Site icon ETHIO12.COM

ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ለሌላቸውና የተጭበረበር መረጃ ለሚጠቆሙ ሰላሳ ቀን ተሰጠ

“እድሉን ተጠቅመው ወደ ህጋዊ መስመር በማይገቡ ላይ ህጋዊ እርምጃ ይወሰዳል”

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ህጋዊ ምዝገባና የመኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸው በኢትዮጵያ ለሚኖሩ የሌሎች አገር ዜጎች “ወደ ህጋዊ መስመር ግቡ” ሲል ቀድሞ ካስተላለፈው ጥሪ በተጨማሪ የሰላሳ ቀን ገደብ አስቀመጠ። ቀነ ገደቡ ካለፈ አገለግሎቱ በህግ የተሰጠውን አጋብ ተጠቅሞ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል።

ዋና ዳይሬክተር ሰላማዊት ዳዊት የሚመሩት ተቋም ልክ ሌሎች አገሮች እንደሚያደርጉት ህግና ስርአትን በመከተል ከህግ ውጭ የሆኑትን ሁሉ ወደ ህጋዊ መስመር የማስገባት ስራ እንደሚሰራ ቀደም ሲል አስታውቀው ነበር። በርካታ ዜጎችም ህግ አለመከበሩ አገሪቱን ለዝርፊያ፣ ኮንትሮባንድ፣ ወንጀልና አገሪቱን ለገጠማት መተራመስ አንዱ ምክንያት ይኸው ችግር እንደሆነ ጠቅሰው አስተያየት ሲሰጡ ቆይተዋል።

በዚህ መነሻ መንግስት ህገወጥ ያላቸውን አካላት ሲያጤንና መረጃ ሲያሰባስብ መቆየቱን ገልጾ አገልግሎቱ “ተመዝገቡና ህጋዊ ሁኑ” ሲል ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል። በዚህ ጥሪ ኢትዮጵያዊ ሳይሆኑ የኢትዮጵያ ፓስፖርት፣ መታወቂያና ሰነድ የተዘጋጀላቸውን በማስጠንቀቅ ባወጣው የ”ተመዝገቡ” ጥሪ እስካሁን ምን ያህል ራሳቸውን ህጋዊ እንዳደረጉ ይፋ አልተገለጸም።

የኢትዮጵያ ዜግነት ሳይኖራቸው ከተፈቀደላችሁ ጊዜ በላይ በኢትዮጵያ ለቆዩ፣ ሀሰተኛ የትውልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ ይዘው እየተንቀሳቀሱ ለሚገኙ፣ ሀሰተኛ የካምፓኒ ምዝገባ በማድረግ ቪዛ እና የመኖሪያ ፍቃድ ለወሰዱ፣ እንዲሁም ሌሎችም ህጋዊ ያልሆኑ መረጃዎችን ይዘው ለሚንቀሳቀሱ ሁሉ!  ከጥር 1 እስከ ጥር 30 ቀን 2016 ዓ.ም ባሉት 30 ተከታታይ የስራ ቀናት ውስጥ በኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ዋናው መ/ቤት በአካል ቀርበው  ህጋዊ ሰነድ መያዛቸውን እንዲያረጋግጡ የጊዜ ገደብ መሰጠቱ ይታወሳል” ይላል አገለግሎቱ በድጋሚ ያሰራቸው ጥሪ።

“ሆኖም የተሰጠው ጊዜ እንዲራዘም የተለያዩ ጥያቄዎች በመቅረባቸው ተቋሙ ቀኑን ማራዘም አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል። በመሆኑም  አስቀድሞ እስከ ጥር 30 ብቻ የተባለው ለአንድ ተጨማሪ ወር መራዘሙን የኢግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እያሳወቀ በዚህ መሰረት እስከ የካቲት 30 ቀን 2016 ባሉት ተከታታይ የስራ ቀናት በዋናው መ/ቤት በአካል በመቅረብ ወደ ህጋዊ ስርዓት እንዲገቡ ጥሪ የሚያቀርብ ሲሆን  ይህን በማያደርጉ አካላት ላይ ተቋሙ በህግ በተሰጠው ስልጣን መሰረት እርምጃ እንደሚወስድ በጥብቅ ያሳውቃል”

የተራዘመው ጥሪ ” ተባረርን፣ ታሰርን፣ ወደ ማጎሪያ ተላክን” ወዘተ ለሚሉትና ራሳቸውን የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ተቋም በማድረግ የፖለቲካ ቁማር ለሚጫወቱ ጭምር በቂ ግብዓት እንዲሆን አገልግሎቱ ጥሪውን ማራዘሙን አሳውቋቸዋል።

በየተናውም አገራ አንድ የውጭ አገር ዜጋ ህጋዊ ሰነድ ሳይኖረው በሌላ አገር እንደማይኖር ሁሉ፣ በተለይ ለዜጎች በተፈቀዱ መብቶች ሰንድ አጭበርበሮ በማዘጋጀት መገለገል ስለማይፈቀድ ኢትዮጵያም “ስርዓት” ማለቷ ዘግይቶ ካልሆነ በቀር አግባብነቱ አጠያያቂ እንዳልሆነ የህግ ባለሙያዎች መንግስት ወቅሰው በተለያዩ ጊዜያት አስተያየት ሲሰጡ እንደነበር ይታወሳል።

Exit mobile version