ETHIO12.COM

” ዐድዋ የኢትዮጵያ ልክም መልክም ነው” ተመስገን ጥሩነህ – ስለ አደዋ – የክልል መሪዎች

ዐድዋ የኢትዮጵያ ልክም መልክም ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ለ128ኛው የዐድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ዐድዋ ሀብት ነው። አባቶቻችን ያቆዩልን ሀብት። በደም ቀለም፣ በአጥንት ብዕር የተጻፈ ቼክ ነው። እየመነዘርን መጠቀም የዚህ ትውልድ ድርሻ ነው ብለዋል።

ኅብረ ብሔራዊ የሆነው የኢትዮጵያ ሠራዊት አንድ ሆኖ ዘምቶ፣ አንድ ሆኖ ተዋግቶ፣ አንድ ሆኖ ድል አድርጓል። ኅብረ ብሔራዊነቱ በጥበብ፣ በዐቅምና በስልት ልዩ ልዩ መንገዶችን እንዲጠቀም ረድቶታልም ነው ያሉት።

አንድነቱ ደግሞ ለአንድ ዓላማ ዘምቶ፣ ለአንድ ዓላም ተዋግቶ፣ አንድ የጋራ ድል እንዲያገኝ አድርጎታል ሲሉም ገልጸዋል።

ልክነቱ ማናቸውንም ችግሮቻችንን አንድ ሆነን ማሸነፍ እንደምንችል ማሳየቱ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መልክነቱ ደግሞ የኢትዮጵያውያንን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት በሚገባ መግለጡ ነው ብለዋል።

ይሄንን ልክና መልክ ጠብቀንና አልቀን በመጠቀም ኢትዮጵያን ከአድዋ ከፍታ በላይ እንደምናደርሳት እምነቴ ነው ያሉት አቶ ተመስገን

መልካም በዓል ይሁን ሲሉም መልዕክታቸውን ቋጭተዋል።

ኦሮሚያ

የዓድዋ ድል ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ ማንነት ግንባታ ትልቅ መሰረት የጣለ ነው ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ 128ኛውን የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓልን አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም የዓድዋ ድል በታሪክ ዓለም የሚያውቀው እና ለሁሉም አፍሪካውያን የነጻነት አርማ ሆኖ እንደሚዘከር አውስተዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን ትክክለኛ ማንነታቸውን የሚናገሩበት እና ጥቁሮች ነጮችን ድል የተቀዳጁበት ሁነት ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

የዓድዋ ድል የኢትዮጵያውያን የምንጊዜም ታሪክ እና ከትውልድ ወደ ትውልድ በኩራት የሚተላለፍ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

የዓድዋ ድል መታሰቢያን ስናከበር ከልዩነት ይልቅ አንድነትን እንዲሁም ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን በማጉላት መሆን እንዳለበትም አጽንኦት ሰጥተዋል ሲል ኤፍቢሲ ዘግቧል፡፡

አማራ

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ለ128ኛ ዓመት የአድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት አስተላልፏል።

ክልልሉ ባስተላለፈው መልእክትም የአድዋ ድል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ክብር ማሕተም፤ የጥቁር ህዝቦች ኩራትና የነፃነት ተጋድሎ አርማ ና አድዋ በሰው ልጆች ታሪክ በዓለም ላይ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ፤ የታላቅ ህዝቦች ታላቅ ድል መሆኑን ጠቅሷል።

መላ ኢትዮጵያውያን ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን ትተው አገራዊ ክብርንና ነጻነትን አስቀድመው በጋራ ዓላማቸው ላይ ከልብ የመግባት ውጤት መሆኑን አንስቷል።

ጀግኖች አባቶቻችን በሀገር ፍቅር ስሜት ለክብርና ነጻነት ሲሉ የደም፣ የአካል ዋጋ ከፍለው ዳር ደንበሯ የተከበረ፤ ነጻነቷ የተረጋገጠ ሀገር ለትውልድ አስረክበዋልም ብሏል።

የዛሬው ትውልድም ከአባቶቹ የወረሰውን የአንድነት፣ የመተሳሰብና ትብብር ስነልቦና ሰንቆ ሰላሟ የጸና በሕብረ ብሔራዊ ወንድማማችነት ላይ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት በሚደረገው ሒደት አርበኛ ሊሆን ይገባል ሲልም መልእክት አስተሏልፏል።

አፋር

ዓድዋ ለመላው ኢትዮጵያውያን እና ወዳጆች የነፃነት፣ የእኩልነትና የአልገዛም ባይነት አርማ ሲሉ የአፋር ክልል ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ ገለጹ፡፡

ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ 128ኛውን የዓድዋ ድል በዓል አስመልክተው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመልዕክታቸውም ዓድዋ ለመላ ኢትዮጵያውያን እና ወዳጆች የነፃነት፣ የእኩልነትና የአልገዛም ባይነት አርማ ከመሆኑ በሻገር ለመላው ጭቁን ሕዝቦች የድል ችቦ የለኮሰ ድል ነው ብለዋል፡፡

ቅኝ ግዛት ከዓለማችን እንዲወገድ ፈር ቀዳጅ የሆነው የዓድዋ ድል ቀንን አስበን ስንውል እኒያ አጥንታቸውን ከስክሰው ደማቸውን አፍስሰው መስዋዕትነት ከፍለው ሀገር ላቆሙ አርበኞቻችን ክብርና ሞገስ በመስጠት ሊሆን ይገባል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በዓድዋ ጦርነት የአፋር ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድም እህቶቹ ጋር ለሀገሩ ተዋድቋል፤ ደማቅ አሻራንም ፅፏል፤ ለዘመናት የሰሜን ምስራቅ በረኛ በመሆን ኢትዮጵያን ለመውረር የመጡ የተለያዩ ሃይሎችን አሳፍሮ፣ ውርደትና ሽንፈትን አከናንቦ መልሷል ሲሉም ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ጉዳይ አሁንም ድረስ የአፋር ህዝብ ጋሻና መከታ ሆኖ የጀግንነትና የአርበኝነት ተምሳሌት ሆኗል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው።

የዛሬው ትውልድ እንደትናንቱ ትውልድ ሁሉ የራሱን ታሪክና አሻራ በማስቀመጥ የትውልድ ቅብብሎሽ ኃላፊነቱን በአግባቡ ሊወጣ ይገባል ማለታቸውን የኢቢሲ ዘገባ ያመላክታል፡፡

ሁሌም ለሀገሩ ቅድሚያ የሚሰጥ፣ በሀገር ጥቅም ጉዳይ ፈፅሞ የማይደራደር፣ ለሀገሩ ሁሌም ዘብ የሚቆም ከታሪከ ተወቃሽነት ነፃ መሆን ይኖርብናል ብለዋል፡፡

የዓድዋ ድል በዓልን ስናከብርም ነጠላ፣ አግላይ እና ከፋፋይ ትርክቶችን ወደ ኋላ በመተው፤ ገዢ፣ አሰባሳቢና ህብረ ብሄራዊነታችን የሚያጠናክሩ ትርክቶችን በማስፋት መሆን እንዳለበትም ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል፡፡

ጋምቤላ

የዓድዋ ድል የሀገር ፍቅር እና አንድነት ለስኬት እንደሚያበቃ ጎልቶ የታየበት ነው ሲሉ የጋምቤላ ክልል ርዕ-መስተዳድር ኡሞድ ኡጁሉ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ 128ኛውን የዓድዋ ድል መታሰቢያ በዓልን አስመልክተው ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት የአድዋ ድል ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ ያስከበረ አኩሪ ታሪካችን ነው ብለዋል።

የዓድዋ ድል የሀገር ፍቅር እና አንድነት ለስኬት እንደሚያበቃ ጎልቶ የታየበት መሆኑን የገለጹት አቶ ኡሞድ ድሉ የመላ ጥቁር ህዝቦች የአሸናፊነት ተምሳሌት እንደሆነም ገልፀዋል።

የዓድዋ ድል ሁሉንም ኢትዮጵያውያን አንድ ከማድረግ ባለፈ ከራስ ፍላጎት ይልቅ የሀገር ፍቅር ቀድሞ የታየበት ትልቅ የአብሮነት እሴት እንደሆነም ርዕሰ መስተዳድሩ ተናግረዋል።

ጀግኖች አባቶች የውጭ ወራሪን አሳፍረው በመመለስ የኢትዮጵያን ክብርና ነፃነት እንዳስጠበቁ ሁሉ የአሁኑ ትውልድም ህብረ ብሔራዊ አንድነቱን በማጠናከር ሀገርን ከድህነት ነፃ ለማውጣት በጽናት እንዲሰራ ጥሪ አቅርበዋል።

በዓሉ ሲከበር እርስ በእርሳችን ያለንን አንድነት በማጎልበትና ሰላማችንን በማጽናት ሊሆን እንደሚገባም አሳስበዋል።

ቤኒሻንጉል

የዓድዋ ድል ኢትዮጵያውያን በጉልህ የሚታወቁበት አንድነት በተግባር የተገለጠበት ድል መሆኑን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሊ ሀሰን ለ128ኛው የዓድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ኢትዮጵያውያን እጅግ አኩሪ ድሎችና ታሪኮች ያሏቸው ህዝቦች ናቸው ሲሉ ቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን ለሀገራቸው ያለ ስስት ራሳቸውን መስጠታቸውንም አንስተዋል።

ኢትዮጵያዊያን እጅግ አኩሪ የሆኑ ድሎችና ታሪኮች ባለቤቶች ናቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ቀደምት አባቶቻችንና እናቶቻችን ለሀገራቸው ያለስስት ራሳቸውን መስጠታቸውንም አንስተዋል።

የዓድዋ ድል ሲነሳ ከሁሉም የሚያስደንቀው ኢትዮጵያውያን በጉልህ የሚታወቁበት አንድነት በተግባር የተገለጠበት ድል መሆኑንም አቶ አሻድሊ ተናግረዋል።

የዘንድሮውን 128ኛው የዓድዋ ድል በዓል ከመቼውም ጊዜ ለዬት የሚያያደርገው አባትና እናቶቻችን ያኖሩልንን ታሪክ የሚመጥን የዓድዋ ድል መታሰቢያ ተገንብቶ በተመረቀበት ማግሥት የሚከበር መሆኑ ነው ብለዋል።

የአሁኑ ትውልድ ለሀገር ሉዓላዊነት ሲባል ኢትዮጵያዊያን በዓድዋ ድል የገለጡትን እውነተኛ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት በአግባቡ መረዳትና መጠቀም ይኖርበታል ብለዋል።

ለዓድዋ ድል መመዝገብ ኢትዮጵያዊያን ከመላው የሀገሪቱ ክፍሎች ዘምተዋል ያሉት አቶ አሻድሊ፣ በዚህ ድል ውስጥ ሀገርን ማስቀደም በጉልህ እንደሚታይም በመልዕክታቸው ጠቅሰዋል።

የዓድዋ ድል አስደናቂነት፣ ድምቀት፣ ታሪካዊነትና አኩሪነት ሚስጥሩ በኅብረ ብሔራዊነት የተገኘ መሆኑ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ትውልዱ በዚህ ድል ውስጥ የተከፈለውን መስዋዕትነት ሁሌም ማሰብ፣ ለትውልድ መዘከር እንደሚጠበቅም ነው ያስረዱት።

ሀገራችን አሁን የጀመረቻቸው አስደናቂ ስኬቶቿን ለማስቀጠል፣ ለቀጣዩ ትውልድም የተሻለች ሀገር ለማስረከብ ሁላችንም ኃላፊነታችንን መወጣት ይጠበቅብናል ሲሉ ጥሪ ማቅረባቸውን የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመለክታል።

ሲዳማ

የአድዋ የድል በዓል የመላው ኢትዮጵያውያን ህብረትና አንድነት ፤ ቆራጥነትና ጀግንነት የታየበት ነው ሲሉ የሲዳማ ክልል ርዕሰ-መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ 128ኛውን የዓድዋ ድል በዓልን አስመልክቶ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት በዓድዋ ያገኘነውን አሸናፊነት አስቀጥለን ድህነትን በማሸነፍ ትውልዳችንን ወደ ብልፅግና ከፍ እናደርጋለን ብለዋል።

በመልዕክታቸውም፤ የዓድዋ ድል የነጮች የበላይነትንና የቅኝ አገዛዝ ሥርዓትን የሚያቀነቅኑትን ያሳፈረና ያስደነገጠ መሆኑን አስረድተዋል።

ድሉ የኢትዮጵያን ልዕልና ያስጠበቀ፣ የህብረ ብሔራዊት ኢትዮጵያ አንድነትና ጀግንነት የተንፀባረቀበት፣ የአፍሪካዊያንን የአሸናፊነት ስነ ልቦና ከፍ ያደረገ እንደሆነ ተናግረዋል።

አውሮፓውያን የቅኝ አገዛዝ ፖሊሲ በኢትዮጵያ ላይ ሊሳካ ያልቻለው አባቶቻችን በአንድነትና በህብረት፣ በቆራጥነትና በጀግንነት ባደረጉት ተጋድሎና በከፈሉት መስዋዕትነት ነው ብለዋል።

ድሉ ጥቁር ህዝቦች ታግሎ ማሸነፍ እንደሚቻል ተስፋን እንዲሰንቁና ብሎም ለነፃነታቸው እንዲታገሉና አሽናፊነትን እንዲጎናፀፉ ያስቻለ እንደሆነ አንስተዋል።

ይህ ትውልድ ዛሬም ዘመናዊ የቅኝ አገዛዝ ሥርዓትን ማሸነፍ የሚችለው ድህነትንና ኋላቀርነትን አሸንፎ ሀገራችንን የብልፅግና ከፍታ ላይ ሲያሻግር ነው ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ አመላክቷል።

የዓድዋ ድል ሲታሰብ ህብረብሔራዊ አንድነትን፣ ወንድማማችነትን፣ ህብረትን፣ ቆራጥነትን፣ የአላማ ፅናትን፣ ጠንካራ ስነልቦናን፣ ጀግንነትን፣ ድልና ድምቀትን፣ ነፃነትን፣ የያዙ ታሪካዊ አውዶች በኢትዮጵያዊያን ውስጥ እንደሚታወሱ ገልጸዋል።

ድሉ የኢትዮጵያዊነታችንን ሃያልነት በትውልድ ቅብብሎሽ ውስጥ ህያው ሆኖ እንዲኖር ያደርጋል በማለት ገልጸው፤ በዓድዋ ያገኘነውን አሸናፊነት አስቀጥለን ድህነትን በስራና በቆራጥነት አሸንፈን ትውልዳችንን ወደ ብልፅግና ማማ ከፍ እናደርጋለን ብለዋል።

ማዕከላዊ ኢትዮጵያ

ታላቁ የዓድዋ ድል በዓል ከታላቅ የገድልና የጀግንነት ታሪክ አሻራነቱ ባሻገር፣ ለአዳዲስ ሀገራዊ ስኬቶች መነቃቃትን የሚፈጥር ነው ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው 128ኛውን የዓድዋ ድል በዓል በማስመልከት ባስተላለፉት መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም ታላቁ የዓድዋ ድል በዓል ከታላቅ የገድልና የጀግንነት ታሪክ አሻራነቱ ባሻገር፣ ለአዳዲስ ሀገራዊ ስኬቶች መነቃቃትን የሚፈጥር፣ የሀገር ፍቅርንና የአንድነትን እሴቶችን ሸማ የሚያጎናጽፍ መሆኑን ገልጸዋል።

የዓድዋ ድል በዓልን ስናከብር ሉዓላዊነትን፣ ብሔራዊ ጥቅምንና ብሔራዊ ክብርን በጋራ የማፅኛ እሴቶችን ከቀደምት አባቶች እና እናቶች ምግባር እየተማማርን መሆን ይኖርበታል ብለዋል።

የዓድዋ ድል ልዩነቶችን በመሻገር ሀገርን የማፅናት አስተምህሮ የሚያስተላልፍልን በመሆኑ ጥቃቅን ልዩነቶችን በመሻገር ትልቁን ምስል ማለትም ኢትዮጵያን የማፅናትና የማበልፀግ ራዕይ ሰንቀን በጋራ ወደ ፊት መራመድ ይኖርብናል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ አውስተዋል።

ኢትዮጵያ የብዝሃነት ሀገር መሆኗ ኢትዮጵያዉያን ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት፣ ለብሔራዊ ጥቅሟና ክብሯ ዘላቂነት በጋራ ከመሰለፍ እንዳልገታቸዉ የዓድዋ ድል ህያዉ ምስክር መሆኑን ጠቁመዋል።

የዓድዋ ድልን እሴቶች ስንቅና መርህ አድርገን በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ መትጋት አለብን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ለሕብረ ብሔራዊ ወንድም/እህትማማችነት እሴት ማበብ መሥራት ይገባል ማለታቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል።

ለዚህ ድል ያበቃን ጥልቅ የሀገር ፍቅር፣ የዓላማ ጽናት፣ መተሳሰብ እና አንድነታችን ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ጀግኖች አባቶቻችን በክብር ያቆዩልንን ታላቅ ሀገር የአሁኑ ትውልድ ከአያቶቹ የወረሰውን የጀግንነት ታሪክ ጠብቆ ማቆየት እንዳለበትም በመልዕክታቸው ጠቁመዋል።

የቀደምት አባቶቻችንንና እናቶቻችንን የዓድዋ ድል ዐሻራ፣ የዛሬዉን ሀገራዊ ፈተናዎች በማሸነፍ የኢትዮጵያንና የህዝቦቿን ሁለንተናዊ ለዉጥ እዉን ለማድረግ የብርታትና የፅናት ምንጭ አድርገን መጠቀም ይኖርብናል ሲሉም አክለዋል።

ሠለማችንን በማፅናት፣ ፀጋዎቻችንን በማልማት፣ ልዩነቶቻችን በሀሳብ የበላይነት መርህ በመዳኘት የኢትዮጵያን ብልጽግና እዉን ለማድረግ በጋራ እንሠለፍ ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ደቡብ

ዓድዋ የመላው ኢትዮጵያውያን ጀግንነትን በደማቅ ቀለም የጻፈ፤ የአሸናፊነት የጋራ አኩሪ ታሪካችን ነው ሲሉ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ገለጹ።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ጥላሁን ከበደ ለ128ኛው የዓድዋ ድል በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልዕክታቸውም ዓድዋ የመላው ኢትዮጵያውያን ጀግንነትን በደማቅ ቀለም የጻፈ፤ የአሸናፊነት የጋራ አኩሪ ታሪካችን ነው ብለዋል።

የዓድዋ ድል መላ ኢትዮጵያውያንን ከዳር እስከ ዳር በላቀ የሀገር ስሜት፤ ወኔ እና ጀግንነት በማሰባሰብ በተባበረ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የጣሊያን ወራሪ ኃይል ጀግኖች አባቶቻችንና እናቶቻችን ድል ያደረጉበት በዘመን የማይደበዝዝ ዘላለማዊ ክብር እና ኩራት ያጎናጸፈን የአሸናፊነት የጋራ አኩሪ ታሪካችን ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ድሉ ከኢትዮጵያውያን አልፎ ለመላው ጥቁር ሕዝቦች የነፃነት ጎህን የቀደደ ነው ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው።

አባቶቻችን ከልዩነቶች ይልቅ የጋራ ሀገራቸውን በማስቀደም በአንድ ዓላማ ጸንተው በአንድነት እና በጀግንነት ያደረጉት ተጋድሎ ሉአላዊነታችንን ሳናስደፍር በነፃነት እንድንኖር አስችሎናል ብለዋል፡፡

የዘንድሮው የዓድዋ ድል በአል የዐድዋ ድል መታሰቢያ በብሄራዊ ደረጃ ተገንብቶ በተጠናቀቀበት ወቅት መከበሩ በዓሉን ይበልጥ ደማቅና ታርካዊ ያደርገዋል ሲሉም አክለዋል፡፡

መታሰቢያው ሀገራችን ትናንትን የሚያስብ፣ የአባቶቹን አንፃባራቂ ድል በልኩ የሚዘከር እና ከአባቶቹ የአርበኝነት እሴት ወርሶ አርበኛ ለመሆን የሚተጋ ትውልድ ባለቤት መሆኗን ያሳየ ነው ብለዋል።

ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን በአንፃባራቂ ድል የደመቀበት የዐድዋ ድል መታሰቢያ ስናከበር በድሉ እየኮራን የማይቻል ከሚመስለው የአባት የእናቶቻችን የአንድነትና የአልሸነፍ ባይነት የተጋድሎ ታሪክ ትምህርት በመውሰድ በአንድ ልብ ከተነሳን ድህነትን ድል ነስተን ብልጽግናችንን በማረጋገጥ ዳግም አዲስ ታሪክ ከመጻፍ የሚያግደን ምንም ኃይል አለመኖሩን በመገንዘብ ጭምር ሊሆን ይገባል ሲሉም ገልጸዋል።

በመጨረሻ መላው የክልላችንና የሀገራችን ህዝቦች እንደ ሁልጊዜው ለጋራ ቤታችን አንድነት፣ ልማት እና ለህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት ፋይዳ ያላቸው አካባቢያዊና ሀገራዊ የልማት ስራዎች የሚጠበቅባችሁን በማድረግ ዳግም የሀገር አለኝታነታችሁን እንድታስመሰክሩ በአደራ ጭምር ለማሳሰብ እወዳለሁም ብለዋል።

ሃረሪ

የሀረሪ ክልላዊ መንግሥት ለመላው ለኢትዮጵያ ና ለክልሉ ህዝብ እንኳን 128ኛው የዓድዋ ድል አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መልዕክቱን አስተላልፏል።

የአፍሪካ የነፃነት አርማ የሆነው የዓድዋ ድል በመላው የሀገራችን ህዝቦች የህይወት መስዋዕትነት የተገኘ ታላቅ ድል ነው ብሏል።

ጀግኖች አባቶች በአድዋ ጦርነት የውጪ ወራሪን በድል አድራጊነት ያሸነፉት በጀግንነታቸው፣ በአንድነታቸውና በዓላማ ጽናታቸው መሆኑን አስፍሯል።

ጀግኖች አባቶች የውጪ ወራሪን አሳፍረው በመመለስ የኢትዮጵያን ክብርና ነፃነት እንዳስጠበቁ ሁሉ የአሁኑ ትውልድም ህብረ ብሔራዊ አንድነቱን በማጠናከር ሀገርን ከድህነት ነፃ ለማውጣት በጽናት እንዲሰራ የክልሉ መንግሥት ጥሪውን አቅርቧል ።

የአድዋ ድል ለኢትዮጵያውያን ጽናትን፣ በዘመን የማይሸረሸር ጀግንነትን፣ ክብርን፣ ነፃነት፣ አንድነትንና መሰል ቱሩፋቶችን ያጸና ደማቅ ታሪክ በመሆኑም የዓድዋን የድል በዓል ስናከብር በእኩልነት፣ በአብሮነት፣ በፍቅር እና በመተሳሰብ ሊሆን ይገባልም ነው ያለው።

በዓሉን ስናከብርም ሀገራችን የጀመረችው የልማትና የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታን በማጠናከር እንዲሁም እርስ በእርሳችን ያለንን አንድነት በማጎልበት አባቶቻችንን ለዚህች ሀገር ሲሉ ለከፈሉት ዋጋ ክብር በመስጠት ሊሆን ይገባል በማለት እክሏል።

ዘላለማዊ ክብር ለኢትዮጵያውያን፣ ለአፍሪካም ሆነ የመላ ጥቁር ህዝብ የኩራት ምንጭ ለሆኑ ለአድዋ ጀግኖች ይሁን ሲል መልካም ምኞቹን ገልጿል።

Exit mobile version