Site icon ETHIO12.COM

ኢትዮጵያ “ለቦንድ አበዳሪዎቹ ገንዘቡን በተለየ አካውንት አስቀምጠን ውይይቱን መቀጠል እንችላለን” አለች፤

ሀገራችን ወለዱን የመክፈያ አቅም አላጣችም። ወለዱን የመክፈል አቅም ማነስ ሳይሆን በመርህ ጉዳይ ነው ያልተከፈለው። January (አዲሱ ዓመት እንደጀመረ) ወደ ውይይት እንገባለን ከቦንድሆልደሮች ጋር፤ ውይይቱ እንዳለቀ ወዲያ የመክፈል ብቃት አለን። በውይይት ጊዜ ለኮንፊደንስ የሚጠቅም ከሆነ ለቦንድ አበዳሪዎቹ ገንዘቡን በተለየ አካውንት አስቀምጠን ውይይቱን መቀጠል እንችላለን።

ከ2007 ዓ/ም ጀምሮ እንደ ፋይናንስ ምንጭ እና መደበሪያ እንዲሆን የ1 ቢሊዮን ዶላር ቦንድ ሽጣ በየዓመቱ ከ62 ሚሊዮን ዶላር ወለድ ስትከፍል ቆይታለች።

በአመት ሁለት ጊዜ የሚከፈለውን የቦንዱን ወለድ በዚህ ጊዜ መክፈል የሚገባውን 33 ሚሊዮን ዶላር አልከፈለችም። 14 ቀን ተጨማሪ የእፎይታ ጊዜ ቢሰጥም እሱም አልፏል። ከጋና እና ዛምቢያ ቀጥሎ ብድሯን መክፈል ያልቻለች ሶስተኛ የአፍሪካ ሀገርም ተብላለች።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ስለጉዳዩ ምን አሉ ?

ኢትዮጵያ ወለዱን በቀነ-ገደቡ ሳትከፍል ከቀረች በኋላ በመንግሥት እና በቦንድ ባለቤቶች መካከል የአከፋፈል ሽግሽግ ድርድር እየተደረገ እንደሚገኝ ዶቼ ቨለ ሬድዮ ዩኒቨርሳል ኢንቨስትመንት በተባለ ኩባንያ በኩል የኢትዮጵያ ቦንድ ባለቤት የሆነው ” ካፒቱሉም አሴት ማኔጅመንት “ን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል።

” ካፒቱሉም አሴት ማኔጅመንት ኩባንያ ” መቀመጫውን በጀርመን ፣ በርሊን ያደረገ ሲሆን የኩባንያ የፈንድ ማኔጀር ቲዎዶር ኪርሽነር ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የቦንድ ባለቤቶች የየራሳቸውን ምክረ-ሐሳብ እንዳቀረቡ ገልጸዋል።

” አሁን ባለው ዋጋ ያን ያህል የተራራቁ አይደሉም ” ያሉት ኪርሽነር የአከፋፈል ሽግሽግ ላይ የሚደረገው ድርድር ዛምቢያ ካለፈችበት ተመሳሳይ ሒደት በጣም ፈጥኖ ሊጠናቀቅ እንደሚችል ተስፋ እንዳላቸው ገልጸዋል።

ባለፈው ሳምንት የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ  ” መክፈል የሚገባንን 2.2 ቢሊዮን ዶላር (ዕዳ) እንዳንከፍል እፎይታ ያገኘንበት ወቅት ላይ ሆነን 33 ሚሊዮን (ዶላር) ይቅርና 300 ሚሊዮን (ዶላር) የመክፈል አቅም አለን ” ሲሉ ለኢቲቪ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት ከፓሪስ ክለብ እና ከቻይና መንግሥት የዕዳ ክፍያ እፎይታ አግኝቷል። 

በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ በኩል የሚደረገው የዕዳ አከፋፈል ማሻሻያ ድርድር በአንጻሩ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (IMF) ጋር የሚደረገው ውይይት ውጤት እየተጠባበቀ ነው።

ኢትዮጵያ በቡድን 20 የጋራ ማዕቀፍ መሠረት ” ሁሉም አበዳሪዎች  ” እኩል ሊስተናገዱ ይገባል የሚል አቋም አላት።

የዚህ መከራከሪያ ዋና ምክንያት የደሀ ሀገሮችን ዕዳ ለማቃለል ከ3 ዓመታት በፊት በቡድን 20 ሀገራት የጸደቀ ማዕቀፍ ነው።

በማዕቀፉ ከሚሳተፉ አበዳሪዎች የመግባቢያ ሰነድ (MoU) የተፈራረመ ተበዳሪ ሀገር ከሌሎች ኦፊሴላዊ እና የግል አበዳሪዎች ተመሳሳይ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ጥያቄ ማቅረብ ይኖርበታል።

የገንዘብ ሚኒስቴር 33 ሚሊዮን ዶላር ወለድ ሳይከፍል የቀረው አበዳሪዎችን እኩል ለማስተናገድ በሚከተለው መርኅ ሳቢያ ” የማዘግየት ጉዳይ እንጂ፤ ያለመክፈል ጉዳይ / የdefault ጉዳይ አይደለም ” ሲል አሳውቋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፋይናንስ እና ኢንቨስትመንት ረዳት ፕሬፌሰር ዶ/ር ሰውአለ አባት ፤ መንግስት የሚጠበቅበትን ክፍያ በመክፈል ድርድሮችን ከጎን ቢያስኬድ ነው ጥሩ ብለዋል። ብድሩን እንደማያዣ አድርጎ የሚደረግ ድርድር ሀገርን ይጎዳል እንጂ አጠቅም ሲሉ ሃሳባቸውን ገልጸዋል።

መረጃው ከቲክቫህ የተወሰደ ነው

Exit mobile version