Site icon ETHIO12.COM

የፌዴራል ፖሊስ የእገታ ወንጀሎችን ለመከላከል እየሰራ መሆኑን ገለፀ

በሀገሪቱ የሚፈፀሙ የተለያዩ የዕገታ ወንጀሎችን ለመከላከል ከፀጥታ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታውቋል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል ከፋና ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ ከዕገታ ጋር ተያይዞ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ለገንዘብ ወይም ለፖለቲካ ዓላማ ማስፈፀሚያ የሚውሉ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተለያዩ አካባቢዎች ሰዎችን በማገት ገንዘብ መጠየቅ እየተለመደ መምጣቱን ያነሱት ኮሚሽነር ጄኔራሉ÷ ድርጊቱ ማህበረሰቡን ለተለያዩ ቀውሶች እየዳረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ድርጊቱን መንግስት የሚፈፅመው ለማስመሰል በመንግስት የፀጥታ መዋቅር ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦችን በመጠቀም የሚፈፀም መሆኑን በተደጋጋሚ በተደረገ ምርመራ መረጋገጡን አስረድተዋል፡፡

በዚህ የወንጀል ድርጊት የተሳተፉ የፀጥታ አካላት ላይ ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደባቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የፀጥታ መዋቅሩን በገንዘብ በመደለል የራሳቸውን የፖለቲካ ዓላማ ማስፈፀሚያ በሚያደርጉ ግለሰቦች ላይም አስፈላጊው ህጋዊ እርምጃ እየተወሰደባቸው መሆኑንና በቀጣይም የግለሰቦችን ማንነት ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ ገልፀዋል፡፡

በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች አሁንም ይህ ድርጊት ተባብሶ መቀጠሉን የጠቆሙት ኮሚሽነር ጄኔራሉ÷ በድርጊቱ የተሳተፉ ግለሰቦችን ተከታትሎ ለመያዝ እና በእገታው የተከፈለውን ገንዘብ ለማስመለስ እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

የዕገታ ወንጀል ለማስቀረትም ሆነ ድርጊቱን ለመከላከል ወንጀሉ የተፈፀመባቸው ግለሰቦች መረጃውን በሰዓቱ ለፖሊስ ያለማሳወቅ ችግር እንዳለባቸው ጠቅሰው፤ ይህ ደግሞ ወንጀለኞችን ተከታትሎ የመያዝ ጥረቱን አስቸጋሪ እንዳደረገው አንስተዋል፡፡

ህብረተሰቡ መሰል ወንጀሎችን ሲመለከት ጥቆማ መስጠት እና ከፀጥታ መዋቅሩ ጋር በጋራ መስራት እንዳለበትም መልዕክት አስተተላልፈዋል፡፡

በምንይችል አዘዘው fana

Exit mobile version