Site icon ETHIO12.COM

ለትግራይ መርዶ ምክንያቶቹን በዝምታ? በየመንደሩ”ማን ማንን ያጽናና ?”

የትግራይ መርዶ እጅግ ለማመን የሚከብድ መረጃ፣ ለመስማት የሚያም ምስክርነት፣ ለማየት የሚያም ምስል የተደገፈ ምስክርነት እየቀረበበት ነው። ሃዘኑ መላው ትግራይን እንደ ወረሽኝ መቷል። “ካሁን በሁዋላ ጥይት መስማት አንፈልግም” ያሉ በዝተዋል። ሃዘኑ ከተማ ገጠር ሳይል ከአንድ ቤት ሶስትና ከዚያ በላይ ለጋዎች የረገፉበት መራር ሆኗል።

“በምርኮ ቆይቶ ከዛሬ ነገ ወደ ቤቱ ይመለሳል” የሚል ግምት የነጠፈባቸው እጅግ ልብ የሚነካ ምስክርነታቸውን አሰምተዋል። የሃዘኑን ግዝፈት፣ የሃዘኑንን መነሻ ምክንያት ደብቆታል? ለምን ይህን ይህል ህዝብ አለቀ? ይህ ሊሆን የገባው ነበር? በእውነት የትግራይን ህዝብ በዚህ ደረጃ የሃዘን ማቅ ውስጥ እንዲወድቅ ያደረገው ማን ነው? ማን ጦርነት ቀሰቀሰ? ለምን? እንዴት ቆመ? ለምን ቆመ? የሚሉ ጉዳዮች በወጉ ሊጤኑና ፍትህ ሊበየንባቸው ይገባል።

በመቶ ሺህ ህዝብ አስጨርሶ ሃውልት በመትከል፣ በይቅርታና በግርግር ማለፍ አስነዋሪ ነው። ቋሚዎች ይህን እንዲሆን ምክንያት በሆኑት ላይ ሁሉ ፍትህ እንዲበየን ካልተሙገቱ የሞቱትን ዳግም ቀስቅሶ የመግደል ያህል ነው። ቢቢሲ የዘገበውን ለታሪክና ለፍርድ እንዳለ አቅርበነዋል። ታሪኩ የቢቢሲ ነው።

በትግራይ ለሁለት ዓመት በተካሄደው ጦርነት ላይ ከትግራይ ኃይሎች ጋር ተሰልፈው ሲዋጉ ሕይወታቸው ያለፈ የሠራዊቱ አባላት መርዶ እና የሐዘን ሥነ ሥርዓት አስከ ሰኞ ጥቅምት 05/2016 ዓ.ም. ድረስ ለሦስት ቀናት በክልሉ ተካሂዷል።

በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በታወጀው የሐዘን ሥነ ሥርዓት ላይ የክልሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት ለጦርነቱ የተሰዉ ተዋጊዎች የመታሰቢያ መረሃ ግብር ተካሂዷል።

በመላው የትግራይ ክልል በታወጀው የሐዘን ሥነ ሥርዓት ምክንያት መደበኛ እንቅስቃሴዎች ከቅዳሜ ጀምሮ ለሦስት ቀናት ተገትተው ቆይተዋል። ዋና ከተማ መቀለ ጭር ብላ በሐዘን ሥነ ሥርዓቱ ላይ ለመሳተፍ እና ሐዘን ለመድረስ ከቦታ ቦታ የሚንቀሳቀሱ ሰዎች ብቻ ይታዩ ነበር።

ተመሳሳይ ሥነ ሥርዓት በክልሉ ውስጥ ባሉ አካባቢዎች መካሄዱን ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሽረ እንዳ ሥላሴ እና የአክሱም ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የዛሬ ዓመት በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል በተደረሰው ስምምነት በቆመው ጦርነት ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከኢትዮጵያ መንግሥትም ሆነ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በኩል የተሰጠ ይፋዊ መረጃ የለም።

በተለያዩ ጊዜያት የወጡ መረጃዎች በጦርነቱ ምክንያት የሞቱ ሰዎች በተመለከተ ከግማሽ ሚሊዮን አስከ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ቁጥሮች ሲጠቀሱ ቆይተዋል። እስካሁን ቁርጥ ያለ አሃዝ ባይኖርም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸው ይታመናል።

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ የተሰዉ ታጋዮች ቁጥር በእጃቸው እንዳለ በመግለጽ “የተሰዉ ታጋዮች ቁጥርን እንገልጻለን። ለጊዜው ግን መግለጹ አስፈላጊ ሆኖ ስላልታየን እናቆየዋለን” ማለታቸው ተዘግቧል።

ለጊዜው በጦርነቱ የተሰዉ ተዋጊዎች ቁጥር በትክክል አይታወቅ እንጂ ባለፉት ሦስት ቀናት ውስጥ በትግራይ ከተሞች ውስጥ የተነገረው መርዶ ብዛት እና የተፈጠረው ሐዘን ከባድ እንደሆነ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ሁሉም ሐዘንተኛ በመሆኑ ጦርነቱ የሚያጽናና እና የሚያበረታ የሌለበት ሁኔታ መፈጠሩን ቢቢሲ ከሽረ እና ከአክሱም ያነጋገራቸው ሐዘን ላይ ያሉ ወላጆች በተሰበረ ልብ ገልጸዋል።

“ማን ማንን ያስተዛዝናል?”

ሽረ ውስጥ በእያንዳንዱ ስፍራ ሦስት እና አራት መርዶ ነው የተነገረው የሚሉት የከተማዋ ነዋሪ “ከአንድ ቤት ሦስት የተሰዋበት ቤተሰብም አለ” በማለት ሽረ በከባድ የሐዘን ድባብ ውስጥ መሆኗን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉት የሽረ ነዋሪ፣ መርዶው ሁሉንም የከተማዋን ክፍል መዳረሱን በመጥቀስ በተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ ውስጥ የሚገኙ ተፈናቃዮች ሳይቀሩ መርዶ እየተነገራቸው በተደራራቢ ሐዘን ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተፈናቃዮች ካምፕ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ሐዘንተኞች መርዶው መራራ እንደሆነባቸዋል።

“ልጆቻችን የሞቱት እኛ ከመጠለያ እንድንወጣ ነበር፤ እኛ ግን መጠለያ ውስጥ ሆነን መርዷቸው ተነግሮናል” በማለት ይናገራሉ።

የበርካታ ጓደኞቻቸውን እና የሥራ ባልደረቦቻቸውን መርዶ የሰሙት የሽረ ነዋሪው ሐዘኑ የራሳቸውንም ቤተሰብ ክፉኛ ጎድቶታል።

“በእኔ በኩል በአድያቦ አራት የአጎቴ ልጆች፣ በእናቴ በኩልም ሰባት ድረስ ተሰውተዋል” በማለት በየቦታው የሚነገረው መርዶ እጅግ ብዙ እንደሆነ እና “በገጠር አካባቢ የሞተው ሰው ቁጥር የለውም” ይላሉ።

በጦርነቱ የሞቱ ሰዎች መርዶ የተነገራቸው ቤተሰቦች ቁጥር ከፍተኛ በመሆኑ በየቦታው ሁሉም ሐዘንተኛ ነው በማለትም “ማን ማንን ያስተዛዝናል? ዝም ብሎ ከአንዱ ቤት ወደ ሌላኛው በመሄድ ለቅሶ እየተደረሰ ነው” በማለት ያለው የሐዘን ስሜት ከባድ መሆኑን ተናግረዋል።

የምስሉ መግለጫ,በመቀለ በጦርነቱ ለተሰዉ የትግራይ ኃይሎች መታሰቢያ ዝግጅት ከተሰቀሉ ሰሌዳዎች አንዱ

“የ15 እና የ16 ዓመት ልጆች ሳይቀሩ ነው የሞቱት፤ የእነዚህ ልጆች እናቶች በጣም ያሳዝናሉ። በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ በከባድ ሐዘን ውስጥ ያሉትን ወላጆችን ‘እግዚአብሔር ያጽናችሁ’ ለማለት ፊታቸውን ማየት እንኳን ይከብዳል። አንዳንዶቹም ‘ሳትነግሩኝ ልጄ ይመጣል ብዬ ብጠብቅ ይሻለኝ ነበር’ ይላሉ።”

በዚህ ወቅት የልጃቸውን መርዶ ለመስማት ተዘጋጅተው እየጠበቁ ያሉ ቤተሰቦች በድንገት መምጣታቸውን የሚገልጹት የሽረ ነዋሪው፣ በዚህ የመርዶ እና የሐዘን ወቅት አንዳንድ ወላጆች ጦርነቱ ከፈጠረው ሰቆቃ ባሻገር ልጆቻቸው ድንገት ሊመጡ ይችላሉ ብለው እንዲጠብቁ እንዳደረጋቸው ይናገራሉ።

“የልጆቻቸው መርዶ የተነገራቸው አንዳንድ ወላጆች ምናልባት በጦርነቱ ወቅት በኤርትራ፣ በጦላይ፣ በአዋሽ ወይም በሌላ ቦታ በምርኮ ላይ ይሆናሉ ብለው የሚጠብቁም አሉ። መርዶ ብትነግሩኝም ልጄ አልተሰዋም የሚሉም አሉ።”

በሁለት ዓመቱ ጦርነት ውስጥ ሕዝቡ ያለፈበት አስቸጋሪ ሁኔታ እና የልጆቹ መርዶ ወላጆችን በእጅጉ ጎድቷቸዋል የሚሉት የሽረው ነዋሪ፣ በአብዛኛው “ሐዘን መልሶ ሐዘንን ነው የሚወልደው” በማለት ለመጽናናት እየጣረ ነው ይላሉ።

ነገር ግን ከዚህ በፊት በነበሩ ጦርነቶች የተሰዉትን ሰዎች ቁጥር በማስታወስ የአሁኑ የመርዶ ብዛት ከፍተኛ መሆኑን ይናገራሉ።

“የአሁኑ ከባድ ነው! ትዝ ይለኛል፤ በ80ዎቹ መርዶ ሲነገር ቁጥሩ ጥቂት ነበር። በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ወቅትም እንደዚያው። አሁን ግን ይዘገንናል፤ ታይቶ አይታወቅም።”

ለእንዲህ ያለው የሞት መጠን ከፍተኛ መሆን ምክንያቱ እሳቸው እንደሚገምቱት በጦርነቱ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋሉት እንደ ድሮን ያሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ያሳደሩት ጫና ሊሆን ይችላል ብለው ያስባሉ።

“ሁሉም የሚመጣው የራሱን ሐዘን ይዞ ነው”

በአክሱምም የለውም ሁኔታ ተመሳሳይ እንደሆነ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የታሪካዊቷ ከተማ ነዋሪ፣ ከ15 ዓመት አንስቶ ያሉ ልጆች ተሰውተዋል፣ ሐዘን እያንዳንዱ ቤት ገብቷል። ገጠር ይሁን ከተማ ወላጅ እና ቤተሰብ ከባድ ሐዘን እና ጭንቀት ላይ ነው።

“. . .ይህን የሚያክል ጥፋት አጋጥሞናል የሚል ግምት አልነበረንም። አሁን ግን ለመናገርም የሚያስጨንቅ ከባድ ሐዘን ነው የገጠመን፤ እኔም የልጄ መርዶ ተነግሮኝ ሐዘን ላይ ነኝ። በዙሪያችን ብዙ የሚያስጨንቅ ሁኔታ ነው ያለው።”

በአሁኑ ወቅት እራሳቸውን ጨምሮ “ሁሉም ሐዘንተኛ ሆኖ የሚያጽናና ሰው የለም” የሚሉት እኚህ ወላጅ፤ ለቅሶ ለመድረስ “ሁሉም የሚመጣው የራሱን ሐዘን ይዞ ነው። ሁላችንም አንድ ላይ ለቅሶ ላይ ነን” ብለዋል።

ልጆቻቸው አስከሬን የት እንዳረፈ ያላወቁ ወላጆች የእራሳቸውን ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን የሚገልጹት የአክሱም ከተማ ነዋሪው ሐዘንተኛ አባት፣ ሐዘኑ በሁሉም ሰው ቤት በመግባቱ መጽናናት ከባድ መሆኑን ይናገራሉ።

በሰላሙ ጊዜ በሕዝቡ ባሕል መሠረት ሐዘን የገጠመው ቤተሰብ በዙሪያው ባሉ ሰዎች እንዲጽናና እና እንዲበረታ ይደረጋል። አሁን ግን ሁሉም ሐዘንተኛ ሆኖ ወደ ለቅሶ ቤት ስለሚሄድ “ሁሉም ሰው ወደ ለቅሶ ቤት ሲሄድ የሚያለቅሰው ላጣው ልጁ ነው እንጂ ሊደርሰው ለሄደበት ሰው አይደለም” በማለት ያለውን ከባድ የሐዘን ድባብ ገልጸውታል።

ሐዘኑ በፈጠረባቸው ጭንቀት ምክንያት መድኃኒት አስከመውሰድ ደርሰው የነበሩት አባት የተፈናቀሉት ወደቀያቸው እንዲመለሱ ተደርጎ “አሁን ሰላም ነው የምንፈልገው፤ ጾማችንን እያደርንም ቢሆን የመሳርያ ድምጽ መስማት አንፈልግም” በማለት የቀሩት ልጆቻቸውን በሰላም እያስተማሩ ማሳደግ እንደሚፈለጉ ተናግረዋል።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ ፕሪቶሪያ ላይ በተፈረመው የሰላም ስምምነት የቆመው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች ተስፋፍቶ እንደነበረ ይታወቃል።

በጦርነቱ ከሞቱ ተዋጊዎች በተጨማሪ በሁሉም ወገኖች ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰላማዊ ሰዎች ከመገደላቸው በተጨማሪ፣ ግፍ እና ሰቆቃ እንደተፈጸመ በመብት ተቆርቋሪዎች ወጡ ሪፖርቶች አመልክተዋል።

አሁን በትግራይ ኃይሎች በኩል በጦርነቱ ተሳታፊ ሆነው ስለሞቱ ተዋጊዎች መርዶ ለቤተሰቦቻቸው መንገር እና ይፋዊ የመታሰቢያ መረሃ ግብር ይካሄድ እንጂ፣ በጦርነቱ ተሳታፊ በነበሩት በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ በኤርትራ ሠራዊት እና በክልል ኃይሎች አባላት ላይ ስለደረሰው ሞት አስካሁን የተባለ ነገር የለም።


Exit mobile version