Site icon ETHIO12.COM

የአዲስ አበባ አስተዳደር ከብሄር ተኮር አሰራሩ እንዲላቀቅ ኢዜማ ጠየቀ፤ የአሰራር ማሻሻያው ከብዥታና ስጋት ነጻ እንዲሆን አሳሰበ

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ ፤ የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ሊሰጥ በዝግጅት ላይ ስላለው የመንግሥት ሰራተኞች የብቃት ምዘና ፈተና ጉዳይ ግልጽ ማብራሪያ እንዲሰጥ ጠይቋል።

ፓርቲው ፤ በመርኅ ደረጃ ምዘናው ለማኅበረሰቡ የሚሰጡ አገልግሎቶች በተሻለ ብቃት እና ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በተላበሰ ሥነምግባር እንዲሠጡ ታላሚ ያደረገ ከሆነ ለአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ጥራት ያለው ቀልጣፋ አገልግሎት ለማግኘት የሚረዳ መሆኑን ለሠራተኞች ደግሞ ሁልጊዜም ተወዳዳሪ የሚያደርግ አሠራር ስለሚሆን የሚበረታታ ተግባር እንደሆነ ገልጿል። ሙሉ መግለጫው እንደሚከተለው ቀርቧል።

የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር በጉዳዩ ላይ ግልጽ ማብራሪያ እንዲሰጥ እንጠይቃለን!

የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳደር ፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ የከተማዋ ነዋሪዎች በአገልግሎት ላይ እየተባባሰ የመጣውን ቅሬታ ለመቅረፍ ይረዳ ዘንድ የከተማዋ የመንግሥት ሠራተኞች ከታህሣሥ 12/2016 ዓ.ም. ጀምሮ ለምዘና እንደሚቀመጡ ቀደም ባሉት ጥቂት ቀናት የገለፀ ሲሆን አስተዳደር መሥሪያ ቤቱ በጠቀሰው ዕለትም ብዙ ተገልጋይ የሚያስተናግዱ፣ ብልሹ አሰራር በከፍተኛ ሁኔታ የሚታይባቸው እና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ መጓደል ያለባቸው ሲል የጠቀሳቸው 16 ተቋማት ላይ ከ 14,000 በላይ ሠራተኞች ለፈተና እንደሚያስቀመጥ ገልጾ ነበረ። ሆኖም ምዘናውን እንዲያከናውኑ ኃላፊነት የተሰጣቸው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና የኮተቤ ትምሕርት ዩኒቨርሲቲ ፈተናው ሊደረግ በነበረት መጨረሻ ሰዓት ባጋጠመ የቴክኒክ ችግር ፈተናው ወደሌላ ጊዜ እንዲሸጋገር መደርጉን ከይቅርታ ጋር አያይዘው ገልጸዋል።

በመርኅ ደረጃ ምዘናው ለማኅበረሰቡ የሚሰጡ አገልግሎቶች በተሻለ ብቃት እና ኢትዮጵያዊ ጨዋነት በተላበሰ ሥነምግባር እንዲሠጡ ታላሚ ያደረገ ከሆነ ለአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ጥራት ያለው ቀልጣፋ አገልግሎት ለማግኘት የሚረዳ ሲሆን ለሠራተኞች ደግሞ ሁልጊዜም ተወዳዳሪ የሚያደርግ አሠራር በመሆኑ የሚበረታታ ተግባር ነው ብሎ ፓርቲያችን ያምናል።

እንደሚታወቀው በነዚህ አስተዳደር መ/ቤቶች የተገልጋይን ስም እንኳ በቅጡ በሠነዶች ላይ ማስፈር የማይችሉ፣ ፈጣን አገልግሎት እንዲሠጡ ታስበው አገልግሎት ላይ የዋሉ ቴክኖሎጂዎችን በአግባቡ መጠቀም የማይችሉ፣ ከሥነምግባር ያፈነገጡ እና በሌብነት የተተበተቡ ሠራተኞችን መመልከት የተለመደ ሆኗል። ሌላው ቀርቶ አንድ ዜጋ በነፃነት ለመንቀሣቀስ የሚያስፈልገውን የነዋሪነት መታወቂያ ለማግኘት እንኳ ሲጉላላ እና እጅ መንሻ ሲጠየቅ ይስተዋላል። ከዚህ አንጻር የአገልግሎት ጥራትን ለማስፈን የምዘና ጅምሩ የሚበረታታ መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን።

ሆኖም በተደጋጋሚ እንደገለጽነው እነዚህን አስተዳደር መሥሪያ ቤቶች የሚመሩት የገዢው ፓርቲ አመራሮችም ሆነ ገዢው ፓርቲ እንደተቋም ለብሄርተኝነት ባላቸው የተዛባ ውግንና በተደጋጋሚ በሚያደርጓቸው አግላይ የአደባባይ ንግግሮች እና አሠራሮች ምክንያት እያንዳንዱ በነዚህ አካላት የሚደረግ እንቅስቃሴ እና ውሳኔ በማኅበረሰቡ በጥርጣሬ የሚታይ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

በመሆኑም አስተዳደሩ “የብቃት ደረጃን ለማረጋገጥ እና አገልግሎትን ለማሻሻል የሚደረጉ እርምጃዎች ናቸው” ቢልም ከፍ ብሎ በተጠቀሰው ምክንያት በጥርጣሬ እንዲታዩ መሆናቸውን መገንዘብና ተገቢውን ማብራሪያ በወቅቱ መስጠት ዜጎችን ከስጋት እና ከውዥንብር ያድናል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በአንድ መሥርያ ቤት ውስጥ የሚገኙ ዳይሬክተሮች እና የቡድን መሪዎች ከአንድ ብሔር ከ 40 % በላይ ሊበልጡ እንደማይገባ መገለጹ አገልግሎት የሚሰጡ መሥሪያ ቤቶች ውሰጥ ለምዘና ሊቀመጥ የሚገባውን ዋነኛውና መሠረታዊ የሆነውን ከትምህርት ዝግጅት እና ከሥራ ልምድ የሚመነጩ የችሎታና የብቃት ጉዳይ አሳንሶ እንዳይመለከት ጥብቅ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል እንላለን፡፡

ኢዜማ በፓለቲካ ፕሮግራሙ እንደገለጸው ከቀዳሚ መርኆዎቹ አንዱ ኢትዮጵያውያን በብዝኀነት የተገመድን እና የተዋብን ሕዝብ መሆናችንን የሚያምን ሲሆን ተቋማቶቻችንም ለሁሉም ዜጎች እኩል እድል የሚሰጡ መሆን እንዳለባቸው እንገነዘባለን።

ይህ ሲባል ግን የብሔር ኮታን በዚህ ደረጃ ከፍተኛ መስፈርት አድርገው እያዩ በኃላፊነት ቦታ ላይ መደልደል አገልግሎትን ማቀላጠፍም ሆነ ማኅበራዊ ፍትህን ማስፈን የማይችል አሠራር በመሆኑ በጽኑ የሚያወግዘው እና የሚታገለው ተግባር ነው።

በዘውግ ማንነት ላይ ከተንጠለጠለው ፖለቲካችን የሚቀዳ አስተሳሰብ እና አሠራር ሀገራችንን የጦርነት እና የድህነት መቀመቅ ውስጥ የከተተና እየከተተ ያለ አስተሳሰብ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

የከተማ መሥተዳደሩ ስለ ፈተናው እና ከላይ የተጠቀሰውን ለማኅበረሰቡ ጥራት ያለው አግልግሎት ከመስጠት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌለውን የብሔር ኮታ ምደባን አስመልክቶ ለከተማዋ ነዋሪዎች በአፋጣኝ ግልጽ ማብራሪያ እንዲሰጥ እንጠይቃለን።

ኢዜማ በኃላፊነት ቦታዎች ላይ ለሚደረጉ ምደባዎች በምንም ዓይነት መንገድ የብሔር ማንነትን መሠረት ያደረገ መድልኦ የሚደረግባቸው እንዳይሆኑ፤ አሠራሩም ለሁሉም ዜጎች ግልፅና ችግር በሚፈጥሩ አመራሮች ላይ የማያወላዳ ተጠያቂነት ማስፈን የሚችል እንዲሆን ማድረግ ይገባል ብሎ ያምናል፡፡

ሚዲያዎችም ይህን ሁኔታ በትኩረት በመከታተል ለሕዝብ ተገቢውን ሚዛናዊ መረጃ በመስጠት እና ችግር ሲፈጠርም ተከታትሎ በመረጃ በማጋለጥ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ አበክረው በመሥራት የሙያ ግዴታቸውን እንዲወጡም እንጠይቃለን፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (#ኢዜማ)

ታኅሳስ 15/2016 ዓ.ም.

Exit mobile version