Site icon ETHIO12.COM

ስንዴ በገፍ – ለምን ገበያው አይረጋጋም?

ኢትዮጵያን ከጠብመንጃ ባልተናነሰ የንግድ አሻጥርና የአመራር ዥጉርጉርነት ፈተናዋ እንደሆነ በርካታ አመላካች ጉዳዮች አሉ። በዚሁ የንግድ አሻጥር የተነሳ ህዝብ ክፉኛ መከራውን እንዲያይ ተፈርዶበታል። ስግብግብነትና ሻጥርን የትግል ስልት ያደረጉ በሁሉም አቅጣጫ ከምንም በላይ ህዝብን እየጎዱ እንደሆነ ከአገሪቱ ዙሪያ የሚሰማው ዜና ምስክር ነው።

ጠብ መንጃ ያነገቱ እንዲፈናቀል፣ በንግድ የተሰማሩ እህል በማከማቸት እጥረት ለመፍጠር ተጋምደውና ተናበው እንደሚሰሩ በርካታ መረጃዎች ቢኖሩም ” ከዶሮ ጋር የቆቅ እንቁላል አስታቅፈውናል” የሚለው ብልጽግና ውስጥ የተሰገሰጉ ቁጥጥር አጥበቀው ህገወጥነትን ማስቆም አልቻሉም። አንዳንዴም ፊት ለፊት ተባባሪ የሚሆኑበት አግባብ አለ።

የተቃውሞ ጎራውን ከሚመሩት ጮርቃ ፖለቲከኞች መካከልም ” እህልህን ከዝን፣ ለገበያ አታውጣ” የሚሉ ጥቂት አይደሉም። እነዚሁ ጥቂቶቹ አደባባይ ወጥተው ይናገሩ እንጂ ጀሌዎቻቸው ከስለጠነው ፖለቲካ ይልቅ ሴራና አመጽ ማራባቱ ላይ እየተረባረቡ የህዝቡ መከራ ሆነዋል። አያይዛቸው ገና በዚሁ መንገድ እንደሚገፉበት ነው።

አዲስ ዘመን ፈራ ተባ እያለ ቢጽፍም ያነሳቸው ቁምነገሮችና አበይት ዳያዎች ” የዕህል ዋጋ ንረት እንዴት ሊከሰት ይችላል?” በሚል ጸጉር የሚያስነጭ ነው። ስንዴ በገፍ ስለመመረቱ ምንም ጥያቄ የሚነሳበት ጉዳይ አይደለም። ችግሩ ይህ ሁሉ ምርት ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለስንዴ የምታወጣውን አንድ ቢሊዮን ዶላር ገደማ ከማስቀረቱ ጎን ለጎን ለክ እንደ ስንዴው ምርቱ ርብርብ ተደርጎ ገበያውን ማጥለቅለቅ አልተቻለም የሚለው ነው። ለሁሉም የአዲስ ዘመንን ጽሁፍ ያንብቡ።

… የተመረተው ምርት እንደ ልብ ገበያ ላይ አለመገኘቱና በዋጋም ረገድ መሻሻል አለማሳየቱ አሁን በሸማቹ ዘንድ ያልተፈታ ጥያቄ ሆኗል፡፡ ሆኖም ባለሙያዎቹ ከላይ እንዳብራሩት ከጸጥታ ችግር እና ከግብይት ሰንሰለቱ አለመዘመን ጋር የተያያዙ ችግሮች ለአቅርቦቱም ሆነ ለዋጋ አለመረጋጋቱ ማነቆ እንደሆኑ ተብራርቷል፡፡

ከዓመታት በፊት የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) “ስንዴ የሚባል ነገር ኢትዮጵያ እንዳይገባ ካደረግን ሰባ ፐርሰንት የኢትዮጵያ ችግር ይራገፋል። የኢትዮጵያ ችግር የእርዳታ ስንዴ ነው። ከእርዳታ ስንዴ ጋር በሽታ ይመጣል። ከእርዳታ ስንዴ ጋር ብዙ መዘዝ ይመጣል እሱን ካስቀረን አብዛኛው ችግር ይቀረፋል በማለት ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንትም በተካሄደ 6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 14ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ስንዴ አለ ወይም የለም፤ የት ነው የሚመረተው? የሚል ጥያቄ ከአባላቱ ተነስቶላቸው በሰጡት ምላሽም፤ “አዲስ አበባ ስንዴ የለም፤ ወጣ ስትሉ ግን ሞልቷል፤ ወጣ ብሎ ማየት ነው። እኔ ግን የማየው በየዓመቱ 7 መቶ፤ 8 መቶ ሚሊየን ዶላር ለስንዴ የምናወጣውን ገንዝብ ማትረፋችንን ነው። አሁን ለስንዴ አንድ ብር አናወጣም። አምናም ዘንድሮም አላወጣንም “ ካሉ በኋላ ይህ ውጤት የመጣው ደግሞ መንግሥት ስንዴን ጨምሮ ለተለያዩ የግብርና ምርቶች አርሶ አደሩ የሚፈልጋቸውን የምርጥ ዘርና ማዳበሪያ አቅርቦቶች እንዲሁም ቴክኖሎጂዎች በወቅቱ በማድረስ ድጋፍ እያደረገ በመሆኑና አርሶ አደሩ ስንዴውን ማምረት ብቻ ሳይሆን እየተፈጠረለት ባለው የገበያ ትስስር የኢኮኖሚ ተጠቃሚ መሆን በመቻሉ ነው ሲሉም ተደ ምጠዋል።

የድጋፍና ክትትሉ ሥራ አርሶ አደሩ ወደ ስንዴ ልማት ሥራ እንዲገባ ማስቻሉ፤ ከፍተኛ ጊዜ፣ ጉልበትና ወጪ የሚጠይቁ ምርቶችን በስንዴ በመተካት አዋጪና የተሻለ ምርት እያገኙበት እንደሆነና በኢትዮጵያም ከ1 ሄክታር መሬት ላይ ከ3 ቶን በላይ ስንዴ ምርት እየተገኘ መሆኑንም አብራርተዋል። የስንዴ ኤክስፖርት መጀመሩ አርሶ አደሮች ከእጅ ወደ አፍ የአኗኗር ዘይቤ ተላቀው ወደ ሰፋፊ ልማት እንዲገቡና በታክስ ሥርዓቱ ውስጥ ተካተው የአገር ውስጥ ገቢን ከፍ ለማድረግ የበኩላቸውን እንዲወጡ የሚያስችል ሂደትም መሆኑ ታምኖበት እየተተገበረ ነው።

መንግሥት ስንዴ በስፋት መመረት አለበት በሚል ከበልግ እርሻ ባሻገር በጋ ላይም እንዲመረት ማድረጉ የአገር ውስጥ ምርትን ከመሸፈን አልፎ ኤክስፖርት ወደ ማድረግ ደረጃ መሸጋገር አስችሏል። ይህ ውጤት ለኢትዮጵያውያን በምግብ ራስን የመቻልና ለሌሎች የመትረፍ ጉዞ በይቻላል መንፈስ እንዲያጠናክሩ ጉልበት የሚፈጥር ሆኗል። ለጎረቤቶቿና ለሌሎች አገሮች ደግሞ ተሞክሮ የሰጠ የትጋት ውጤት ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ ነው።

ባለፉት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መሪነት የተሰሩ የልማት ስራዎች የአርሶ አደሩን ሕይወት ከመቀየር ባለፈ ዓለም አቀፍ ተሞክሮ ሆኗል። የበጋ ስንዴ ልማት በኢትዮጵያ ከምርታማነቱ ባሻገር የሥራ ዕድል በመፍጠር አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እያደረገ ይገኛል። አርሶ አደሮች ከግብርና ባለሙያዎች የሚያገኙት ሙያዊ ምክር በስንዴ ልማት ውጤታማ እንዲሆኑ አስተዋፅዖ እያደረገም መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፉት ዓመታት የስንዴ ምርት እንዲያድግ የመስኖ ልማት፣ የግብርና ኤክስቴንሽን ድጋፍ በዘመናዊ መሳሪያ የታገዘ የእርሻ ሥርዓት እንዲዘረጋ እየሰራ መሆኑንና ግብዓቶች እያቀረበ እንደሚገኝ ግብርና ሚኒስቴር በወቅቱ ባወጣው መረጃ አስታውቋል።

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው በኦሮሚያ ግብርና ቢሮ የበጋ መስኖ ስንዴ ልምት ኢኒሼቲቭ አስተባባሪ አቶ ጣሃ ሙሜ እንደሚሉት አሁን ላይ የበጋ ስንዴ ልማት በመላው አገሪቱ በሚባል መልኩ በሰፊው እየተሰራበት ውጤትም እየታየበት ያለ ነው:: እንደ ኦሮሚያ ደግሞ በተያዘው ዓመት ብቻ 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ልማት ስንዴን ለማልማት አቅደን ሰፊ ስራ እየሰራን ነው::

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፉት ዓመታት የስንዴ ምርት እንዲያድግ የመስኖ ልማት፣ የግብርና ኤክስቴንሽን ድጋፍ በዘመናዊ መሳሪያ የታገዘ የእርሻ ሥርዓት እንዲዘረጋ እየሰራ መሆኑንና ግብዓቶች እያቀረበ እንደሚገኝ በወቅቱ ባወጣው መረጃ ማስታወቁ ይታወሳል። አቶ ጠሃም ይህንን ሃሳብ በማጠናከር እንደሚሉት አሁን ድረስ ወደ 2 ነጥብ 78 ሚሊየን ሄክታር መሬት ለማረስ ተችሏል :: ከዚህ አንጻር የሚጠበቀው ምርትም በጣም ሰፊ ነው:: ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት የነበረውን ብናይ 1 ነጥብ 1 ሚሊየን ሄክታር መሬትን ብቻ ነበር በመስኖ ስንዴ ልማት መሸፈን የተቻለው::

አቶ ጣሃ አያይዘውም 2 ነጥብ 6 ሚሊየን ሄክታርን ስናቅድ ወደ መቶ 5 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የስንዴ ምርት ይገኛል ተብሎ የታሰበው:: አሁን ላይ ግን ከሰራነው ስራ ከተሸፈነው የመሬት ስፋት እንዲሁም ከቀረቡት ግብዓቶች አንጻር ውጤቱ እንደሚጨምር መገመት አያቅትም በማለት ይናገራሉ::

ዋናው ነገር መዘራቱ ብቻ አይደለም የሚሉት ኃላፊው የማሳ አያያዙ የተዘራው ሰብል በአግባቡ ውሃ ማግኘቱ አብሮት ከሚዘራው ማዳበሪያ በተጨማሪ በቡቃያ ደረጃ ሲሆን የሚደረግን ማዳበሪያ ሁሉ ማግኘቱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል :: በተመሳሳይ የአረምና የበሽታ ቁጥጥር ማድረግም ለውጤቱ ማማር የበኩሉን አስተዋጽዖ ይኖረዋል:: በመሬት ሽፋን ደረጃ እቅዳችንን አሳክተናል የሚሉት አቶ ጣሃ ከላይ የተገለጹት ነገሮች ላይ አርሶ አደሩና ባለሙያው ትኩረት ሰጥተውና ተቀናጅተው ከሰሩ ውጤቱ ያማረ እንደሚሆንም አብራርተዋል::

ምርቱ በዚህን ያህል ደረጃ ካለ ገበያው ላይ ለምን ዋጋው አልወደረደም ተብለው ለተጠየቁት ሲመልሱም፤ የበጋ ስንዴ ምርት እንደ አገር ሲጀመር መጀመሪያ የአገር ውስጥ ፍጆታችንን ማሟላት ነው፤ ከ 2014 ዓ.ም ጀምሮም ምንም ዓይነት ስንዴ ከውጭ አላስገባንም፤ ትልቁ አላማው ይህ ነበር፤ ይህንን ለማጠናከር ደግሞ ሰፊ ስራ እየሰራን ነው:: በመቀጠል የእኛ ፍላጎት ከተሟላ በኋላ ቀሪውን ደግሞ ወደ ጎረቤት አገራት የመላክ ስራው አምና የተጀመረ ነው:: ይህም ዘንድሮ ላይ በሰፊው የሚሰራበት ይሆናል::

ከውጭ ስንዴን ማስገባት ማቆማችን ራሳችንን የመቻል ምልክቱ ነው ያሉት አቶ ጠሃ ነገር ግን በአገር ውስጥ በሚፈለገው ልክ የስንዴ ምርት እየቀረበ ነው ለማለት የማያስደፍሩ ብዙ ምክንያቶች እንዳሉም ይናገራሉ:: ገበያው ላይ ምርቱ እንደልብ አለመኖር ዋጋው ከጊዜ ወደጊዜ እየጨመረና እየናረ መሄድ ይታያል ይህ ምናልባትም ከአቅራቢው ጋር የሚያያዝ ላይሆን ይችላል ይላሉ::

በምርት ደረጃ በቂ ምርት እየተመረተ እንዳለ ነው የምናምነው የሚሉት አቶ ጠሃ በዚህም ከግብርና ሚኒስቴር ጀምሮ እስከ ታች ያለው መረጃም የሚያሳየው ይህንኑ ነው፤ ነገር ግን የገበያው ስርዓት ምርቱ በአግባቡ ገበያ ውስጥ ተሰራጭቶ ሕብረተሰቡ ጋር እንዲደርስ የሚያስችል አይደለም ብለዋል::

ይህ ምርት በተመረተው ልክ ገበያው ውስጥ ገብቶ እንዳይሰራጭ ያደረገውን የገበያ ስርዓት መፈተሽ በጣም ያስፈልጋል የሚሉት አቶ ጠሃ እዚህ ላይ በአግባቡ ሊታይ የሚገባው ነገር ደግሞ ምርቱ በብዛት ተመርቶ እያለ ያንን ሰብስቦ ከማሰራጨት ይልቅ ማከማቸት መደበቅ እየታየ ስለሆነ በዚህ ላይ የሚመለከታቸው አካላት ሰፊ የቁጥጥር ስራ መስራት መቻል አለባቸው:: ይህ የማይሆን ከሆነ ምርቱ እያለ አቅርቦቱ ከዚህም በላይ ፈተና ውስጥ ሊወድቅ የሚችልበት አጋጣሚ ሰፊ ነው::

እንደ አገር ፍትሃዊ የገበያ ውድድር ኖሮ በዛ መሰረት ዋጋውን ተተምኖ መስራት ካልተቻለ አሁን ዋጋውም ላይ ሆነ አቅርቦቱ ላይ ችግር የሚፈጥሩ አካላት ስላሉ እነሱ ላይ ቁጥጥር ማድረግ ይገባል፡፡ ይህ በአገር ደረጃ መሰራት ያለበት ትልቅ ስራ ነውም ይላሉ::

ለምሳሌ እንደ ኦሮሚያ ክልል የሚመረተውን ሰፊ ምርት ሕብረት ስራ ማህበራት ሰብስበው በአግባቡ ለተጠቃሚው እንዲያቀርቡ የማድረግ ስራ እየተሰራ ቢሆንም እነሱም ጋር የሚታየው የአቅም ውስንነት ሌላ ችግር እየፈጠረ በመሆኑ እነሱን የማጠናከር ከዛ በተጨማሪ ደግሞ አቅም ያላቸው ግለሰብ ነጋዴዎች ስርዓቱን ጠብቀው ገዝተው እንዲያሰራጩ ለማድረግ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ተናግረዋል::

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ ከሸገር ሬዲዮ ጋር ይህንኑ ጉዳይ አስመልክተው እንደተናገሩት ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ላይ ያሳየችው እምርታ ለሌሎች ሀገራት ምሳሌ የሚሆን ነው፡፡ ቀደም ሲል በየዓመቱ ስታወጣ የቆየችውን ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ወጪ ያሰቀረና ሀገሪቱም ሙሉ ለሙሉ በስንዴ ሰብል እራሷን ያስቻለ ነው፡፡ ነገር ግን ከጸጥታ እና ከግብይት ሰንሰለቱ ጋር በተያያዘ የተመረተው ምርት በአግባቡ ሸማቹ ጋር እንዳይደርስ እንቅፋት ሆኗል፡፡ በዚህ ምክንያት የአቅርቦትና የዋጋ መናር ችግር ሊፈጠር ችሏል ብለዋል፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት መንግሥት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማሳደግና ተግዳሮቶቹን ለመፍታት በግብርናው ዘርፍ ከሰራቸው ስራዎች አንዱ የስንዴ ልማት መሆኑ የሚታወስ ነው። መንግሥት በተለይም መስኖን በመጠቀም ስንዴን በዓመት ሦስት ጊዜ ማምረት የሚቻልበትን መንገድ በመፍጠር የአገሪቱን ምርታማነት ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት ማድረጉም በተለያዩ መንገዶች እየተገለጸ ይገኛል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እያደገና በተለያዩ ክልሎች እየተስፋፋ በመምጣቱ ለስንዴ ልማት ጥቅም ላይ የሚውለው መሬት እያደገ መጥቷል። የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት እያደገ መምጣቱ በቆላማ አካባቢዎች የሚገኙ አያሌ አርሶና አርብቶ አደሮች በሥራው ላይ እንዲሰማሩ ውጤታማ ሆነውም በምግብ እህል ራስን የመቻል ጉዞው አካል እንዲሆኑም ያስቻለ ነው።

ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ በ2016 በጀት ዓመት 3 ሚሊየን ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ ሲሆን በዕቅዱ መሠረትም በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አምስት ወራት 2 ነጥብ 4 ሚሊየን ሄክታር መሬት ታርሶ ተዘጋጅቶ 1 ነጥብ 9 ሚሊየን ሄክታር መሬት በዘር መሸፈኑና 117 ሚሊየን ኩንታል ምርት ለማግኘት መታቀዱን ያመለክታል።

ይህንን እቅድም ከግብ ለማድረስ የአፈር ማዳበሪያ፣ የምርጥ ዘር፣ የውሃ መሳቢያ ሞተር (ፓምፕ) እና ሌሎች የግብርና ግብአቶች አቅርቦት እየተደረገ ከመሆኑም ባሻገር የቴክኒክ ድጋፎችም የሚያደርጉ ባለሙያዎች በየአካባቢው ስለመኖራቸው ነው መረጃው የሚያመላክተው።

አገራችን ቀደም ባለው ጊዜ ፍላጎቷን ለመሙላት ለዓመታት ከ700 ሚሊየን ዶላር እስከ 1 ቢሊየን ዶላር በየዓመቱ ለስንዴ ግዥ ወጪ ታደርግ ነበር። ዛሬ ላይ ግን በተሰሩና እየተሰሩ ባሉ ስራዎች አማካይነት ከውጭ አገር ከመግዛት እምርታ ወደመላክ የሚያሸጋግራት መንገድ ላይ ደርሳለች::

ሆኖም የተመረተው ምርት እንደ ልብ ገበያ ላይ አለመገኘቱና በዋጋም ረገድ መሻሻል አለማሳየቱ አሁን በሸማቹ ዘንድ ያልተፈታ ጥያቄ ሆኗል፡፡ ሆኖም ባለሙያዎቹ ከላይ እንዳብራሩት ከጸጥታ ችግር እና ከግብይት ሰንሰለቱ አለመዘመን ጋር የተያያዙ ችግሮች ለአቅርቦቱም ሆነ ለዋጋ አለመረጋጋቱ ማነቆ እንደሆኑ ተብራርቷል፡፡

ስለሆነም እነዚህን ችግሮች መቅረፍና ከተመረተው ስንዴም በዋጋም ሆነ በአቅርቦት ተጠቃሚውን ማርካት እንዲችሉ ያላሰለሰ ጥረትን የሚጠይቅ ነው፡፡

እፀገነት አክሊሉ

አዲስ ዘመን የካቲት 5/2016

Exit mobile version