Site icon ETHIO12.COM

በአማራና በትግራይ ክልል ለሚገኙ አወዛጋቢ ሥፍራዎች መንግስት የመፍቻ ቁልፍ ማበጀቱን አብይ አህመድ አስታውቁ

“በአማራና በትግራይ ክልል መካከል ጥያቄ የሚነሳባቸው ቦታዎችን በሚመለከት ህግን የተከተለ፣ ዘላቂ ሰላምን ባከበረና የህዝብን አብሮነት ያስቀደመ የመፍትሄ አቅጣጫ እንከተል ብለን እየሰራን ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የስራ ዘመን 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት እየተካሄደ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከምክር ቤት በቀረቡላቸው ጥያቄዎች ላይ ማብራሪያ ሲሰጡ እንደገለጹት መንግስት በሁለቱ ክልሎች መካከል ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎች ህግን በተከተለ፣ ዘላቂ ሰላምን ባከበረና የህዝብን አብሮነት ያስቀደመ መፍትሄ ለማምጣት እየሰራ ይገኛል።

የኛ መፍትሄ ይተግበር አላልንም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዘላቂ ሰላምና ለህዝቦች አብሮነት የሚሆን መፍትሄ ለሚያመጡ አካላትም በራችን ክፍት ነው ሲሉ አስረድተዋል።

የመንግስት ፍላጎት በሁለቱም ክልሎች መካከል ዘላቂ ሰላም ሰፍኖ ማየት መሆኑን ገልጸው የህዝቡ ፍላጎትም ከዚሁ የተለየ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

አብይ አህመድ ሪፈረንደም አማራጭ መሆኑንንም አመላክተዋል። ህዝብ በድምጹ የሚፈልገውን እንዲወስን የቀረበውን አማራጭ ለሚገፉ ” የህዝብ ውሳኔ ካልተከበረ የማን ውሳኔ ሊከበር ነው” የሚል ምላሽ የማይቀርብበት ጥያቄ ሲቀርብ መቆየቱ ይታወሳል። ዋናው ጉዳይ ድምጽ አሰጣጡን በወጉ ማካሄድና ተአማኒ እንዲሆን ማድረጉ ላይ እንጂ መፍትሄነቱን ማጣጣል በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይ እንደማያደርግ ባለሙያዎች ሲገልጹ ቆይተዋል።

በ4ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ እንደራሴዎቹ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄዎችን አንስተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው በአማራ ክልል ስላለው አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ትግበራ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ዋነኛ ዓላማው ሰላምና ደኅንነትን ማምጣት መኾኑን በጥቅሉ አንስተዋል።

አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀው የክልሉ መንግሥት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት መኾኑንም ተናግረዋል፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አንጻራዊ ሰላም አምጥቷል፤ የክልሉን መንግሥት ከመፍረስ ታድጓል፤ ነገር ግን የተሟላ ሰላም እንዲመጣ ተጨማሪ ሥራ ያስፈልጋል ነው ያሉት፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው ለሕዝባችን የገባነውን ቃል ለመፈጸም እንሠራለንም ብለዋል፡፡ ሰላም እንዲሰፍን፣ ልማት እንዲፋጠን እና ድህነት እንዲጠፋ ሕዝቡ ይፈልጋል፤ ዲሞክራሲ እንዲገነባ ይፈልጋል፤ ሕዝብ ማለት ቀጣይነት ነው፣ ለልጆቹ የተሻለ ነገን ያስባል ብለዋል፡፡

የሕዝብን ጥያቄ እናውቃለን፣ ለሕዝባችንም ቅርብ ነን፣ የሕዝቡን ፍላጎት እና ጥያቄ ለመመለስ በጋራ መሥራት ይገባል ነው ያሉት፡፡ ለአንደኛው መልስ የሚኾነው ለሌላኛው ጥያቄ ስለሚኾን የሕዝብን ጥያቄ በስክነት እና በትክክል ማረጋገጥ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ መንግሥታቸው ድፍረት የሚያስፈልጋቸውን ጥያቄዎች በመድፈር መመለስ መጀመሩንም ገልጸዋል፡፡

“በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የችግር ትንታኔ የስሜት እና የሤራ ትንታኔ ይበዛዋል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ.ር) ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

በምላሻቸውም ጥያቄዎችን ከሥረ መሠረቱ መገንዘብ እና መርመር ይገባል ብለዋል፡፡ ችገሮችን እኩል የሞንገነዘባቸው እና የሞንረዳቸው ከሆነ ጉዟችን ወደ መፍትሔ ይኾናል ነው ያሉት፡፡ በችግሮች ላይ መግባባት ካልቻልን ላይ መፍትሔ ላይ አንደርስም ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የችግር ትንታኔ የስሜት እና የሤራ ትንታኔ እንደሚበዛውም ገልጸዋል፡፡ የሴራ እና የስሜት ትንታኔዎች ችግሩን እንዳንረዳ እና ከመፍትሔው እንድንርቅ ያደርገናልም ብለዋል፡፡

ብልጽግና የሚመራው መንግሥት የተለያዩ ስያሜዎች ይሰጡታል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሄ የኾነው የስሜትና የሤራ ትንታኔ በመኖራቸው ነው ብለዋል፡፡ ለየትኛውም ሴራ መጠቀሚያ እንደማይኾኑም አስታውቀዋል፡፡

የሤራና እና የስሜት ትንታኔዎች የጋራ ግንዛቤ እና መግባባት እንዳይኖር እንደሚያደርግም ገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በሁሉም ጫፍ ያሉ ልጆቿ በእኩልነት የሚኖሩባት፣ ሁሉም የሚከበሩባት፣ ያማረች ሀገር እንድትፈጠር እንሠራለንም ነው ያሉት፡፡

በመንግሥታቸው ሕብረ ብሔራዊ አንድነት መፍጠር እና አካታች የዲሞክራሲ ሥርዓት መገንባት ትኩረት እንደተሰጠውም ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ መሠረት የእያንዳንዱ ዜጋ ድምር ውጤት ነውም ብለዋል፡፡ በጋራ የመበልጸግ እና የመኖር እምነት እንዳላቸውም አመላክተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አካታችና ሁሉን ያቀፈ ፓርቲ ኖሮ እንደማያውቅም አንስተዋል፡፡

ከተለመዱ ነገሮች በመውጣት ሰላምን ማስቀደም፣ ችግሮችን መፍታት፣ ደህነትን ማስቀረት እና ሰላምን ማምጣት ይገባልም ብለዋል፡፡ የተሻለ ነገር ለማምጣት ሃሳብ ማመንጨት እና መተግበር እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንደኛው ችግር አባባሽ ትርክት መኾኑንም ተናግረዋል፡፡

ነጠላ፣ የተዛባ እና አፍራሽ ትርክት ሀገር እንደማይገነባም ገልጸዋል፡፡ ታላቅ እና ሀገራዊ ትርክት ይሰበስባል፣ ከዚያ የሚቃረነው ሀገር ይበትናል፤ ስንለያይ አቅማችን ያንሳል እንጎዳለን ነው ያሉት፡፡

ዋልታ ረገጥ እሳቤዎችን ማስፋት ጎጂ መኾናቸውንም አንስዋል፡፡ ዋልታ ከረገጠ እሳቤ ሚዛን ወደሚደፋ እሳቤ መምጣት ይገባልም ብለዋል፡፡

አላካኪነት ሌላው ችግር እንደኾነ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማላከክ ለውጥ አይመጣም፣ ለውጥ የሚመጣው ኀላፊነት በመውሰድ መኾኑን አንስዋል፡፡

በጊዜ መታከክ እና አቅላይነት ሌላው ችግር መኾኑንም ገልጸዋል፡፡ እነዚህን ጉዳዮች ማስተካከል ለሀገር አንድነት እንደሚጠቅምም ተናግረዋል፡፡ የጋራ የሆነ ነገር መፍጠር ካልቻልን ለልጆቻችን የሚተርፍ ችግር እናወርሳንም ብለዋል፡፡

“ለኢትዮጵያውያን የምመክረው በጥይት ከመገዳደል፤ በሀሳብ መገዳደር ይሻላል” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)

ባሕር ዳር: ኅዳር 4/2016 ዓ.ም (አሚኮ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 4ኛ መደበኛ ስብሰባ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ እየሰጡ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ግጭቶች መኖራቸው ገልጸዋል፡፡ በክልሎች ያለው ግጭት ሰው የሚገድሉ፣ ንብረት የሚያወድሙ መኾናቸውንም ተናግረዋል፡፡

የእኛ መሻት ሰላም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ እስካሁን ድረስ በእኛ መሻት ጦርነት አልተካሄድም ነው ያሉት፡፡ ሁሉም ግጭቶች እና ጦርነቶች የሚከሰቱት በሌሎች ፍላጎት ነው ብለዋል፡፡

እኛ በቀደድነው ክፍተት ሌሎች ኃይሎች እንዳይገቡ ስለምንፈልግ እና ኢትዮጵያን ስለማናሳንሳት ጦርነት መክፈት አንፈልግም ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ሳናሳንሳት በጋራ ብንሠራባት ታላቅ ሀገር ናት ብለዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያውያን ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር በጋራ ከመኖር ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌላቸውም አመላክተዋል፡፡ አሁን በሚደረጉ ግራና ቀኝ ባሉ ውጊያዎች መንግሥትን ማሸነፍ አይቻልም ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በሕልውናዋ የሚመጡባትን ልማቶቿን አዘግይታም ቢሆን ትታገላለች ነው ያሉት፡፡ለኢትዮጵያውያን የምመክረው በጥይት ከመገዳደል፣ በሀሳብ መገዳደር ይሻላል ብለዋል፡፡

ጥይት ዶላር መኾኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገር በኢኮኖሚ የሚጎዳ፣ ሰው የሚገድልና ወደፊትም ቀና እንዳንል የሚያደርግ መኾኑንም ገልጸዋል፡፡

ግጭትን እና ጦርነትን በመተው በውይይት ችግሮችን መፍታት ይገባል ነው ያሉት፡፡ ሀሳባችን የጥላቻ ግንብ አፍርሰን የይቅርታ ድልድይ እንገንባ ነው፣ የመገዳደሉን ሰይፍ እንተውም ብለዋል፡፡ ፍቅር፣ አብሮነት እና በጋራ ሰላምና ልማትን ማምጣት ይገባል ነው ያሉት፡፡

አንደኛውን የሕዝብ ተቆርቋሪ ሌላኛውን እንደማይቆረቆር መቁጠር አይገባም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄዎችን በሰላማዊ መንገድ መፍታት ይገባል ነው ያሉት፡፡ ጠመንጃን ማውረድ እና ሃሳብ መንጃውን መያዝ የተሻለ ጥቅም እንዳለውም ተናግረዋል፡፡

በማንኛውም ሰዓት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመወያየት ዝግጁ መኾናቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በሴራ አናምንም ብለዋል በምላሻቸው፡፡

ከተለያዩ ሚዲያዎች ተሰባስቦ የቀረበ


Exit mobile version