Site icon ETHIO12.COM

የካፒታል ገበያ በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምር ይፋ ሆነ፤ “ኢ-መደበኛና ሕገ-ወጥ ኃብት ወደ መስመር ይገባል”

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የካፒታል ገበያ የዝግጅት ጊዜውን አጠናቆ በቅርቡ ሥራ እንደሚጀምር ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶር) የኢኮኖሚውን ዘርፍ አስመልክቶ በሰጡት ማብራሪያ ካነሷቸው ኃሳቦች መካከል የካፒታል ገበያ ይጠቀሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የካፒታል ገበያ በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባ የጠቆሙ ሲሆን ይህ የፋይናንስ ግብይት ሥርዓት ሲጀመር በርካታ ኢ-መደበኛና ሕገ-ወጥ ኃብት ወደ ትክክለኛ ሕጋዊ መሥመር ገብቶ በርካታ ኢንቨስትመንት ለመፍጠር እንደሚያስችል አመልክተዋል።

ሥራውን ለማስጀመር ተቋም ተመስርቶ የሕግ ዝግጅቶች በመከናወን ላይ እንደሚገኙና የኢትዮጵያ መንግሥት የኢንቨስትመንት ፈንድና ኃብቶች እንደሚያስተዳድርም ጠቁመዋል።

የካፒታል ገበያው ወደ ሥራ ሲገባ አሰራሮችን ሕጋዊ በማድረግ ብዙ ለውጦችን ያመጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ካፒታል በማሰባሰብ የገንዘብ ሥርዓቱን በአዳዲስ ፈጠራዎች በመደገፍ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ልማት የሚያጠናክር የካፒታል ገበያ ‘በካፒታል ገበያ አዋጅ ቁጥር 1248/2013’ ተቋቁሟል።

በዚህ አዋጅ መሰረት ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሆነ “የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን” መሥሪያ ቤት ተቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል።

የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለሥልጣን የሰነድ መዋዕለ ንዋዮችን በማውጣት የግብይት ሥርዓቱን ፍትኃዊ፣ ቀልጣፋና ግልጽ በማድረግ የተሟላ የካፒታል ገበያ ሥነ-ምህዳር የመፍጠር ሥልጣን ተሰጥቶታል።

ኢንቨስትሮችን በመጠበቅና ከለላ በመስጠት ኢንቨስትመንቱን ለማበረታታት ምቹ ሁኔታን መፍጠርና የካፒታል ገበያውን ተዓማኒነት እንዲኖረው የማድረግ ኃላፊነትም አለበት።

በበጀት አመቱ ስድስት ወራት ከተሰጠው 170 ቢሊዮን ብር ብድር ውስጥ 83 በመቶው ለግል ዘርፍ የተሰጠ ነው

በበጀት አመቱ ስድስት ወራት ከተሰጠው 170 ቢሊዮን ብር ብድር ውስጥ 83 በመቶው ለግል ዘርፍ ተሰጠ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 14ኛ መደበኛ ስብሰባውን ባካሄደበት ወቅት ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከቀረቡት ጥያቄዎች መካከል የኢኮኖሚና የፋይንናስ ጉዳዮች ላይ ያጠነጠኑት መንግስት ለዓመታት የነበሩ የማክሮ ኢኮኖሚ ስብራቶችን ለመጠገን መልከ በዙ ስራዎች እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህም በማክሮ ፋይናንስ ስራዎች ከፍተኛ መሻሻል መታየቱን ጠቅሰው በፊሲካል ፖሊሲ አቅጣጫዎች እና ስራዎች ለአሁን ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ መንግስት የሚተርፉ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።

በፋይናንስ ዘርፉ ረገድ በበጀት አመቱ ስድስት ወራት 100 ቢሊየን ብር ተቀማጭ ገንዘብ መጨመሩን ገልጸዋል።

ጠቅላላ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን ከ1 ነጥብ 2 ትርሊዮን ብር በላይ መድረሱንም አንስተዋል።

በበጀት አመቱ ስድስት ወራት 170 ቢሊዮን ብር ብድር መሰጠቱን ገልጸው ከዚህ ውስጥ 83 በመቶው ለግል ዘርፍ የተሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።

በቀድሞ ጊዜ 70 ከመቶው ለመንግስት ሲሰጥ ከነበረው ብድር አንፃር ለግሉ ዘርፍ ትልቅ እምርታ ነው ብለዋል።

ከሞኒተሪ እና ፊሲካል ፖለሲ የተወሰዱ እርምጃዎች መካከልም ከባድ ጫና ውስጥ የነበሩትን የኢትዮጵያ ንግድና ልማት ባንኮችን መታደግ መቻሉን ለአብነት ጠቅሰዋል።

በኢኮኖሚ ክፍለ ኢኮኖሚ እድገት ደረጃም በግብርና ዘርፍ ባለፈው ዓመትም ሆነ ዘንድሮ ከፍተኛ ዕምርታ መምጣቱን ተናግረዋል።

በኢንዱስትሪው ዘርፍ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱንም ጠቁመዋል።

በትራንስፖርትና በማዳበሪያ አቅርቦት፣ በአይ ሲ ቲ እና ሌሎች ዘርፎች ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል።

በአጠቃላይ ዘንድሮ 7 ነጥብ 9 በመቶ ዕድገት እንደሚጠበቅ ገልጸው ኢትዮጵያ በፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት ላይ ትገኛለች ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአምስት አመታት 9 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር እዳ ከፍላለች – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

አዲስ አበባ፤ ጥር 28/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ከ2011 ጀምሮ በአምስት አመታት 9 ነጥብ 9 ቢሊዮን ዶላር እዳ በመክፈልና የንግድ ብድርን ሙሉ በሙሉ በማቆም ትልቅ ስኬት ማስመዝገቧን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በማብራሪያቸውም የለውጡ መንግስት ባለፉት ዓመታት ካስመዘገባቸው ትላልቅ ስኬቶች ዋነኛው እዳ ላይ የያዘው አቋም ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ስትበደረው የነበረው የንግድ ብድር አራጣ ነበር ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም ልማት ሳይሳካ ሀብታችንን መልሰን ለመስጠትና የእዳ ጫና ላይ የጣለ መሆኑን አስታውሰዋል።

የለውጡ መንግስትም ይህንን በመገንዘብ የንግድ ብድርን ሙሉ በሙሉ በማቆም የነበረውን እዳ በመክፈል ስኬታማ ስራ ማከናወኑን ገልጸዋል።

በዚህም ከ2011 እስክ 2015 ዓ.ም ድረስ 9 ነብጥ 9 ቢሊዮን ዶላር እዳ መክፈል ተችሏል ብለዋል።

ከለውጡ በፊት ከሀገራዊ ጥቅል ምርት 32 በመቶ የነበረው የውጭ እዳ በአሁኑ ወቅት ወደ 17 በመቶ ዝቅ ማለቱን ጠቅሰው በቀጣይ ከ10 በመቶ በታች ለማውረድ እየተሰራ ነው ብለዋል።

የእዳ ሽግሽግ እንዲደረግ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ሆና ላለፉት ሶስት አራት ዓመታት ስትጠይቅ መቆየቷን ጠቅሰው የፈጠነ መላሽ አለመሰጠቱን ተናግረዋል።

ሆኖም እጃችንን መጠምዘዝ የሚፈልጉ አካላት ኢትዮጵያ 33 ሚሊዮን ዶላር የዩሮ ቦንድ ክፍያ መክፈል አልቻለችም የሚል መረጃ እያናፈሱ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ እንኳን 33 ሚሊዮን ዶላር የመክፈል አቅም ልታጣ ቀርቶ በአምስት ወራት ብቻ 7 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር አውጥታ የገቢ ምርት ከውጭ ያስገባች ሀገር ናት ብለዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሁለት ቀን ገቢው ለሆነው 33 ሚሊዮን ዶላር ኢትዮጵያ ይህንን ለመክፈል የምትታማ ሀገር እንዳልሆነችም ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ አቅሙ እያላት መክፈል ያልቻለችው ለምንድን ነው ለሚለው ጥያቄ በሰጡት ማብራሪያም የእዳ ቅነሳና ሽግሽግ ላይ ያቀረብናቸው ጥያቄዎች እኩል ምላሽ እስኪያገኙ ለአንድ ወገን ቀድሞ ላለመክፈል ነው ብለዋል።

ባለፉት 6 ወራት ከ1 ሚሊየን ለሚበልጡ ዜጎች የሥራ ዕድል ተፈጥሯል -ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)

ባለፉት ስድስት ወራት ከ1 ሚሊየን በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል አገኙ

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 14ኛ መደበኛ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የሥራ ዕድል ፈጠራን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ በየዓመቱ ከፍተኛ የሆነ የሥራ ፍላጎት መኖሩን ገልፀዋል።

በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ከ1 ሚሊየን በላይ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ጠቁመዋል።

150 ሺህ የሚሆኑ ዜጎችም በውጭ አገራት የሥራ ስምሪት ማድረጋቸውንም ተናግረዋል።

በዚህም በተለያዩ አገራት ስምሪት ያደረጉ ዜጎች መብታቸውና ክብራቸው ተጠብቆ እንዲሰሩ ጠንካራ ሥራ መሠራቱን አስረድተዋል።

አሁንም በየዓመቱ ካለው ፍላጎት አንጻር ብዙ ጥረት ማድረግ እንደሚጠይቅ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት።

ዜናው የኢዜአ ነው

Exit mobile version