ETHIO12.COM

በትግራይ ከ”መርዶ” በሁዋላ ምን እየሆነ ነው? አጀንዳውስ የማን ነው? መጨረሻውስ ምንድን ነው?

” ትህነጎች ቢያይዋቸው ቢያዩዋቸው ሁሉም አንድ ናቸው” የሚለው የትህነግ አፍቃሪዎች ዜማ መልኩን እየቀየረ ከሄደ ቆቷል። በተለይም ከለውጡ በሁዋላ ባይሰፋም የአመለካከትና የአሰላለፍ ልዩነት መታየት ጀመሮ እንደነበር ብልጭ ድርግም የሚሉ አስተያየቶች አስረጂዎች ነበሩ። ይህ ልዩነት አሁን ላይ አድጎ የቀድሞው የድርጅቱ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ በህንፍሽፍሽ ዘመን እንዳይነሳ አድርገው ከቀበሩት የአመለካከትና አሰላለፍ ልዩነት ጋር የሚወዳደር እንደሆነ እየተሰማ ነው። አቶ ጌታቸው “በትግራይ ህግ የማስከበሩ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ማለታቸው የዚሁ መመሳሰል ማሳያ እንደሆነም እየተገለጸ ነው።

” መንግስት የማያውቀው ፤ የህዝብ ሃብት በማባከን ከቀበሌ እስከ ዞን ስብሰባ መጥራት ምክንያቱ ግልፅ አይደለም ” ሲሉ አቶ ጌታቸው ረዳ መግልጽ ግብረ ምላሽ የሰጡበት ጉዳይ ዶክተር ደብረጽዮን የሚመሩት የትግራይ ህዝብ ነጻ አውጪ ግንባር ትህነግ በህጋዊ የድርጅቱ ማህተምና ማህበራዊ ሚዲያ ካድሬዎችን ለስብሰባ ወደ መቀለ እንዲመጡ ይፋዊ ጥሪ ማቅረቡን ተከትሎ ነው።

ሶስት ጊዜ ሰፊ ማጥቃት ፈጽሞ፣ አማራና አፋርን ወሮና ደብረ ብርሃን መዳረሻ ላይ ሆኖ ለመንግስት ባለስልጣናትና ለአገር መከላከያ እጅ የመስጪያ ቀን ሲቆጥር የነበረው ትህነግ፣ በጦርነት ተሸንፎ ለሰላም አማራጭ ተገዝቶ ስምምነት መፈረሙ አይዘነጋም።

ትጥቅ ለመፍታት፣ ለማዕከላዊ መንግስት ዕውቅና ሰጥቶ ዳግም ምርጫ እንደሚያደርግ፣ የገነባውን ሃይል ለማፍረስና መሳሪያውን ለማስረከብ ቃል የገባው ትህነግ ይህን ስምምነት በማድረጉ በከፍተኛ ደረጃ ተቃውሞ ተነስቶበትም ነበር። ከሰላም ስምምነቱ በሁዋላ በተለይም የጊዚያዊ መንግስት ተብሎ የተሰየመውንና ዶክተር ደብረጽዮንን በቀድሞ መንበራቸው እንዲቆዩ ያደረገውን አዲሱን አሰላለፍ መንግስት እንደማይቀበለው ይፋ ካደርገ በሁዋል ልዩነቱ ግሟል።

በጦርነቱ ወቅት የትግራይ መከላከያ ሃይል የሚባለውን ታጣቂ ሲመሩ የነበሩት ሌተናል ጀነራል ጻድቃንና ታደሰ ወረደ፣ በጦርነቱ ዝግጅት ወቅት ከአቶ ጌታቸው ረዳና ሌሎች ጋር በቅርብ ለመምከር አጋጣሚ ማግኘታቸው አሁን ላለው የሃይል አሰላለፍ እንደ መልካም አጋጣሚ እንደሚቆጠር አካሄዱን የሚረዱ አስተያየት ሲሰጡ ይሰማል። ቆየት ብሎ አቶ ጌታቸውን የክልሉ መሪ፣ ተገለው የነበሩትና ኢንቨስተር ሆነው የነበሩት ሌተናል ጻድቃንና ታደሰ ወረደ የአቶ ጌታቸው አካል መሆናቸው ሲሰጥ የነበረውን አዲሱ አሰላለፍ ትክክል መሆኑን አሳይቷል።

ይህ አቶ ጌታቸው የሚመሩት ወገን ክልሉን በጊዚያዊነት መምራት ከጀመረ በሁዋላ ድርጅቱ በአሳብና በግብር ማፈንገጡን የሚያሳዩ በርካታ ጉዳዮችን ሲፈጽም ቆይቷል። ይኸው ፈራ ተባ፣ ወጣ ገባ ሲል የነበረው የትህነግ መሪዎች እንቅስቃሴ በክልሉ በውል ያልተገለጸ የሰው ህይወት ማለፉ ተመልክቶ መረዶ ማርዳት ከተጀመረና ” የሃዘን ጊዜ” ተብሎ ከታወጀ በሁዋላ ይፋዊ የካድሬውች ስብሰባ ጠርቷል። ይህጀው የዞናና የበታች አመራሮችን የጠራው ስብሰባ ዓላማውና አጀንዳው በግልጽ ባይነገረም በክልሉ አመራር ላይ ኩዴታ መሰል ወይም የበታች አደረጃጀቱ እንዲአፈነግጥ የሚያደርግ ስምሪት ለማከናወን እንደሆነ ተሰምቷል።

ይህን የከትሎ “በትግራይ የተጀመረው ህግ የማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ሲሉ የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው በጽህፈት ቤታቸው መግለጫ ሰጥተዋል። አቶ ጌታቸው በአሁኑ ሰዓት የትግራይ ክልል የማያስተዳድረውን ምዕራብ ትግራይን ጨምሮ የስድስት ዞኖችን የሕዝብ ንቅናቄ ጽህፈት ቤት ሃላፊዎችን በድብዳቤ ማሰናበታቸውን ተከትሎ ነው የህግ ማስከበሩ እንደሚቀጥል ያስታወቁት።

ፕረዚደንቱ ዛሬ ጥቅምት 16 /2016 ዓ.ም በፅህፈት ቤታቸው በኩል ባወጡት መግለጫ ፤ ” የተሰው ታጋዮች መርዶ በተነገረበት ማግስት ያሉ የመንግስት ስራዎች ወደ ጎን በመተው መንግስት የማያውቀው የህዝብ ሃብት በማባከን ከጥቅምት 14/2016 ዓ.ም ጀምሮ ከቀበሌ እስከ ዞን ስብሰባ መጥራት ምክንያቱ ግልፅ አይደለም ” ብለዋል።

እሳቸው በፖለቲካ ቋንቋ “ምክንያቱ ግልጽ አይደለም” ይበሉ እንጂ ምክንያቱ እሳቸውንና እሳቸው የሚመሩትን ቡድን ለማስወገድ እንቅስቃሴ ቀደም ሲል መጀመሩ የሚታወስ ነው። ገና ከጅምሩ በክልሉ የጊዚያዊ አስተዳደር ሳይሰየም ለሪፖርተር ጋዜጣ ዶክተር ደብረ ጽዮን የሚመሩት የካቢኔ ቡድን መመረጡን ከነሙሉ ስም ዝርዝር በማሰራጨት የጀመሩት ዘመቻ ያልተሳካላቸው እነዚህ ወገኖች፣ የአቶ ጌታቸውን የህግ ይከበራል ማስጠንቀቂያ ሰምተው ከድርጊታቸው እንደሚቆጠቡ እርግጠኛ መሆን እንደማይቻል በስፋት እየተሰማ ነው።

በጦርነት ሰብአዊና ቁሳዊ ጥፋቱ ያየለባት ትግራይን እንዲመሩ በጊዜያዊነት የተሰየሙት አቶ ጌታቸው ” … በአማራ ክልል የሚካሄደው ግጭትና ጦርነት ልዩ ተልዕኮ ባላቸው ሃይሎች የተጠለፈ ነው” ሲሉ መግለጫ በሰጡበት ወቅት “አጋጣሚውን ተጠቅመን ወልቃይትን በሃይል እናስመልስ” የሚሉ ሃይሎች መኖራቸውንም አክለው ነበር። እሳቸው በአፈ ቀላጤነት የመሩት ጦርነት ከከፍተኛ ክስረት በሁዋላ በጠርጰዛ ዙሪያ ካለቀና ወላዶችም በይፋ መርዶ እርም እንዲያወጡ መደረጉን ተከትሎ በቅጽበት ክልሉን ወደ ሌላ ትርምስ የሚወስድ አለመግባባት መሰማቱ “ትግራይ ወዴት እየሄደች ነው? ምንስ ነው የሚፈለገው? መጨረሻውስ ምንድን ነው? ለትግራይ ህዝብስ የሚያስቡ መሪዎች የሚነሱት መቼ ነው? የዚህ ህዝብ ስቃይስ መቼ ነው የሚያቆመው?” የሚሉ የምሬት ጥያቄዎች እየተሰነዘሩ ነው።

አማራን፣ አፋርን፣ ኤርትራን ዙሪያ ጠላት የማድረግና የትግራይ ህዝብ በጠላት እንደተከበበ በማሰብ ከትህነግ ውጭ ሌላ የሚያምነውና የሚከላከለው ሃይል እንደሌለው አስመስለው ሲገዙት የኖሩት ፖለቲከኞች በመቶ ሺህ የትግራይ ተወላጆች ለሞቱበት ምክንያት አልባ ጦርነት ተጠያቂ መሆን ሲገባቸው ዳግም ለስልጣን ብለው ክልሉን ለማተረማመስ መነሳታቸው ሃዘን ፈጥሯል።

ይደረጋል የተባለው ስብሰባ በይፋ መቅረቱ፣ ወይም መካሄዱ በሚታውቅ የመንግስት ወይም የፓርቲ ልሳን ባይገለጽም፣ የሰማእት ሃውልት በሚባለው አካባቢ መጠነኛ ሰዎች የሚታዩበት ምስል ተሰራጭቷል። ከዛም ጎን ለጎን ስብሰባ እንዳልተሳካ የሚያሳዩ መረጃዎችም ተሰምተዋል።

ጸጋዬ ገብረመድህን “ሰበር ዜና”ብለው በማህበራዊ ገጻቸው ” አ፤እም ገብረዋህድና ደብረጽዩን ከካድሬዎች ጋር ሊያደርጉት የነበረው ስብሰባ አልተሳካም” የሚል ጽሁፍ አጋርተዋል። አያይዘውም ሁለቱ ዋና አስተባባሪዎች ” እንደማንታሰር ቃል ይገባልንና ስብሰባውን እናስቀረዋለን” ሲሉ በአገላጋዮች በኩል መጠየቃቸውም ተመልክቷል።

አሁን ላይ የነደብረጽዮን ውገን የታጣቂ ሃይሉ ውስጥ ሚና ስለሌላቸው ብዙም ችግር እንደማይፈጥሩ የሚገልጹ፣ በዚህ ምክንያት ከዞን ጀምሮ እስከ ታችኛው እርከን ድረስ መዋቅሩን ወደ ራሳቸው ለመገልበጥ የትህነግን ድርጅታዊ መዋቅር በመጠቀም ስራ ሲሰሩ መቆየታቸው ታውቆባቸዋል። ብዙም ሚስጢር አልነበረም። ቲክቨሃ የአቶ ጌታቸውን መግለጫ እንደሚከተለው አቅርቦታል።

የሰብሰባው ዋነኛ ተሳታፊ በየደረጃው ያሉ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊዎች ሲሆኑ ፣ መንግስትና ህዝብ የሰጣቸው ሃላፊነት ወደ ጎን በመተው በራሳቸው መንገድ በሄዱ ሃላፊዎች እርምጃ ተወስዷል፤ የተጀመረውም ህግ የማስከበር እርምጃ ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ አረጋግጠዋል።

እነዚህ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊዎች ህዝብ በማስተባበር ያጋጠመን ችግር መፍታት ትተው ወደ መቐለ በመምጣት መንግሰት የማያውቀው ስብሰባ ማካሄድ አላማው ግልፅ እንዳልሆነ ፕረዚደንት ጌታቸው ረዳ ጨምረው ገልፀዋል።

ለስብሰባው በተደረገው ጥሪ ” በአንዳንዱ አከባቢ ስንቃቸውን ይዘው እንዲመጡ ” መነገሩን የገለፁት አቶ ጌታቸው ፤ የመንግስት አሰራር ጥሰው በተገኙ ሃላፊዎች በተወሰደው እርምጃ ምክንያት የአመራር ክፍት እንዳይፈጠር ማስተካከያ እርምርጃ እየተወሰደ ነው ብለዋል።

” አሁን ያጋጠመው ችግር ለማስተካከል ሰራዊቱ ፣ ድርጅቱ ህዝቡ በማንቀሳቀስ ይሰራል ” ያሉት ፕረዚደንቱ ” ሁሉም ነገር በህግና አሰራር ብቻ መከናወን ይገባል ” ብለዋል።

” በየደረጃው የሚገኝ የመንግስት አካል ህዝብና መንግስት የሰጠው ሃላፊነት በአግባቡ በመወጣት ህዝብ የሚጠቅም ስራ መስራት አለበት ” ያሉት አቶ ጌታቸው ረዳ ” ይህንን ለማደናቀፍ በሚሞክር ማንኛውም አካል ጥንካራ ህግ የማስከበር እርምጃ ይወሰዳል ” ማለታቸው የጊዜያዊ አስተዳደሩም ፕረዚደንት ፅህፈት ቤት መግለጫ በመጥቀስ የቲክቫህ ኢትዮጵያ የመቐለ ቤተሰብ ዘግቧል።

ፕረዚደንት ጌታቸው ረዳ ጥቅምት 15 /2016 ዓ.ም ጊዚያዊ አስተዳደሩ በማያውቀው እንቅስቃሴ ተገኝተዋል ያሉዋቸውን 6 የክልሉ ዞኖች የህዝብ ግንኙነት ሃላፊዎች በደብዳቤ ከስራ አስነብተዋቸዋል።

Exit mobile version