Site icon ETHIO12.COM

በአማራ ክልል ከ90.5 ቢሊዮን ብር በላይ ፕሮጀክቶች ቆመዋል፤ “በተፈጠረው የሰላም እጦት ክልሉ ከፍተኛ ገቢ እያጣ ነው”

“በተፈጠረው የሰላም እጦት ክልሉ ከፍተኛ ገቢ እያጣ ነው” ሲል የክልሉ ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ አስታወቀ።

በክልሉ እየታየ ያለው የሰላም እጦት በኢንቨስትመንቱ ላይ ቀጥተኛ የኾነ ተጽእኖ እያሳደረ እንደኾነ ነው የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ የገለጸው፡፡

እየታየ ያለው አለመረጋጋት ወደ ክልሉ እየገባ ያለውን እና ለመግባት በሂደት ላይ የነበረውን ኢንቨስትመንት እንደሚያስቀር ተገልጿል። ይህ ደግሞ በክልሉ ምጣኔ ሃብት ላይ ጉዳት እንደሚያስከትል ነው ቢሮው ያስገነዘበው።

የአማራ ክልል ኢንዱስትሪ እና ኢንቨስትመንት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ይሄነው ዓለም እንዳሉት ሰላም የሌለው ክልል አልሚዎችን ሊስብ አይችልም፡፡ አልሚዎች ለዳግም ኢንቨስትመንት በተለይም አዳዲስ ማሽኖችን ለማስገባት ያላቸውን ፍላጎት እንደሚቀንስም አብራርተዋል፡፡

ሰላም ከሌለ ኢንቨስትመንቱ አትራፊ ስለማይኾን አዳዲስ የሥራ እድል መፍጠር እንደሚሳነው እና ምርትም ማምረት እንደማይቻል አስገንዝበዋል፡፡

አሁን ላይ ያለው አለመረጋጋት የጥሬ እቃ ዝውውርን እየገታ በመኾኑ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ማምረት እንዳልተቻለ የሚናገሩት የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው ጉዳዩ የውጭ ምንዛሬን ለማግኘት አስቸጋሪ ነው ብለዋል፡፡

አቶ ይሄነው በሰላም መደፍረሱ ምክንያት ተጨማሪ ምርት አምርቶ በገበያው ላይ የሚታየውን የዋጋ መናር ለመቀነስ አስቸጋሪ እንዳደረገውም ነው ያስገነዘቡት፡፡

እየተፈጠረ ባለው ችግር ዋነኞቹ ተጠቂዎች ፋብሪካዎች ኾነዋል ፤ ይህም በፋብሪካዎቹ የሚሠሩ ሠራተኞችን ከሥራ እያፈናቀለ ስለመኾኑ ነው ያብራሩት፡፡ ባለፈው ጊዜ በተከሰተው አለመረጋጋት ብቻ ከ3 ሺህ በላይ የፋብሪካ ሠራተኞች ከሥራ ገበታቸው ስለመፈናቀላቸው ነው የገለጹት፡፡

በተለይም እስከ 8 የሚጠጉ የእርሻ ኢንቨስትመንቶች ላይ ጉዳት በመድረሱም ክልሉ እየተጎዳ ስለመኾኑ ነው ያስገነዘቡት፡፡

ከዘጠኝ በላይ በሚኾኑ የአበባ ልማት ዘርፎች ላይ ጉዳት በመድረሱ በዓመት ከ9 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መታጣቱንም አብራርተዋል፡፡

የክልሉን ኢኮኖሚውን ለማሳደግ በክልሉ ያለውን ችግር ለመቅረፍ እና አሁን የተጀመረውን አንጻራዊ ሰላም ለማስቀጠል የሁሉንም የክልሉን ሕዝብ ለሰላም መረባረብን ይጠይቃል። (አሚኮ)


Exit mobile version