውም መንገድ ቢሆን መንግሥት ሰላም የሚሻ መሆኑን እንደገለጹላቸው አቶ ካሳሁን ተናግረዋል፡፡

ሰላም ከሌለ ለሠራተኛ ውጭ ሆነ ለሁሉም ሕዝብ ችግር በመሆኑ ጉዳዩ እንደሚያሳስብ የተናገሩት አቶ ካሳሁን፣ በአንዳንድ ድርጅቶች ውስጥ ሠራተኞች በታጣቂዎች እንደሚገደሉና እንደሚታገቱ በመጥቀስ ጭምር ግጭቶች በሰላም መፈታታቸው ተገቢ መሆኑን በማመን ጥያቄውን ማቅረባቸውንም ጠቁመዋል፡፡ ለቀረበላቸው ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ፣ ጥያቄዎቹ መቅረባቸው ትክክል መሆኑን በመግለጽ፣ መንግሥት ሁሉም ነገር በሰላም እንዲፈታ የሚፈልግ መሆኑን እንዳረጋገጡላቸው አቶ ካሳሁን ገልጸዋል፡፡

‹‹ሰላምን የሚጠላ ስለሌለ ካልተገደድን በስተቀር ለእኛ ሰላም ከሁሉም በላይ ነው፤›› በማለት መንግሥት ለሰላም ቅድሚያ እንደሚሰጥ ጭምር መናገራቸውን ከቶ ካሳሁን ገለጻ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ‹‹እናንተም ምርትና ምርታማነት ተረጋግጦ ሥራዎችን ከመሥራት አንፃር ጥያቄውን ማንሳታችሁ ትክክል ነው፤›› እንዳሏቸው የተናገሩት አቶ ካሳሁን፣ ‹‹የውጭ ጣልቃ ገብነት ከሌለ በስተቀር እርስ በርሳችን በውይይት ችግሮቻችን የማንፈታበት ምክንያት አይኖርም፤›› በማለት መንግሥት የሚፈጠሩ ችግሮችን በሰላም ለመፍታት ሙሉ እምነት እንዳለው እንደነገሯቸው አመልክተዋል፡፡

ሰላምን ለማምጣት ግን የሁሉንም ርብርብ ይፈልጋል የሚል መልዕክታቸውን ለሠራተኞች መሪዎች የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግሥት ሰላምን እንደሚሻ ተናግረዋል ብለዋል፡፡ በውይይት መድረኩ ላይ ከፀጥታ ችግር ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ከቀረቡ ጥያቄዎች ባሻገር፣ የሠራተኞች አንገብጋቢ የተባሉ ጥያቄዎችንም በሠራተኞች መሪዎች አማካይነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጥታ ቀርቧል ሲሉ አቶ ካሳሁን አስረድተዋል፡፡

ሦስት ሰዓታት እንደፈጀ በተነገረለት በዚህ የውይይት መድረክ ላይ፣ ኢሠማኮ ሊመለሱ ይገባል ብሎ ላቀረባቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዎንታዊ ምላሽ የሰጡ መሆናቸውን አቶ ካሳሁን አብራርተዋል፡፡ ‹‹ሊመልሱልን ይገባል ላልናቸው ጥያቄዎች ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተፈጻሚ ይሆኑ ዘንድ አቅጣጫ ሰጥተዋል፤›› ያሉት አቶ ካሳሁን፣ ያደረጉት ውይይትም ጥያቄዎቻቸው በአግባቡ ሊመለሱ የሚችሉ መሆናቸውን ማረጋገጫ ያገኙበት መድረክ እንደነበረም አስታውሰዋል፡፡

ኢሠማኮ በዚህ መድረክ በዋናነት በዋጋ ንረት ምክንያት በሠራተኛው ላይ እየተፈጠረ ያለውን ጫና ለማርገብ፣ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲተገበርና የደመወዝ የሥራ ግብር እንዲቀንስ ጥያቄ ማቅረቡን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Exit mobile version