Site icon ETHIO12.COM

“የባህር በር አይገባሽም” በሚል አልሸባብባ፣ ግብጽ፣ አረብሊግ፣ ሞቃዲሾና “ባንዳዎች” በህብረት ኢትዮጵያ ላይ ዘምተዋል፤

The Somaliland port of Berbera in 2018 -Getty Images

በኢትዮጵያ ስም የሚምሉም የኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤትነት በምን መስፈርት ይቃወማሉ? የዘመን ውርጃ

ኢትዮጵያ የባህር በር አልባ መሆኗን ተከትሎ የአጠቃላይ የወጪ ገቢዋን ከ25 በመቶ እስከ 30 በመቶ ስትከስር ሰላሳ ዓመት አልፏታል። ይህ ያንገበግባል። ያማል። ያስቆጫል። ይህ የሆነው ደግሞ ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ህዝብ ያለ አንዳች በደላቸው የባህር በር አልባና ታሪክ አልባ እንድትሆን በሴራ የተፈጸመ ነው። ይህ ሴራ እውን የሆነው ደግሞ ኢትዮጵያ በወለደቻቸው የአብራኳ ልጆች አማካይነት ነው። እንዲህ ያለ የዘመን “ውርጃ” ኢትዮጵያን አክስሯታል። አሳንሷታል። ጎትቷታል። ሰሞኑንን የተሰማውን ዜና ተከትሎ አዳዲስ በኢትዮጵያ ባንዲራ የተጠቀለሉ “የዘመን ውርጃዎች” ሌት ከቀን በቅጥረኝነት እየጮሁ ነው። ለምን? የ

ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ኢትዮጵያ አርሶ አደረቿ አፈር ግጠው፣ ለፍተው ያመረቱትን በመሸጥ የምታገኘውን የወጪ ገቢዋን ለወደብ ኪራይ እየገበረች መኖሯ ብቻ ሳይሆን በፖለቲካው የማንም ወጠጤና ጉልበተኞች እንዳሻቸው እንዲያላምጧት ምክንያት ሆኗል። ይህን ፈር የለቀቀ ጫና “አባይን አትገድቡ” በሚል የጸጥታው ምክር ቤት በየሳምንቱ ገትረርው አሳይተውናል። ፍትህን ዓለም አደባባይ ሰቅለው ሉዓላዊነታችሁን አታስጠብቁ፣ ስትወረሩ ዝም በሉ፣ መንግስታችሁን አፍርሱ፣ ለወንበዴ ቤተመንግስት ልቀቁ ወዘተ ብለው አላግጠውብናል። የሃሰት ዜና በደቦ እያሰራጩ እረፍት ነስተውናል። “ትፈርሳላችሁ” በሚል ፋታ ነስተውናል። በስንዴና ዘይት ሰበብ ቆመረውብናል።

ኢኮኖሚያችን ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ ክብራችንና ታላቅ የፖለቲካ ጡንቻችንን ሰብረው ተላላኪ አድርገው ሊያስቀሩን የባህር በር አልባ እንድንሆን ወንበዴ አደራጅተው፣ ወንበዴ አንግሰው፣ በወንበዴዎች ስምምነት ዓላማቸውን አስፈጽመው በድህነት ሲያደቁን ኖረዋል። ትንሽ ቀና ስንል በማዕቀብ፣ በዛቻ፣ በእግድ እያሽመደመዱ የድህነት ዓመድ ላይ እየተንከባለልን እነዚህኑ አላካት ስንለምን እንድንኖር አስገድደውናል። ይህ እንደ ዜጋ ያማል። ያሳዝናል። በሌላ በኩል ጀዝመኛ ለሆኑ ኢትዮጵያዊያን እልህ ውስጥ የሚከት አጋጣሚም ሆኖልናል። ደግሞም ነው።

በዚህ በድህነትና ያለንን በመገበር የድህነት አዙሪት ውስጥ እየተንፏቀቅን መኖር ሊያበቃ እንደሚገባ ሲታሰብ የባህር በር ባለቤት መሆን ቁልፍ ጉዳይ እንደሆነ በስፋት አስተያየት ቢሰጥም ተግባር ላይ ያዋለው አካል አልተገኘም። አንዳንዴም ፍላጎቱ ሁሉ ስለመኖሩም እስክንጠረጥር ድረስ ለጉዳዩ ጀርባ የሰጡ መሪዎች አይተናል። የነበረንን ማስረከብ ብቻ ሳይሆን ሌላ አማራጭም እንዳይኖር አድርገው ጉልበታችን የሰበሩ እንጂ ሊያቀኑንን ያሰቡ መሪዎች አላየንም። ከስህተት ለመታረም የሞከሩ ቢኖሩም እንዳይጸኑ አምክነዋቸዋል። በዚህ መነሻ ህዝብ ተቀይሞ ይህ ታሪካዊ ሃፍረት ሊያበቃ እንደሚገባ በየአቅጣጫው ጩኸት በርክቶ ነበር።

ከዚህ የሞራል ብስባሽ ማቀን ብንቆይም፣ ለዓመታት በርካቶች የጮሁለት፣ የታገሉለት፣ ሲያልፍም የሞቱለት የኢትዮጵያ ከፍታ ሚስጢር የሆነው የባህር በር ጉዳይ በሰበር ዜና ተሰማ። ዜናው የፈጠረው ደስታ አፍታም ሳይቆይ እግር በግር የዘመኑ ውርጃዎች በቅጥፈት ዜናቸውና በተለመደው ማጥላላት በባንዲራዋ ተሸፍነው እንደ አልሸባብ፣ ግብጽ፣ የሞቃዲሾው ወራሪና ጨፍጫፊ ሃይልና በሚከፍላቸው ጣውንት ምሬት ኢትዮጵያ ላይ ተነሱ። የባህር በርን ማግኘትን ከተቀጠሩበት ዓላማ ጋር አሳንሰው ላንቃቸውን አላቀቁ። እንዲህ ያለው ታሪካዊ ሃፍረት ዛሬ ላይ እንደምንወቅሳቸው የቀድሞ ቅመኞች ተርታ የሚያሰልፍ መሆኑንን በበሉት መጠን ዘንግተው ዜናውን ለማጠልሸት ድርጅታቸውንና ሎጅስቲካቸውን አነቃነቁ።

“ከኢትዮጵያ ድንበር እስከ በርበራ ድረስ የ241 ኪሎ ሜትር ርቀት አለው። መንገዱ እውቅና ያላገኘው የሶማሌላንድ መንግሥት ከአውሮጳ ኅብረት ባገኘው የገንዘብ ድጋፍ የተሠራ ነው። ከኤደን ባህረ-ሰላጤ ደቡባዊ ጫፍ ላይ የምትገኘው ሶማሌላንድ እንደ አገር ለመቆም የሚያስፈልጋትን ቅድመ-ሁኔታዎች ሁሉ ታሟላለች። የመገበያያ ገንዘብ፣ በተግባር የሚሠራ የቢሮክራሲ ስርዓት፤ የሰለጠነ ፖሊስ እና የመከላከያ ሠራዊት አላት። መቀመጫውን ሐርጌሳ ላይ ያደረገው እና ዓለም አቀፍ እውቅና ለማግኘት የሚታትረው መንግሥት የሶማሌላንድን ድንበር ማስጠበቅ፤ ከሞቅዲሾ መንግሥት ጋር መደራደር የሚችል፣ እንደሆነ የፕሬዚዳንቱ አማካሪ ሆነው የሰሩት ረዳት ፕሮፌሰር መድህኔ ታደሰ ሚያዝያ 5 ቀን 2008 ዓ ም ለጀርመን ድምጽ ተናግረው ነበር። ይህን ያሉት ኢትዮጵያ የበርበራን ወደብ መጠቀም እንዳለባት ሲያሳስቡ ነው። ግን ተግባር ላይ ሳይውል ቀረ።

የሶማሌላንድ የሚሠራ የዴሞክራሲ ስርዓት የተሻለ ጸጥታ እና ደህንነት ያላት በመሆኑ የሚያስፈራ የጸጥታ ስጋት እንደሌለባት በዝርዝር አስታውቀውም ነበር። ከዚህ አኳያ ከሶማሊላንድ ጋር የሚደረገውን ስምምነት ሊገፋና በሃይል ሊገለብጥ የሚችል ሃይል እንደሌለም አመላክተው ነበር።

ከኤርትራ በተሻለ ምርጫና አማራጭ ሚዲያዎችን የምትጠቀመው፣ ህግና ህገመንግስት ያላት፣ አልሸባብን ድርሽ እንዳይል ያደረገችው የሶማሊ ላንድ ከኢትዮጵያ ጋር የባህር በር የሚያጎናጽፍ ስምምነት ማድረጓን ተከትሎ የሚጠበቀው ጫጫታ ከውስጥም ከውጭም ቢሰማም ተግባራዊ ከመሆን የሚያግደው ነገር እንደሌለ የሚገልጹ አሉ።

ግብጽ፣ አልሸባብ፣ የሞቃዲሾው መንግስት፣ ኤርትራን ጨምሮ የአረብ ሊግ ስምምነቱን እንደማይቀበሉ ጠቅሰው ዛቻ አስምተዋል። የአውሮፓ ህብረትም ” የሶማሌያን ሏላዊነት ማክበር ግድ ነው” ዓይነት መግለጫ አውጥቷል። እነዚህ ሃይሎች በሙሉ የአረብ ኤምሬትስ የበርበራን ወደ በሊዝ ስትከራይ አልተነፈሱም።

አልሸባብ “ደም እንደ ጅረት ይወርዳል” ሲል እንደለመደው በደም ጎርፍ አስፈራቷል። ግብጽ ከሞቃዲሾ መነግስት ጋር እንደምትቆም በይፋ አስታውቃለች። እንግሊዝ ዝምታን ስትመርጥ አሜሪካ የቀድሞዋን ሶማሊያ ብቻ እንደምታውቅ ብዙም ሳትዘባርቅ በዲፕሎማቲክ ቋንቋ አቋሟን አስፍራለች። ኤርትራ ያለችበት አርብ ሊግ ከግብጽ ጽህፈት ቤቱ ጩኸቱን አሰምቷል። ሁሉም የሚጠበቅ ነው።

ከሁሉም በላይ የሚገርመው የኢትዮጵያን የባህር በር አልባነት ደረታቸውን እየደቁ በሃዘን ሲናገሩና በወቅቱ ኢትዮጵያን ጎዶሎ ያደረጉትን መሪዎች ሲያወግዙ የነበሩ ዛሬ ተገልብጠው “ለምን የባህር በር ባለቤት እንሆናለን” የሚል ጫጫታ እያሰሙ ነው። እነዚህ በኢትዮጵያ ስም የሚምሉ የሳይበር ተዋጊዎች ህዝብን በማደናገርና በማደናበር ስራ መሰማራታቸው ብቻ ሳይሆን ” ኢትዮጵያ የባህር በር አይስፈልጋትም” የሚሉበትን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ሌሎችም መሰራታዊ ምክንያቶቻቸውን አያስረዱም። ጥቂት ቢሆኑም ተከታዮቻቸው ” ጀግና፣ ወሰን የሌለህ፣ የቁርጥ ቀን…” በሚል ከማወደስና ቅስቀሳቸውን ከማሰራጨት በዘለለ ጥያቄ ሲያነሱ አይታይም።

ይህ ለኢትዮጵያ የታሪክ እጥፋት እንደሚሆን በሚነገርለት ስምምነት ዙሪያ ከላይ የዘረዘርናቸው የኢትዮጵያ ቋሚ ጠላቶች ሳያንሱን፣ ከላይ የተዘረዘሩት ቀመኞች የሚያሴሩት ሴራ ተባባሪ የሆኑ “ኢትዮጵያዊ ነን” የሚሉ የዘመናች ጉዲቶች ጉዳይ በተመሳሳይ የሚዘከር ጥቁር ታሪክ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።

አገላለጹ ልክ ባይሆንም መንግስትን፣ ፓርቲንና ሹመኞችን መጥላት ከብሄራዊ ጥቅም ጋር ማገናኘት ነውር ነው። በኢትዮጵያ ቢቻልና ቢያድለን የፓርቲ ፕሮግራምን በመቃወም አሳብና መርህ ላይ ተመስርተው የሚታገሉ ተፎካካሪዎች እጅግ አስፈላጊ ቢሆኑም መንገዱ ስራ የሚጠይቅ፣ ትዕግስትን የሚፈታተን፣ አድካሚ ውጣ ውረድ ያለው በመሆኑ አቶ ጃዋር ” ብሄረተኛነትን ማቀንቀን ህዝብን በዘር ለማነሳሳት ይጠቅማል” እንዳለው በነጻ አውጪ ስምና “በተጎዳሁ” ትርክት አገርን ወደ ቀውስ መስደድ የስልጣን መወጣጫ አቋራጭ መንገድ ሆኗል።

ይህ አጭሩ በዘር ህዝብን የማነሳሳት አባዜ በተግባር እንደታየው ውጤቱ የሚማልበትን ህዝብን ያቆረቆዘ፣ በረሃብና ችጋር የደፋ፣ ህጻናትን ከትምህርትና ተስፋቸው ያስተጓጎለ፣ የአገር ኢኮኖሚን ያነከተ፣ ሞት፣ መፈናቀልን፣ ስደትና ልመናና ያባባሰ፣ እጅግ የሚዘገንን ሃፍረት የተመዘገበበት፣ በጥቅሉ በዓለምም ሆነ በገዛ ደጅ ውርደትን የጋበዘ እንደሆነ ኢትዮጵያዊያን አስረጂ አይፈልጉም። ሁሉም በየጓዳው ይህን አይቷል። ወይም ደርሶበታል። በዚህ የተጠቀሙ ቢኖሩ የዘር ቅስቀሳ ተዋንያን የነበሩት አቶ ጃዋርን ጨምሮ ሚሊዮን ብሮችን ማፈሳቸው፣ ለታጣቂ ገንዘብ ሰብስቡ የሚሉ የደም ነጋዴዎች፣ የዩቲዩብና የዩቲዩብ የአደባባይ ለማኞች ናቸው። እዚህ ላይ አቶ ደረጀ ደስታ ከአቶ ጃዋር ጋር ኪንያ ድረስ ሄዶ ያደረገው ቃለ ምልልስ አስመልክቶ አንድ ነገር ልበል።

ኢትዮጵያ ውስጥ “ጋዜጠኛ” ብዬ ለመጥራት ስለምቸገር አቶ ደረጀ ልበል። ለመሆኑ ኪንያ ድረስ የሄድከው ጃዋርን ለማናውቀው ለኢትዮጵያዊያን ለማስተዋወቅ ነው? እዛ ድረስ መሄድህን የነገርከን ጃዋር ” በለውጡ ማዘኑንን ልታረዳን ነው? ለያውም በጃዋር አንደበት? ሻሸመኔ፣ ዝዋይ፣ መቂ ዘር ተለይቶ ንብረት ሲወድምና ልጅ እያየ አባት በስለት ሲታረድ የት ነበርክ። የነ ሃይሌ ገብረስላሴ ንብረትና የበርካታ ኢትዮጵያዊያን የላብ ውጤት በዘራቸው እየተመረጡ እንዲውድምና እንዲዘረፍ ሲደረግ ማን ነበር መመሪያ ሰጪው? ጃዋር፣ መረራና፣ በቀለ ገርባ ቁጭ ብለው “በአማርኛ አትናገሩ፣ አማርና ተናጋሪ አታግቡ፣ ካገባችሁ” እየተባለ ዳንኪራ ሲጨፈር አላየህም? “ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት መንግስት አለ” በሚል ራሱን መንግስት አድርጎ የሚሰብከው ጃዋር ይህን ሲል አንተ ተኝተህ ነበር ወይስ አልጀበንክም? ጃዋርን አግኝተህ ማነጋገርህ፣ ልምዱን እንዲያካፍል ማድረግህ ክፋት ባይኖረውም የሃጫሉ ሁንዴሳ ወንድም፣ ሚስትና ቤተሰብ አስከሬን ላይ የነበረውን የፖለቲካ ግብግብ አስመልክቶ የተናገሩትን አልሰማህም? ራሱ ሃጫሉ ማንን ነበር የሚጠረጥረው? ምን ብሎ ስጋቱን እንዳስታወቀ አደባባይ ሲናገር ኬንያ ጃዋርን ፍለጋ ሄደህ ነበር? ብዙ ጊዜ ሚዲያ ላይ እንደኖረ ሰው ይህ ሁሉ አይጠፋህምና አስብ። ወይ በሙያው በአግባቡ ግፋበት ወይም ማዕረግ ቀይር። ወደ መነሻዬ ለመስለስ

አልሸባብ ከመቃዲሾው መንግስት ጋር ሆኖ ኢትዮጵያን ደም በደም እንደሚያደርግ ዝቶ ስምምነቱን ተቃውሟል። በፍጹም ተቀባይነት እንደሌለው ጠቅሶ የለመደውን ሽብር እንደሚፈጽም አመልክቷል። ለሞቃዲሾ መንግስት መጽናትና ለሶማሌ መረጋጋት የልጆቿን ህይወት የከፍለች አገር በራሱ በሶማሌ መንግስት “ወዮልሽ” ተብላለች። የሞቃዲሾው መንግስት ከአልሸባብ ጋር ግንባር ፈጥረው ሊወጉን ሲዝቱ …

በሚሊዮን የሚቆጠሩ የሶማሌና የኤርትራን ተወላጆች አቅፋ ከዜጎቿ እኩል እያስተዳደረችና እየቀለበች ያለች አገር ከራሷ ምድር፣ በራሷ ኢንተርኔት፣ራሷ ላይ ዘመቻ እየተካሄደባት መሆኑ ሊያሳበንና በአንድ ልንቆም ሲገባ፣ እስከ አዋሽ ድረስ ኢትዮጵያን ወሮ ላረደ፣ ለጨፈጨፈ የሞቃዲሾ መንግስት አፈንደደው የሚከራከሩ “ኢትዮጵያዊያንን” ማየት የዘመን ሁሉ ሃፍረት ው ቢባል አያንስም።

ከዚህ ብስባሽ ስብዕና ፊት ለፊት በአንድ ወር ስልጠና ወራሪውን የዚያድባሬ ሃይል የበሉ የኢትዮጵያ ሚሊሻና ወታደሮች ደም ይጮሃል። የነዚህ የካራማራ ጀግኖች ደም ከዩቲዩብ ገቢና ከተራ የደም ፖለቲካ ሸቀጥ በላይ ይናገራል። ግብጽ ኢትዮጵያ አዋሽ ድረስ ስትወረር አልተነፈሰችም። የአርብ ሊግም ስምምነቱን ዛሬ እንደዚህ ፈጥኖ በተቃውመበት ፍጥነት አልተቃወመም። ይህ ሁሉ ቁስል ያለባት አገርና ህዝብ አካል ነነ የሚሉ በምን መስፈርት ነው ኢትዮጵያ የባህር በር ማግኘቷን ሃጢያት አድርገው በግብጽና አልሸባብ ልክ የሚያስቡት? ወይም ለግብጽና አልሸባብ ብሎም ለሴረኛው ጣውንታቸው የሚያጎበድዱት?

ኢትዮጵያ ቂሟን ረስታ፣ ልጆቿን ሶማሌ አዝምታ ህይወት የገበረችው፣ ለሶማሌ ሰላም ከአልሸባብ ጋር የተፋለመችው ሁሉ ተረስቶ፣ ሶማሌያዊያንንን በቦንብ በየአደባባዩ ከሚያቃጥለው አልሸባብ ጎን ሆና ራሷ ሞቃዲሾ ኢትዮጵያ ላይ ስትዝት መንገበግብ ሲገባን የአገራችንን ብሄራዊ ጥቅም በዜሮ አባዝቶ ለአራጆች መስገድ አሳፋሪ ነው። የፖለቲካ ጸብ፣ አለመግባባት፣ ልዩነት፣ የተጓደለ ፍትህ ወዘተ ችግሮን በብሄራዊ ክህደት ማስተካከል አይቻልም። የሚቻለው በአድካሚ ትግል፣በህዝባዊ ትግል፣ በሚቻለው ሁሉ ብሄራዊ ጥቅም ላይ አንድ በመሆን ብቻ ነው። አገርን በማኮሰስና በጠላት አጀንዳ ዶላር እየተቀበሉ አገር ብሄራዊ ጥቅም እንድታጣ መስራት በየትኛውም ዘመን የማይሽር ጠባሳ ነው።

ይህን ሁሉ ስል መንግስት ትክክል ነው። ጽድቅ ነው። እንከን የለበትም ለማለት ሳይሆን በርካታ ግድፈቶቹን ነቅሶ መታገል ሲቻል ብሄራዊ ጥቅማችን ላይ መረባረቡን ለመቃወም ነው።

በዓለም አርባ አራት ባህር አልባ አገራት አሉ። ሰላሳ ሶስቱ አፍሪካ ውስጥ ናቸው። ከሰላሳ ሶስቱ አስራ ስድስቱ እጅግ ደሃ አገራት ናቸው። ኢትዮጵያ ከሁሉም አገራት የሚበልጥ ህዝብ ያላይና ባለ ትልቅ ኢኮኖሚ አገር ናት። ታሪክ ተሸቅጦ አንገቷን ማጅራት ተመታች እንጂ የባህር በሮች ባለቤት ነበረች።

ጥናቶች እንደሚሉት ባህር የሌላቸው አገራት ከ35 እስከ 40 በመቶ የወጪ ንግዳቸው ላይ ጫና አለባቸው። ወይም ይቀንስባቸዋል። ይህ ማለት አንድ አገር የባህር በር ሲኖራት ከነበራት ኢኮኖሚ ላይ በአንድ ጊዜ ከ30 እስከ 40 በመቶ ገቢ ይጨምራል ማለት ነው። እንግዲህ ይህንን ነው የኢትዮጵያ “ልጆች” ነን የሚሉ የሚቃወሙት።

ኢትዮጵያን ጨምሮ ኢንቨስተሮች የባህር በር የሌላቸው አገሮችን አይመርጡም። ብዙ ወጪ ስለሚኖርባቸው አይመርጡትም። በመሆኑም አሁንም ጥናቶች እንደሚያሳዩት የባህር በር ባለቤት መሆን ኢንዘስትመንት ያሳድጋል። ኢንዘስትመንት ሲያድግ ምርት ይጨምራል። ገቢ ያድጋል። የዜጎች የመግዛት አቅም ይጨምራል። በባህር ወደብ ክፍያ ሳቢያ የሚሰቀለው የሸቀጦች ዋጋም ይቀንሳል።

ስለዚህ የምትቃወሙና ” ኢትዮጵያ ለመን የባህር በር ባለቤት ትሆናለች” የምትሉ ከላይ የተነሱትን መከራከሪያዎች አንሱና ሞግቱ። ለህዝብ ለአገር የሚያስከትለው ኪሳራ ካለ ንገሩን። ለምን ብልጽግና ወይም ተቅላይ ሚኒስትር አብይ የሚመሩት መንግስት እዚህ ውል ላይ ደረሰ የሚል የዘር ጉዳይም ካለ ግልጽ አድርጉልን። ሃሜትና የዩቲዩብ ጉሊት ወሬ ይሰለቻል።

ትልቁ ቁም ነገር፣ ከተለያዩ ምንጮች እንደሚሰማው ከሆነ ጉዳይ ውስጥ ውስጡን ያለቀ ነው። የኢትዮጵያን መከላከያ ሃይል ባብ ኤልመንደብ ላይ መስፈር አውራዎቹ ይፈልጉታል። እናም ሶማሊ ላንድም አገር. ኢትዮጵያም የባህር በር ይኖራታል። ረዳት ፕሮፌሰር መድህኔ ታደሰ ድሮ እንዳረጋገጡትም ሶማሊ ላንድ ቸፍቻፊው የሞቃዲሾ ሃይል ስጋቷ አይደለም። ቀድሞ የጎበዝ አለቃ የሚነዳውን ፖለቲካና ውጥንቅጥ ማረቅ ያልቻለ፣ በለመና ወታደሮችም ሊጸና ያቃተው ልምሻ መንግስት ነው። ኢትዮጵያን እነካለሁ ካለም ለይመለስ በቀናት ውስጥ ይሸኛል። ይህን እውነት የቀድሞ ዘማቾችና አይር ሃይላችን አሳይቶናል። እነሱም ያውቁታል። የማይገባቸው ባንዳዎች ብቻ ናቸው።

Exit mobile version