ኮንትሮባንድ ክፉኛ ከሚፈታተነው የኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሬ ገቢ ምንጮች መካከል የቁም እንሳሳት ንግድ አንዱ ነው። ዘርፉ በከፍተኛ ደረጃ በኮንትሮባንድ ንግድ በትሥሥር ዝርፊያ የሚፈጸምበት ሲሆን ጎረቤት አገሮችን በመጠቀም እንደሚከናውን በስፋት ሲነገር ቆይቷል።
ኢትዮጵያ በቀንድ ከብት ከአፍሪካ አንደኛ ከዓለም ደግሞ አምስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኝ ቢሆንም
ዛሬ ይፋ ሲደረግ እንድተሰማው ባለፉት ስምንት ዓመታት ከቁም እንስሳት ንግድ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ ክፉኛ አቆልቁሏል። ቀደም ሲል ከዘርፉ እስከ 150 ሚሊየን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ይገኝበት የነበረው የቀንድ እንስሳት ንግድ፣ በ2014ና በ2015 ዓ.ም ገቢው ወደ 17 ሚሊየን ዶላር አሽቆልቋሏል። ምክንያቶቹ በጥናት አቅራቢዎቹ በዝርዝር ይፋ ስለመሆናቸው ኢዜአ ባይጠቅስም፣ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ አካላት ቀደም ሲል ታጣቂ ሃይሎችን የሚያደራጁ፣ የሚያስታጥቁና የሚያሰማሩ ” ወዳጅ የሚባሉ አገራት” ዝርፊያውን አዲስ አበባ ተቀምጠው ከሚመሩት መካከል ቅድሚያ የሚጠቀሱ ናቸው።
ቀደም ሲል ከፍተኛ የቀንድ ከብት ባለበት የአገሪቱ ክፍል የሚነቀሳቀሱ የብሄር ስም ያላቸው ታጣቂዎች የቀንድ ከብቶችን ወደ ድንበር እንደሚነዱ ጠቅሰን መዘገባችን ይታወሳል። ከብቶቹም በሶማሌ ወደብ በኩል እንደሚሻገሩ ጥቆማ የሰጡት አስታውቀው ነበር። መንግስት ሃይሉን በሙሉ ድንበር በመጠበቅና የዝርፊያ ሰንሰለቱን እንዳይዘጋ እነዚሁ አካላት በብሄር ነጻ አውጪ ስም እዛና እዚህ ጦርነት፣ ግጭትና አለመረጋጋት በመፍጠር የመንግስትን አቅም እንደሚበታትኑ በዜናው ተጠቁሞ ነበር።
- ይህ በንዲህ እያለ ነው ኢትዮጵያ በቀን ከ1 ሺህ 200 በላይ የቁም እንስሳት በሕገ-ወጥ መንገድ ከሀገር በመውጣታቸው በየቀኑ ከ630 ሺህ ዶላር በላይ እንደምታጣ በይፋ በኢዜአ በኩል የተገለጸው።
- በኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አዘጋጅነት ሕገ-ወጥ ንግድን መከላከል ላይ ያተኮረ ሀገር አቀፍ ጉባዔ ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
- ምክር ቤቱ ሕገ-ወጥ ንግድ በስፋት በሚታይባቸው ዘርፎች ላይ ያካሄዳቸውን ጥናቶች ይፋ አድርጓል።
- ጥናቶቹ በቁም እንስሳት፣ በመድኃኒት፣ በጨርቃጨርቅ፣ በሎጂስቲክስ ሥርዓት ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችና ንግድን በተመለከቱ የሕግ ማዕቀፎች ላይ የተካሄዱ ናቸው።
- በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኢንተርፕራይዝ ልማት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አለባቸው ንጉሴ፥ በቁም እንስሳት ኤክስፖርት ግብይት ላይ የሚታዩ ችግሮችና የመፍትሔ ሃሳቦችን በተመለከተ ጥናት አቅርበዋል። በዚህም ባለፉት ስምንት ዓመታት ከቁም እንስሳት ንግድ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ እየቀነሰ መምጣቱን ጠቅሰዋል።
- ለማሳያም ቀደም ሲል ከዘርፉ እስከ 150 ሚሊየን ዶላር የሚጠጋ ገቢ ይገኝ እንደነበር አስታውሰው፤ በ2014 ዓ.ም እና በ2015 ዓ.ም ገቢው ወደ 17 ሚሊየን ዶላር መቀነሱን አስረድተዋል።
- የችግሩ ምንጭም የሕገ-ወጥ ንግድ ስልትና ዓይነት እየተቀያየረ መምጣቱ፣ የክትትልና የቁጥጥር ሥራው አጥጋቢ አለመሆኑ፣ እንዲሁም በቴክኖሎጂ የተደገፈና ሕጉን የጠበቀ የግብይት ሥርዓትን ማስተግበር ላይ ክፍተቶች መኖራቸው መሆኑን ጥናቱ አመላክቷል።
- ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የቁም እንስሳት ልየታና ከተቀባይ አገራት ጋር ያለው ሕጋዊ ስምምነት ላይም ክፍተቶች እንደሚታዩ አንስተዋል።
- በመሆኑም በቅርቡ በአገሪቱ በሦስት የመውጫ በሮች በተካሄደ ጥናት በቀን ከ1 ሺህ 200 በላይ የቁም እንስሳቶች በሕገ-ወጥ መንገድ ከአገር እንደሚወጡ ተረጋግጧል ብለዋል።
- በዚህም አንድ የቁም እንስሳት እስከ 530 ዶላር የሚያወጣ ሲሆን፤ አገሪቱ በቀን 630 ሺህ ዶላር በላይ በአንድ ወር ደግሞ 19 ሚሊየን ዶላር ታጣለች ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት አመልክተዋል።