Site icon ETHIO12.COM

የዓድዋ መታሰቢያ ሙዚያም ምን ተካቶበታል?

ኢትዮጵያ ነጻነቷን ጠብቃ እንድትኖር ያደረጓት አባቶቻችንን የሚዘክር የዓድዋ ድል መታሰቢያ በአዲስ አበባ ፒያሳ ተገንብቶ ዛሬ ይመረቃል፡፡

መታሰቢያው የተገነባው ጀግኖች ወደ ጦርነቱ ሲተሙ በአንድነት ተሰባስበው ጉዟቸውን የጀመሩበት ቦታ ላይ ነው፡፡

የዓድዋ ድል መታሰቢያ ላይ የሚታየው 00 ኪሎ ሜትር መነሻ ቦታ የኮምፓስ ምልክት በአዲስ አበባ እንዲሁም በመላ ኢትዮጵያ ለሚገኙ ቦታዎች የርቀት መለኪያ መነሻ ነው።

የዓድዋ ድል መታሰቢያ በ5 ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን 5 ወለል እና 8 በሮች አሉት። አጠቃላይ ከታች እስከ ላይ በ5ቱ ወለል ላይ ያለዉ መሬት ስፋት 12 ሄክታር ነው።

ሙዚየሙ ከምድር በታች ያለውን ሁለት ደረጃዎችን ጨምሮ 5 ወለሎች አሉት። ከ1 ሺህ በላይ የመኪና ማቆሚያ፣ ሲሲቲቪ ካሜራ፣የራሱ መቆጣጠሪያ ያለው ስማርት ፓርኪን ሥርዓት አለው፡፡

በአንድ ጊዜ 2 ሺህ 500 ሰዎችን መያዝ የሚችል የፓንአፍሪካኒዝም አዳራሽ፣ 2 ሺህ 300 ሰዎችን መያዝ የሚችል ዘመናዊ ሁለገብ አዳራሽ፣ 4 ሺህ ሰዎችን መያዝ የሚችል የቤት ውስጥ የስፖርት ሜዳ እና አዳራሽ ይዟል።

የህፃናት መጫወቻ፣ የንግድ ሱቆች፣ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳ፣ ካፌና ሬስቶራንት፣ የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ቢሮዎች እና የአርት ጋላሪ አለው።

ለዓድዋ ጦርነት ሰበብ የሆነው የውጫሌ ውል አንቀፅ 17ን እንዲሁም ከድሉ በኋላ የአዲስ አበባ ውል በሚል ኢትዮጵያ እና ጣሊያን ካደረጉት ስምምነት ውስጥ ሁለት አንቀፆች ይገኙበታል። እነሱም ኢትዮጵያ ሉዓላዊ አገር መሆኗን እና የውጫሌ ውል በዚህ ውል መሰረዙን፣ የውጫሌው ውል ምንም የሕግ ውጤት እንደማይኖረው የሚያረጋግጡ አንቀፆች ናቸው።

የዓድዋ ድል ታሪክን የኢትጵዮያዊነት እሴቶችን የሚገልፁ ቅርፃ ቅርፆች፣ የሥዕል ሥራዎች ለእይታ ቀርበዋል።

መታሰቢያው እያንዳንዳቸው 280 ሰዎችን መያዝ የሚችሉ 2 ሲኒማ ቤቶች አሉት። ቤተመጻሕፍት፣የቤት ውስጥ ውድድሮች ሜዳ፣ የህፃናት መጫወቻ ስፍራ እና ጂምናዚየም ተሰርቶለታል።

የምሥራቅ ጀግኖች በር፣ የምዕራብ ጀግኖች በር፣ የሰሜን ጀግኖች በር፣ የደቡብ ጀግኖች በር፣ የፈረሰኞች በር፣ የአርበኞች በር፣ የፓንአፍሪካኒዝም በር ተብለው የተሰየሙ ስምንት በሮች አሉት።

በ4ቱም አቅጣጫዎች የተሰየሙ በሮች በዓድዋ ድል ከአራቱም አቅጣጫ ኢትዮጵያውያን በጋራ የተሳተፉበት የጋራ ድላቸው መሆኑን ያመለክታል፡፡ የአንድነት ድልድይ ሙዚየሙን ከማዘጋጃ ቤቱ ጋር እንዲያገናኝ ታስቦ የተሰራ እና ትናንት ከዛሬ ዛሬን ከነገ ያሚያገናኝ ነው።

የኢትዮጵያ ታሪክን፣ የባህል አሻራዎችን፣ የጦር ሜዳ ስፍራዎችን የሚያሳዩ እና የዓድዋ ድል የክተት አዋጅ የታወጀበት ነጋሪት በነሐስ ተሰርቶ በሙዚየሙ ውስጥ ይገኛሉ።

የዓድዋ ድል መሃንዲሶች አፄ ምኒሊክ እና እቴጌ ጣይቱ ብጡል ሀውልት፣ የ12ቱን የጦር መሪዎች ሀውልት፤ በጦርነቱ የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን እና የቤት እንሰሳት መታሰቢያ የቅርፃ ቅርፅ እና የአርት ሥራዎችንም ይዟል።

በጦርነት ግንባር ከዘመቱ 120 ሺህ ጀግኖች መካከል 45 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን እና በዐውደ ውጊያው ከመሳተፍ አልፈው ምግብ ዝግጅት እና ቁስለኞችን በመንከባከብ ሴቶች ለድሉ ቁልፍ ሚና መጫወታቸውን የሚዘክር ማስታወሻ ተቀምጧል።

የጀግኖች መታሰቢያ ሀውልት ማስታወሻ፣ የዓድዋ ድል ለፓንአፍሪካኒዝም ንቅናቄ ያበረከተውን አስተዋጽኦ የሚዘክር የአፍሪካ ከርታ እና የኅብረቱን አርማ እንደፀሐይ ብርሃን ፈንጣቂ ማሳያ ይዟል።

ከዓድዋ ጀግኖች መታሰቢያ ሐዉልት አጠገብ ደግሞ የአሁኑ ትውልድ በገንዘቡ በጉልበቱ በእውቀቱ ያለምንም ብድር እና እርዳታ በራሱ አቅም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ እውን ማድረጉን የሚያመለክተው ፋውንቴን ተሰርቶለታል።

በነጋሪት ቅርጹ ትይዩ ያለው ስፍራ የዓድዋ ድል በዓል ማክበርያ ቦታ ነው፡፡ መታሰቢያ ዲዛይኑም ግንባታውም የግንባታ ቁጥጥሩም በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች የተሰራ እና የከተማዋን ገፅታ የቀየረ ነው።

በኢትዮጵያ የተሰራችው እና ከ88 ዓመታት ስደት በኋላ ወደ ሀገሯ የተመለሰችው ፀሀይ አውሮፕላን በዓድዋ ድል መታሰቢያ እንድትቀመጥ ተደርጓል።

ታላቁ የሕዳሴ ግድብ እና የዓድዋ ድል ትስስር የዓድዋ ዘመን ትውልድ በአንድነት እና በተባበረ ክንድ የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት አስከብረው ነፃ አገር እንዳስረከቡን ሁሉ የዚህ ዘመን ትውልድ ደግሞ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን በአንድነት እና በተባበረ ክንድ በመላ ኢትዮጵያውያን ርብርብ የኢትዮጵያን ሕዳሴ ያበሰረ የዘመናችን ዓድዋን ገንብቷል። ተምሳሌቱም የአኩሪ ታሪክ ግንባታችን ይቀጥላል የሚል ነው።

በላሉ ኢታላ ኢቢሲ

Exit mobile version