Site icon ETHIO12.COM

ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ማድረግ ረገድ!

ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን በማድረግ ረገድ የዲጅታል 2025 ስትራቴጂ ተቀርጾ ተግባራዊ በመደረጉ አበረታች ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ። ዶክተር በለጠ ሞላ፤ በዘርፉ እየተከናወኑ ያሉ ሥራዎችን አስመልክተው ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት፤ ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ለግሉ ዘርፍ ክፍት የማድረግና መሰረተ ልማትን ማስፋፋት ላይ በትኩረት እየተሰራ ነው።

የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ዕውን መሆን እንደ ሀገር ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች የኢኖቬሽን ፣የቴክኖሎጂና የአይሲቲ ዲጅታላይዜሽን (አይ ሲ ቲ ) ዘርፍ አንዱ ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ መንግሥት የቴሌኮሙኒኬሽን ኢንዱስትሪውን ለግሉ ዘርፍ ክፍት በማድረጉ በቴሌኮሙኒኬሽን ኢንዱስትሪው ተወዳዳሪ ኦፕሬተር መፍጠር ተችሏል፤ ይህም ለዘርፉ ልዩ ትኩረት እንደተሰጠው በተጨባጭ የሚያሳይ ነው ብለዋል።

በመሰረተ ልማት ግንባታው ረገድም ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ በዚህም የብሮድባንድ ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ቁጥር ከ35 ሚሊዮን በላይ እንዲሁም የሞባይል ስልክ ተጠቃሚዎች ቁጥርም ከ73 ሚሊዮን በላይ መድረሱን አመላክተዋል።

የክፍያ ሥርዓቱን ወደ ዲጂታል አሰራር የመቀየሩ ሂደት እየተፋጠነ በመሆኑ ብዙ ለውጦች እየታዩበት ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ አሁን ዲጅታል አሠራር ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ በመሆኑ በትሪሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በዲጅታል የክፍያ ሥርዓት ውስጥ እየተዘዋወረ ነው ብለዋል።

የመንግሥት አገልግሎቶችን ዲጂታላይዝ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ እስካሁን በሀገር አቀፍ ደረጃ 528 አገልግሎቶች ዲጂታል መደረጋቸውን ጠቅሰዋል፤ በቀጣይም አገልግሎቶች የማዘመን ሂደቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ዕውን እንዲሆን መሰረት የሚጥሉ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው ያሉት ሚኒስትሩ፤ መሰረተ ልማትን ማስፋፋት፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ለግሉ ዘርፍ ክፍት የማድረግ እና የክፍያ ሥርዓቱን ወደ ዲጂታል አሰራር ማስገባት ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ ፤ የዲጅታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ተቀርጾ ተግባራዊ ከሆነ ሦስት ዓመት ከስድስት ወር አስቆጥሯል። ስትራቴጂያዊ ግምገማ ተካሂዶ የታዩ ክፍተቶች እና የተገኙ ውጤቶች ተለይተዋል። የኢንተርኔት ብሮድባንድ ተጠቃሚ ቁጥር መብዛቱ ፣ የሞባይል ቁጥር እያደረ መምጣቱ፣ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ለግሉ ዘርፍ ክፍት መድረጉ እና የክፍያ ሥርዓቱ እያደገ መምጣቱ በዲጅታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ የተያዙ ግቦች እንዲሳኩ መልካም እድሎች ናቸው።

በቀሪ ጊዜያት በስትራቴጂ የታዩ ክፍተቶችን በማሟላት አዳዲስ ሃሳቦች ካሉ ከስትራቴጂው ጋር በማቀናጀት የተሻለ ሥራዎች ይሰራሉ ያሉት ሚኒስትሩ፤ ከአምስት ዓመቱ በፊት እንደሀገር የነበርንበት የዲጅታል ሥነምህዳር እጅግ የተሻለ ውጤት የሚታይበት ይሆናል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ዲጅታል ኢትዮጵያ እውን በማድረግ ረገድ ተግዳሮቶች መኖራቸውን የጠቆሙት ሚኒስትሩ፤ መሰረተ ልማት ግንባታ የሚጠይቅ ካፒታል ለሀገር ቀላል አለመሆኑ፣ የፋይናንስ አቅርቦት እና በፈጻሚው፣ በተጠቃሚው እና በአልሚውም የእውቀት ክፍተትና በዲጅታል ዘርፍ በቂ የተማረ ሀይል አለመኖር እንደሆኑ ገልጸዋል። በቀጣይም ያሉትን ክፍተቶች በመሙላት የስትራቴጂው አምስት ዓመት ሲጠናቀቅ ወደፊት የተራመደ ውጤት ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ አስረድተዋል።

ወርቅነሽ ደምሰው

አዲስ ዘመን ቅዳሜ ጥር 11 ቀን 2016 ዓ.ም

Exit mobile version