Site icon ETHIO12.COM

አደዋ መንፈስ ነው ይጋባብን!!

የዓድዋ ድል በ”አይቻልም” ውስጥ “ይቻላልን”፣ በከበባ ውስጥ ሰብሮ መውጣትን በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ብርሃንን ለዓለም ያሳየንበት በመሆኑ ድሉ የዓለም ጥቁር ሕዝብ ሁሉ ድልና የነጻነት ትግል አዋላጅ ነው። እኛ ብቻ ሳንሆን የዓለማችን ጥቁር ሕዝብ ሁሉ በኩራት ምስክርነት የሚሰጡለት የነጻነታቸው ማተብ አድርገው የሚምሉበት የቃልኪዳናቸው ምልክት ነው። ይህን ምልክት ማራከስ፣ ማጠልሸትና በየዘመኑ በሚነሳ የፖለቲካ ሽኩቻ ለውሶ ማጣጣል ከታላቅ ይቅርታ ጋር ድንቁርና ነው። ባንዳነት ነው።

በዛ ዘመን፣ በዛ መገናኛ ባልነበረበት ጊዜ ስፍራ ተጠያይቀውና ተጠራርተው የተገናኙ ጀግኖች ማሰብ በራሱ ብቻውን ሃሴት ይሰጣል። የቀደሙት ጀግኖቻችንን የጽናት ደራጃ፣ የዓላማ ቁርጠኛነት፣ ከምንም በላይ ለአገራቸው ያላቸውን ክብርና ” አልገዛም” ባይነት ጥልቀቱን ያስተምራል። እናም አደዋ ማህተብ፣ አደዋ ረቂቅ፣ አደዋ ህብር፣ አደዋ የታሪኮቻችን ሁሉ ቁንጮ፣ አደዋ የዛሬዋ ኢትዮጵያ መሰረት፣ አደዋ የጥቁሮችን የነጻነት ትግል ያቀጣጠለ ወዘተ በሚል የምንዘክረው!!
የኢትዮጵያ የማህጸኗ ትክክለኛ ልጆቿ የህን ወርቅ፣ ከወርቅም በላይ ዕንቁ የሆነ ታሪክ ለመዘከር ከዳር እሰከዳር ሲነሱ፣ ይህን ታላቅ ቃላት ሊገልጹት የማይቻላቸውን ታሪክ ለማበሻቀጥና ለማራከስ የሚደክሙ በየስርቻውና በማህበራዊ ሚዲያዎች ሲርመጠመጡ ይታያል።
እነዚህ በግል ወይም በቡድን ወይም በባዕዳን ትዕዛዝ፣ ወይም በባንዳነት፣ ወይም በቀትረ ቀላልነት፣ ወይም ባርነትን ጌጥ በማድረግ ወዘተ ተርታ የሚሰለፉ የኢትዮጵያ እንግዴ “ልጆቿ” መላ ጥቁር ህዝብን አንድ ባደረገ ታሪክ ከመኩራት መረከስን መርጠዋል። ከማናቸውም የፖለቲካም ይሁን ሌላ ጥያቄ ሳቢያ ለጊዜው አብሮ ማክበር ባይቻል እንኳን፣ አደዋ ላይ መዝመት አስነዋሪ ነው።
አደዋን ለማራከስ የሚታትሩ ሌላ በክፍያና ራሳቸውን በመሸጥ ሳያምኑበት የሚያደነቁትና የሚያሞግሱት ጉዳይ ስለተሰራላቸው ነው። በዚሁ የመሸጥ መነሻቸው በሽያጭ ስሜት ሆነው የሚያሞግሱትን ለማንገስ የሚሄዱበትን ርቀት አስበልጠው የሚያጠለሹትን ለማራከስ ይተጋሉ። ከሚሰጣቸው ላይ ቆርተው ይበጅታሉ። ይመነዝራሉ። ዛሬ ላይ ከተለያዩ ጽንፎች የሚሰማው እንዲህ ያለው የዘመን መዥጎርጎር በአደዋ የምንኮራበትን ያህል በእንዲህ ዓይነቶቹ እንዳናፍር ያስገድደናል።
ሃቁ ግን ምን ይባል ምን፣ ተወደደም ተጠላም፣ አደዋ ልዩ ቀን መሆኑ ነው። ምክንያቱምቱም አደዋ የሚጋባ መንፈስ ነው። አደዋ ሃያልነት፣ የስነልቦናችን መሰሶ፣ የአንድነታችን ሚስጢር፣ የጽናታችን ማሳያ፣ የፍትህ አርበኞች ለመሆናችን ምስክር ወዘተ ነው። ጎረቤቶቻችን በነጭ ወራሪዎች ሲገረፉበት የነበረውን አለንጋ ከሞራል ውድቀታቸው ጋር ለትውልድ ሲያወርሱ እኛ ምስጋና “ቀንበርን አንቀበልም” ላሉ የኢትዮጵያ ልጆች ገድል ይሁንና ኩራትና ጀግንነትን ወርሰናል።
ጀግኖቻችን ነብሳቸው በአጸደ ገነት ይረፍልን!! መንፈሳቸው ይጋባብን!! የጥቁር ሕዝብ ሁሉ ታሪክ የሆነው የዓድዋ ድል ታሪክ በየዕለቱ የሚሰበክበትንና ለመጪው ትውልድ እና ለዓለም ሁሉ የሚተረክበትን መታሰቢያ ሙዚያም መሰራቱን ተሰርቶልናል። እናመሰግናለን። ምክንያቱም ለትውልድ ያስፈልጋልና!!
በዚህ የታሪክ ባሕር ውስጥ ትውልድ ሁሉ የአንድነትን፣ የመተባበርን ፍሬ እየተመገበ አዲሷን ኢትዮጵያ በዚሁ መንፈስ ላይ ታንጾ ይገነባል የሚል እምነት አለን። “የተጽዕኖ እጆቿን በዓለም ሁሉ የምታሳርፍ፣ ለሰው ልጅ የሕይወትን፣ የሰላምን እና የፈጣሪን መንገድ የምታሳይ አዲስ ኢትዮጵያ፣ አዲስ አፍሪካ ትታየናለች” ሲል እውቁ የጥቁር መብት ተሟጋች ጃማይካዊው ማርከስ ጋርቬይ የጥቁር ሕዝብን የወደፊት ተስፋ የዓድዋን ድል ወደኋላ በመመልከት ምስክርነት መስጠቱን እዚህ ላይ ማስታወስ ግድ ይላል። ከዓለም ልዩ ያደረገንን ድል ለማራከስ የሚሯሯጡ ያራሳችን ሰዎች (ቅጥረኞች) አይተንና ሰምተን እንዲህ ያሉትን አረቆ አስተዋዮች ስናስብ የአደዋ ሃይል ጎልቶ እንዲታየን ያደርጋል።
በርካቶች የአደዋ ሚስጢር ገብቷቸው አዲሲቷ ኢትዮጵያ በአደዋ መንፈስ ልትተከል እንደሚገባት ቀድመው ጽፈዋል። መስክረዋል። ኢትዮጵያ አሁን ድረስ የነጮች ጫናና በትር የሚጠናባትም በዚሁ የአደዋ ደማቅ ታሪካችን ሳቢያ ስለመሆኑም ምስክረነት ሰጥተዋል። ወራሪዎች ሽንፈታቸውን እያሰቡ በገዟቸው ባንዶች፣ ለአፈናና ለጭቆና ባቋቋሟቸው ተቋማት ኢትዮጵያን ለማነቅ ሌት ተቀን የሚሰሩት፣ እየሰሩ ያሉትና በቅርቡ ሲፈጽሙ የነበረው ሁሉም መነሻው የአደዋ ድል ስለመሆኑ ምስክር ባይኖርም ትውልድ ሁሉ ያውቀዋል።
የአንድነት ማሳያና ከአንድነት ውጭ አንዳችም ዓይነት አማራጭ እንደማይሆንልን አጽንቶ ያስተማረን ዓድዋ፤ የኢትዮጵያ፣ የአፍሪካና የዓለም ጥቁር ሕዝብ ሁሉ ድል ስለመሆኑ መከራከሪያ የለውም። ለዚህም ነው በርካታ የአህጉራችን ታላላቅ ሰዎች “የዓድዋ ድል የአፍሪካ ድል ነው፤ የራሳችን እናድርገው፤ እንውረሰው” ሲሉ የሚደመጡት።
ስለዚህ የትም ብንሆን አደዋ ማህተብ ነው። ይከበራል። ይዘከራል። ሁላችንም በውል እንደምንረዳው አገራችን ላይ የሚካሄደውን ደባ ጨምሮ ዓለም ለጥቁሮች ጨለማ ነች። ክፉ ነች። አድሏዊ ናት። ፍትሐዊ አይደለችም። ሰብዓዊነት ይጎድላታል። ምሕረት አልባም ናት። ክፋቷ ተዘርዝሮ አያልቅም። ግራ ቀኙን ብናይ ወለል ብሎ የሚታየን የዓለም ፍትህ አልባ መሆኗ ብቻ ነው። በተለይ ለጥቁሮች ጸያፍ ናት። ዓለም ለጥቁሮች መሥፈሪያ አበጅታለች፤ ወደላይ ልቀው እንዳይሄዱ መገደቢያ ጣሪያ ሠርታለች፤ ሸብባ የምታስቀምጥበት አጥርም አዘጋጅታለች። ይህንን ሁሉ የዓለም ወጥመድ፣ የክፋት ሤራና መሥፈሪያ አልፎ መውጣት የቻለው ግን የዓድዋ ድል ብቻ ነው። ድሉም ጊዜያዊ ሳይሆን ለሌሎች ሁሉ ለዘመናት ሲተላለፍ የሚኖር፣ የጸና፣ የማይናወጥ፣ ሕያው በመሆኑ ዓድዋን ከሁሉም ድሎች ልዩ ያደርገዋል። መንፈሱ ይጋባብን የምለውም ለዚህ ነው።
የዓድዋ ድል በ”አይቻልም” ውስጥ “ይቻላልን”፣ በከበባ ውስጥ ሰብሮ መውጣትን በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ብርሃንን ለዓለም ያሳየንበት በመሆኑ ድሉ የዓለም ጥቁር ሕዝብ ሁሉ ድልና የነጻነት ትግል አዋላጅ ነው። እኛ ብቻ ሳንሆን የዓለማችን ጥቁር ሕዝብ ሁሉ በኩራት ምስክርነት የሚሰጡለት የነጻነታቸው ማተብ አድርገው የሚምሉበት የቃልኪዳናቸው ምልክት ነው። ይህን ምልክት ማራከስ፣ ማጠልሸትና በየዘመኑ በሚነሳ የፖለቲካ ሽኩቻ ለውሶ ማጣጣል ከታላቅ ይቅርታ ጋር ድንቁርና ነው። ባንዳነት ነው።
ዓለም አብሮና ተባብሮ እንዳንችል ሊያደርገን፣ ሊያሽመደምደን፣ አጥሮ ሊያስቀምጠን ሲል “እችላለሁ፣ በእናንተ መሥፈሪያ አልሰፈርም፣ ዙሪያዬን ብታጥሩትም ሰብሬ እወጣለሁ፣ ጨለማችሁን በደማቅ ብርሃን እለውጣለሁ” ማለትን ያስተማረው የዓድዋ ድል ኢትዮጵያ የጥቁር ሕዝብ መሪ አገር መሆኗን የሚያረጋግጥ ሐቅ ነው። ሲቀጥልም የኢትዮጵያ ሕዝብ የዓለም የጥቁር ሕዝብ ሁሉ መሪና አቅጣጫ ጠቋሚ መሐንዲስ መሆኑን የሚያስረዳ ነው። ለዚህ ነው ዓድዋ ፓን አፍሪካኒዝም የሆነው። የጥቁር ሕዝብ ትግል ወደላቀ ደረጃ፣ ወደ ድል፣ ወደ ስኬት እንዲደርስ ያደረገ የነጻነት ገድል ነው።
በአፍሪቃም ሆነ በዓለም ዙሪያ የነጻነት ፍልሚያን ጸንሶ ያዋለደ የአባቶቻችን ወደር የለሽና የላቀ ጀግንነት ነው ዓድዋ!! ይህ ታሪክ በግልና በቡድን የፈጠራ ትርክት ለማሳነስ መሞከር በጥንት አባቶቻችን ደም እየዋኙ፣ አጥንታቸው ላይ የጠላትን አታሞ እየደለቁ የመደነስና የማሽካካት ያህል ” ለሌላ አዳሪነት” ነው።
ዓድዋ ግዙፍ፣ ወጋገኑ ዓለምን የሚያዳርስ፣ መንፈሱ የሚያበራ በመሆኑ ነው የአፍሪካ ኅብረትን በአዲስ አበባ የተከለው። የኩራታችን ማማ ነው ብለን በኩራት የምንናገረው። የሚጫንብንን ቀንበር አሽቀንጥረን በመጣል “ጠፉ” ስንባል የምናብበው በዚሁ መነሻና መዳረሻችን በሆነው የአደዋ መንፈስ ነው።
ይህን ልዩ ማተባ ለልጅ ልጅ ማሳለፍ ታላቅ ጉዳይ ነውና አደዋን በአደባባይ ብቻ ሳይሆን በቤተሰብ ደረጃም ማሰብና ማክበር ግድ ነው። ሚስጥሩን ለቤተሰብ በመግለጽ አንድ ለመሆን አጋጣሚውን መጠቀም ይገባል። አገር መውደድ የሚተከለው ቤተሰብ ውስጥ ነውና።
ድል ቢያብር እንዲሉ በአንድነት በርካታ ስብራቶቻችን ይጠገናሉና!! “ይህን ደማቅ የኢትዮጵያ ታሪክ፣ በዓመት አንድ ጊዜ ቀን ጠብቀን ከምናከብረው ይልቅ ዕለት ዕለት እንዘክረው፣ እንማርበት፣ ጥሶ የመውጣትና የይቻላል መንፈስን ለአዲሱና ለመጪው ትውልድ በተግባር እናሳይበት።
አዲስ የታነጸው የአደዋ መታሰቢኡይ ሙዚየም በዘርና በብሄር የፖለቲካ መርዝ ለተጠመቁ ሁሉ ፍቱን መድሃኒት ነውና በየዕለቱ እንማርበት። ጥናትና ምርምር እየተደረገ ይዳብር። በዓመት አንዴ መሰብሰብ ሳይሆን ሁሌም አደዋ ይከበር!! መንፈሱ ይጋባብን!!
የአድዋ መንፈስ ሲጋባብን፣ ብዙ ጉዳዮችን አንድ ሆነን እንሻገራለን!! የአፍሪካ ልጆች የታሪክ ድህነት ያጠቃቸው፣ የሽንፈት ሰለባዎች፣ የአእምሮ ሽባዎች ሳይሆኑ ድል ለመንሣት የተወለዱ የድል አድራጊ ልጆች መሆናችውን መጥተው የሚማሩት ኢትዮጵያ በገነባችው ሙዚየም ነው። ምክንያቱም ዓድዋ የባሪያ ሥርዓትን፣ የአውሮጳን ቅኝ አገዛዝን፣ አስከፊው አፓርታይድን ያመከነ ገድል በመሆኑ የዘመናችንን ግፍና ጭቆና ድል መንሳት የሚቻለው በዓድዋ መንፈስ ነው ብለን በየዕለቱ ማስተማር እንዲያስችል በመደረጉ ነው።
በጸዳ አዕምሮ ለምናስብ የዘንድሮው አደዋ ልዩ የሚሆነው እዚህ ላይ ነው። አድዋ ዕለት ዕለት ተማሪዎች፣ አዲስ ትውልድ ትምህርት የሚቀስምበትና አገሪቱን እየበላ ያለውን የዘርና የብሄር መርዝ የሚያራግፉበት ማዕከል ሆኗል።
ኢትዮጵያ የተረጫባትን የዘር መርዝ ታመክን ዘንዳ የዓድዋ ድልና የድሉ አዝማችና ዘማቾች፣ የደጀኑ ጋሻነት፣ የአንድነቱ ከብረት የጠነከረ መሆን፣ የ“አልገዛም” ባይነቱ ዕልህ ዋጋ ውድ በመሆኑ ትውልድ ኮርቶ ታሪኩን ልቡ ላይ እንዲያትም የታነጸው ሙዚያም ዘገየና አነሰ ካልተባለ በስተቀር አይበዛም። ይህንሰሩና አሳቡን ያመነጩ ሁሉ ታላቅ ምስጋና ይገባቸዋል። ግን ሊኩራሩ አይገባም። ስራቸው ነውና!!
ይህ ታላቅ ጅማሮ ነው። ከአድዋ በተጨማሪ የትውልድ አዕምሮ የሚገነባባቸውና የሚበለጽግባቸው በርካታ እሴቶች ስላሉን ሥራው እንደሚቀጥል ይሰማናል። አድዋ አሉባልታን የሚጥየፍ፣ ሴራን የሚጠላ፣ ቀናነትን መርሁ ያደረገ፣መለያየትን አብዝቶ የሚኮንን፣ እኩልነትን እንጂ አድሎን የማያስተናግድ የ“ይቻላል” መንፈስ ነው።
የ“ጥሶ በመውጣት”አሻራችን በሆነው የአድዋ 128ኛ ዓመት ክብረ በዓል የተከናወነው ለክፋት፣ ለሴራና ለመለያየት ሃብት፣ ንብረት፣ጊዜና አቅማቸውን የሚያባክኑ በበዙበት ወቅት ላይ ነው። ይህ የጥፋት ርብርብ ሳይግድ በዚህ ደረጃ አድዋን መዘከር አገርቸውን ለሚወዱ ሁሉ ሙሉ ክብራቸው ነው።
አጤ ሚኒሊክ ብልህ መሪ ነበሩ። እከሌ ከከሌ ሳይባል የዘመኑ ጀግኖች ከባንዶቹ በስተቀር ድንቅ አገር ወዳድ ነበሩ። ዛሬም አደዋን ስናከብር አገሪቱን እየመሩ ያሉ ሁሉ፣ ብልህ አመራርን፣ ታማኝነትን፣ ውይይትንና ንግግርን በማስቀደም በአገራችን ውስጥ እዛም እዚህም የሚነሱ ችግሮችን በመድፈን ሌላ ታሪክ አስመዝግቡ። እዛም እዚህም “ችግር አለ” ብላችሁ ጦር ያነሳችሁም ከራሳችሁ ጋር መክራችሁ ልባችሁን ለንግግርና ለሰላም አንሱ!! ህዝብ ስቃዩ ያብቃ!!

Exit mobile version