Site icon ETHIO12.COM

በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች እህልና አልሚ ምግብ እየተጓጓዘ ነው

በትግራይ ክልል በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች ከ23 ሺ ኩንታል በላይ እህልና አልሚ ምግብ እየተጓጓዘ መሆኑን የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ ወደ ትግራይ ክልል ከትናንት ጀምሮ እያጓጓዘ ያለው እህልና አልሚ ምግብ ድሬዳዋ ከሚገኘው መጋዘን መሆኑን የኮሚሽኑ የሎጂስቲክስ አስተዳደር አመራር ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ደምሴ ለኢዜአ ገልጸዋል።

በትግራይ ክልል የተለያዩ ድርጅቶች እያደረጉት ከሚገኙት ድጋፍ በተጨማሪ መንግስት ድርጅቶቹ ባልደረሱባቸው 15 ወረዳዎች ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች ድሬዳዋ ከሚገኘው የእህል መጋዘን እህልና አልሚ ምግብ ማጓጓዝ መጀመሩን አስታውቀዋል።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ የፌዴራል መንግስት ከሚያደርገው ድጋፍ ጎን ለጎን ዲያስፖራውንና ሌሎች አካላትን በማስተባበር ለችግር የተጋለጡ ወገኖች አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያገኙ እየተሰራ ነው።

መንግስት በተለያየ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎችን በጊዚያዊነትና በዘላቂነት እንዲቋቋሙ ለማድረግ ከምንጊዜውም በላይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።

የኮሚሽኑ የዕለት ደራሽ ትራንስፖርት ስምሪት ቁጥጥር ቡድን መሪ አቶ ዘመድኩን ታደሰ እንዳሉት፤ ወደ ትግራይ ክልል 23 ሺ 309 ኩንታል እህል እየተጓጓዘ ነው።

ደራሽ እህሉ በትግራይ ክልል ለሚገኙ ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የሚሰራጭ መሆኑን ተናግረዋል።

በኮሚሽኑ የድሬዳዋ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተፈራ መንገሻ በበኩላቸው ፤ በቅርንጫፍ መጋዘን ውስጥ የተከማቸ እህል ወደ ሰሜኑ የአገራችን ክፍሎች የማጓጓዙ ስራ “በተሳካ መንገድ እየተካሄደ ይገኛል” ብለዋል።

በመጋዘን የተከማቸው እህል በልማታዊ ሴፍትኔት ለተሰማሩት፣ በድርቅና በሌሎች ችግሮች ምክንያት ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች የሚሰራጭ መሆኑን አመልክተዋል።

መንግስት ባለፉት ስድስት ወራት በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግር ድጋፍ ለሚሹ ለ8 ሚሊዮን ወገኖች እህልና አልሚ ምግብ እንዲሰራጭ ማድረጉም ተመልክቷል።

ድሬዳዋ፤ የካቲት 2/2016 (ኢዜአ)

Exit mobile version