Site icon ETHIO12.COM

“አፈቀላጤው” ርዕሰ መስተዳድር በትግራይ የኩዴታ ስጋት ውስጥ

የትግራይ ክልል አሁናዊ ቁመና አሳሳቢ ነው። ከጦርነቱ በሁዋላ የተከሰተው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ስነልቦናዊ ቀውስ ሳያገግም ፖለቲካዊ ዳግም እየጦዘ ነው። ከፊታቸው “ንጻነት” የሚል ወይም “ወያኔ” የሚል መለያ የማያጡት የትግራይ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች “አዲስ” የሚባለው የክልሉ አስተዳደርም መከራውን እያበዙበት ነው። የዚሁ መገለጫ የሆነው ደግሞ ” አዲሱ አስተዳደር በቃው” የሚል አጀንዳ የተካተተበት ሰላማዊ ሰልፍ መጠራቱ ነው።

በስዊዲን የሚኖሩ የትግራይ ተወላጅ እናት ” ከጦርነቱ ወቅት ባልተናነሰ ጭንቀት ነው። ከዘመዶቼና ቤሰቦቼ የምሰማው ዕረፍት የሚነሳ ነው። ግድያ፣ ዝርፊያ፣ የተፈናቃዮች ችግር … ” እኙህ እናት የሚገርማቸውን ሲያክሉ ” ዛሬ ትግራይን መልሶ ማቋቋ የተቸገሩትን መርዳት በቀደመ ነበር። እጅ ለእጅ መያያዝ ልክ በጦርነቱ ወቅት የነበረው ዓይነት ቅስቀሳ ማድረግ መረባረብ ነበረብን። ጦርነቱን ሲቀሰቅሱ የነበሩ ሁሉ ተጸጽተው ማስተባበር ሲገባቸው ዛሬም የተማሩ አይመስሉም” ብለዋል።

በጦርነቱ ልጆቻቸውን ያጡና አካለ ጎደሎ የሆኑባቸውን የዘመዶቻቸውን ስም እየጠሩ በለቅሶ ” ሁሉም ረጋ ብለው ቢስማሙ ይበጃል” ሲሉ መክረዋል። የትግራይ ነፃነት ፓርቲ፣ ሳልሳይ ወያኔ (ሶስተኛ ወያኔ) ትግራይና የታላቋ ትግራይ ብሄራዊ ሸንጎ የተባሉ ሦስት ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ ምላሽ ያላገኙ የትግራይ ህዝብ ወቅታዊ ችግሮች ለማሰማት በሚል የተቃውሞ ሰልፍ እንደሚያደርጉ ማስታውቃቸውን ተከትሎ በትግራይ የፖለቲካውን መካረር የሚያመላክቱ መረጃዎች እየወጡ ነው።

“በትግራይ ኩዴታ ታስቧል” ሲሉ መላምታቸውን የሚያስቀምጡ ቢኖሩም ሰልፍ የጠሩት ወገኖች በፖለቲካ ቋንቋ ” ይህ መንግስት የሽግግር ጊዜውን ጨርሷል” ሲሉ የስልጣን ጥያቄያቸውን በገሃድ አንስተዋል።

በትግራይ ብቻ ሳይሆን በመላው አገሪቱ በሚባል ደረጃ የሽግግር መንግስትና የክልልነት ጥያቄ አቋራጭ የስልጣን መያዣ ሆኗል። በተለይም የክልልነት ጥያቄ በምስኪኖች ደም የሚነገድበት የፖለቲካ ቁማር ነው። በትግራይ ያለው ከዚህ ቢለይም የሰላማዊ ሰልፉ ዓላማ ሲጠቃለል “አዲስ” የሚባለው የክልሉ መንግስት የማስወገድና “ምዕራብ ትግራይ” የሚባለውንና ቀደም ሲል በፖለቲካ ውሳኔ ወደ ትግራይ ክልል የገቡ የአማራ ክልል ይዞታዎች እንዲመለሱ መግፋት ነው።

ራሱን “የትግራይ የመጀመሪያ ተቀናቃኝ ፓርቲ” ሲል የሰየመው ” አረና ትግራይ” ጉባኤውን ካጠናቀቀ በሁዋላ የትግራይ ክልል በኢትዮጵያ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ባለቤት ለማድረግ ለመስራት ዕቅድ መያዙን ባስታወቀበት መግለጫው ሰልፉን ደግፏል። ለሰልፉ ድጋፍ ሲሰጥ ተሰልፎ አቋምን መግለጽ መብት እንደሆነ አመልክቶ ሁሉም ወገኖች ግን የሰው ህይወት እንዳይጠፋ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ሁሉንም ወገኖች አሳስቧል።

ዓረና ትግራይ ለሉአላዊነትና ዴሞክራሲ የኢትዮጵያ ሕገመንግሥትን በማሻሻል አዲስ ማኅበራዊ እና ፖለቲካዊ ውል ለመመስረት ከሌሎች በኢትዮጵያ ካሉ የፖለቲካ ፖርቲዎች ጋር በጋራ እንደሚሠራ አመልክቶ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ባለቤት ለመሆን ይቻል ዘንድ ሌሎች ያላቸውን ፓርቲዎች እንደሚያስተባብር አመልክቷል። ድርጅቱን ጠቅሶ ዜናውን ያሰራጨው የጀርመን ድምጽ ዓረና ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ጥያቄን ቀዳሚ ለማድረግ ያሰበበትን ምክንያት አላብራራም። ምን አልባት ውዝግብ ባለባቸው አካባቢዎች ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የመጨረሻ ውሳኔ ሰጪ አካል ከመሆኑ ጋር ሊያያዝ እንደሚችል የገመቱ አሉ።

ዓረናም ሆነ ሌሎች የትግራይ ተቀናቃኝ ድርጅቶች በትግራይ ክልል ስልጣን የያዙ ግለሰቦች በተለይም ሴቶችን መግደል፣ ሀብት መውረስን ጨምሮ በተለያዩ ሕገወጥ ተግባራት ተሰማርተዋል ብለዋል ። ፓርቲዎቹ  “የማዕድናትና የሰዎች ሕገወጥ ዝውውር ላይ ከፍተኛ የፖለቲካና ወታደራዊ መሪዎች እጃቸው አለበት” ሲሉ ትህነግን ይከሱታል።

ሲጀመሩ ሶስት ቢሆኑም አምስት ሆነው ማለትም ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ፣ ውድብ ናፅነት ትግራይ ፣ ባይቶና ዓባይ ትግራይ ፣ ዓረና ንሉኣላውነትን ንዴሞክራስን፣ ውድብ ዓሲምባ ከጳጉሜን 2 እስከ 4 /2015 ዓ.ም በጥምር ለሚያካሂዱት ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ በመቐለ ከተማ በመኪና በመዞር በድምፅ ማጉልያ በመታገዘ እየቀሰቀሱ መሆናቸው ቲክቫህ ኢትዮጵያ የመቐለ ቤተሰብን ጠቅሶ አስታውቆ ነበር።

የመቐለ ከተማ አስተዳደር ከዚህ ቀደም የተቃውሞ ሰልፉን በተመለከተ ከፓርቲዎቹ በተላከለት ” የእወቁልኝ ” ደብደቤ በሰጠው ምላሽ ሰልፍ ማድረግ በኢፌዴሪ አዋጅ ቁጥር  3/1991 የተቀመጠ መብት ቢሆንም የተመረጠው ጊዜ አዲስ ዓመትና ሃይማኖታዊ በዓላት የሚበዙበት በመሆኑ ለማስተናገድ እንደሚቸገር ማሳወቁ ይታወሳል።

ለአሸንዳ በዓል መቀለ ደርሳ ወደ አውሮፓ የተመለሰች አንድ የትግራይ ተወላጅ እንዳለችው በበላዓሉ ዕለት ብቻ በሺህ የሚቆጠር ሞባይል በሌቦች ተዘርፏል። ነጠቃ ነው የሚመስለው። ህግና ስርዓት ያለ አይመስልም። የሚታየው ሁሉ ያሳዝናል” ስትል ትዝብቷን አጫውታናለች።

አቶ ጌታቸው የሚመሩት ጊዜያው አስተዳደር ለተጠራው የተቋውሞ ሰልፍ ፀጥታ የማስከበር ግዴታና ሃላፊነት እንዳለበትም አስታውሶ፣ በመጪው አዲስ ዓመት በዓል በሚኖረው ሰፊ እንቅስቃሴ ሳቢያ የስራ መደራረብና የጸጥታ ስራው አስቸጋሪ በመሆኑ ሰልፉን መፍቀድ ከደህንነት አንጻር አዳጋች እንደሚሆን አስታውቋል። ስለሆነም የቀረበውን የሰላማዊ ሰልፍ ጥያቄ ማስፈፀም እንደማይችል ይፋ አድርጓል።

የመቀለ ከተማ አስተዳደር የሰጠው ምላሽ አሳማኝና አጥጋቢ አይደለም በሚል ሰልፉን በተያዘው ጊዜ እንደሚያካሂዱ ዳግም ማረጋገጫ ሰጥተዋል። ይህንኑ ውሳኔያቸውን ተከትሎ ሰልፉን በተሽከርካሪ ማስተባበር ቀጥለው ነበር። ሰልፉ ሰላማዊ በመሆኑ ምንም ስጋት እንደሌለ በመጥቀስ ክልከላውን ወደ ጎን በማለት ቅስቀሳ ላይ የነበሩት መያዛቸውም ተሰምቷል።

” ኪዳን ሱር በቆስ ለውጢ ” በሚል ለተሰየመው ሰላማዊ የተቋውሞ ሰልፍ ሲያነሳሱ የነበሩት ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ፣ ውድብ ናፅነት ትግራይ ፣ ባይቶና ዓባይ ትግራይ ፣ ዓረና ለሉኣላውነትና ለዴሞክራስና ፣  ዓሲምባ የተባሉ 5 ቱ የትግራይ ተፎካካሪ የፓለቲካ ፓርቲዎች ከጳጉሜን 2 እስከ 4 /2015 ዓ.ም በጥምር ለሚያካሂዱት ሰላማዊ የተቓውሞ ሰልፍ በመቐለ ከተማ በመኪና በመዞር በድምፅ ማጉልያ በመታገዘ እየቀሰቀሱ ሳሉ ነው አባላቱ መታሰራቸውን የተለያዩ ሚዲያዎች ዘግበዋል።

ነገብረኣብ ወልዱና ብርሃነ ኣርኣያ ከሳልሳይ ወያነ  ፣ ብርሃነ ዘመን ዮሃንስና ገብሩ ከባይቶና ፣ ጠዓመ ሓጎስና ኣፅብሃ ተኽለ ከውድብ ናፅነት ትግራይና እንዲሁም የድምፅ ማጉልያና መኪና ያካራዩና ባለሙያዎች መሆናቸ የአይን አማኞች እንዳረጋገጡለት ቲክቨሃ አመልክቷል። ታሳሪዎቹ በቀዳማይ ወያነ ክፍለ ከተማ ፓሊስ ጣብያ እንደሚገኙም ታውቋል። 

የባይቶና ከፍተኛ አመራር አቶ ኪዳነ አመነ በማህበራዊ የትስስር ገፃቸው  “… ‘ኪዳን ንሱር ቦቆስ ለውጢ ‘ በሚል በወርሃ ጳጉሜን እንዲካሄድ ለጠራነው ሰላማዊ የተቋውሞ ሰልፍ ሲያነሳሱ የነበሩ አባሎቻችን መታሰራቸው ለክልሉ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዚደንት ጌታቸው ረዳና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት አባሎቻችን ያለ ቅድመ ሁኔት በአንድ ሰዓት ውስጥ በአስቸኳይ እንዲፈቱ ደብዳቤ ፅፈናል ። ” የሚል አሳብ አስፈረዋል። ምላሹ ግን አልታወቀም።

የከተማው አስተዳደር ለተጠራው የተቋውሞ ሰልፍ ፀጥታ የማስከበር  ግዴታና ሃላፊነት እንዳለበት በመጥቀስ ፤ ይሁን እንጂ በበዓሉ በሚኖረው የህዝብና የመኪና ሰፊ እንቅስቃሴ ምክንያት በሚፈጠር የስራ መደራረብ የተነሳ የቀረበውን ጥያቄ ማስፈፀም እነደማይችል በያዘው አቋም አሁን ድረስ እንደጸና ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዓሲምባ ” ኪዳን ንሱር በቆስ ለውጢ ” በሚል መፈክር ጳጉሜን 2 /2015 ዓ.ም በ5 የፓለቲካ ፓርቲዎች በመቐለ እንዲካሄድ ከተጠራው ሰላማዊ የተቋውሞ ሰልፍ ራሱን እንዳገለለ ይፋ ሆኗል። ፓርቲው በሊቀመንበሩ አቶ ዶሪ አስገዶምና በኩል በፓርቲው በማህበራዊ የትስስር ገፅ ” የተጠራው ሰልፍ ህጋዊ አካሄድ ያልተከተለ እንደሆነ የሚመለከታቸው አካላት በማስረጃ አስደግፈው አስረድተውናል። ህግ ይከበር እያልን ህግ መጣስ ህዝባችንን ስለማይመጥን ከተጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ራሳችን ለማግለል ወስነናል። ሁሉም ከህግ በታች ነው ” የሚል አቁማቸውን ከምክንያት ጋር አቅርበዋል።

ቲክቫህ ከትግራይ ቤተሰቦች እንዳገኘው ጠቅሶ እንዳለው

ሰላማዊ ሰልፉ ሌላ እንደምታ እንዳለው የሚገልጹ እንደሚሉት ጉዳዩ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደርን መብላት ነው። ይህ በተቃውሞ ሰልፍ ስም አስተዳደሩን ለመብላት የተደረጃው ስብስብ ከጀርባ የሚመራው ባኮረፉ የትህነግ ሰዎች እንደሆነም ተመልክቷል። ይህን መረጃ ያደረሱን እንደሚሉት የተቀናቃኝ ድርጅቶቹ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ ትህነግ ስር ሆነው የተደራጁ በመሆናቸው ካኮረፉት ፈጣሪዎቻቸው ጋር አብሮ ለመስራት ችግር አይኖርባቸውም።

የፌደራሉ መንግስት በዶክተር ደብረጽዮን የሚመራውን የመጀመሪያውን የጊዜያዊ አስተዳደር ዝርዝር ከሰረዘ በሁዋላ ነው ኩርፊያው እያደገ የመጣው። የትግራይ መከላከያ ሃይል የተባለውን ታጣቂ ሃይል የሚመሩት ወገኖች ጦርነቱን ተከትሎ የበላይነት መያዛቸው የእነ ዶክተር ደብረጽዮንን ቡድን አቅም በልቶታል።

“አሁን እንደሚሰማው ከሆነ ይህ ሃይል በጦርነቱ የተጎዱትን ሳይቀር ለአመጽና ለተቃውሞ ያደራጃል። ራሱ ቆስቁሶና ሰብኮ ወደ ጦርነት የማገዳቸውን ወጣቶች ማልሶ ለኩርፊያው መጠቀሚያ እያደረገ ነው” የሚሉ ክፍሎች ” እውነቱ አንድ ነው። እሱም ኩዴታ ለማካሄድ ዝግጅት ነው” ሲሉ የባሰ ችግርና ነብስ መጠፋፋት እንዳይከሰት የመክራሉ።

“በሌላ በኩል ግን ትህነግና ከትግነግ ጋር ንክኪ ያያላቸው በሙሉ ለፍርድ እንዲቀርቡ መደረግ ነበረበት” የሚሉ ወገኖች ” ነገር የተበላሸው አሜሪካ አቶ ጌታቸውን ረዳን አበባ እየረጩ፣ ከበሮ እየደበደቡ በዕልልታ የተቀበሉት ቀን ነው” ሲሉ የትግራይ ተወላጆችን ይወቅሳሉ። እነዚህ ወገኖች እንደሚሉት ለትህነግ ሰዎችና አመራሮች በዚህ ደረጃ ሽብሸባና ዕልልታ ምክንያቱ አይገባቸውም። ” የትግራይን ወጣቶች ስላስጨፈጨፉ? አካለ ጎዶሎ ስላስደረጉ? የትግራይ ህዝብ ከጎረቤቶቹ ጋር ጠላት ሆኖ ተፈናቅሎ እንዲኖር ስለፈረዱ? በማይሆን ጦርነት ትግራይ እንዲወድም ምክንያት ስለሆኑ? ህዝቡን ለማኝ ስላደረጉ፣ የትግራይን ህዝብ ወደ ጨለማ ስለመለሱ?…” ሲሉ ይጠይቃሉ።

በማንኛውም መስፈረት ትህነግ የትግራይ ቀጣይ አስተዳድረ ሊሆን ይገባው እንዳልነበር የሚጠቅሱት ወገኖች አሁን የሚቀርበው የሰላማዊ ሰልፍ የተቃውሞ ጥያቄ ውስጥ ውስጡ ካኮረፉ የትህነግ ነባር ቅሪቶች ተላቆ በገሃድ በትግራይ ምርጫ እንዲካሄድ መጠየቅ መሆን እንደሚገባው ያምናሉ። በትግራይ ምርጫ እንዲካሄድና ትህነግ እስከወዲያኛው እንዲወገድ ራሳቸውን ችለው መስራት እየቻሉ ዛሬም የትህነግ አኩራፊዎች መገለገያ መሆናቸው ሌላ ዙር ሃፍረት እንደሚሆን ይጠቅሳሉ።


Exit mobile version