Site icon ETHIO12.COM

“የጣሊያንን ገዢነት ከተቀበለ እንኳን ሰው ምድሯ የተረገመች ትሁን”

አቡነ ጴጥሮስ የተወለዱት በ1875 ዓ.ም በዚህ ሳምንት ነበር። የልጃቸውን የእውቀት ጮራ ለማየት ጉጉት ያደረባቸው ወላጆቻቸው የልጃቸው ዕድሜ ገና ለትምህርት ሳይደርስ ወደ ደብረ ሊባኖስ ገዳም በመውሰድ ለጋ አዕምሯቸውን በእውቀት ያንፁላቸው ዘንድ ባህታዊ ተድላ ለሚባሉ መምህር በአደራ ሰጧቸው። እርሳቸውም በዚያው ገዳም በጥንታዊው የቤተ ክርስቲያኗ ሥርዓተ ትምህርት መሠረት ከንባብ እስከ ቅኔ ያሉትን ትምህርቶች በሚያስደንቅ ሁኔታ በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቀቁ። ከዚያም የቅኔ ትምህርታቸውን ለማበልጸግ ወደ ጎጃም በመሄድ በዋሸራ የቅኔ ትምህርት ቤት ተማሩ።

በውስጣቸው የሰነቁት የመማር ፍላጎት ኃይል እና ብርታት ኾኗቸው እንደቅኔው ሁሉ የዜማውንም ትምህርት በሚገባ ለመማር ከቅኔው አውድማ ጎጃም ወደዜማው ምድር ጎንደር ተሻገሩ። በዚያም የዜማን ትምህርት ተከታትለው ጨረሱ።

ገና በልጅነታቸው ከደብረ ሊባኖስ ወደ ጎጃም፤ ከጎጃም ወደ ጎንደር የወሰዳቸው የትምህርት መንገድ ለታላቅ ክብር አብቅቷቸዋል። ቦሩ ሜዳ ከተባለው ስፍራ ላይ ወንበር ዘርግተው የመጽሐፍት ትርጓሜ ትምህርቶችን ማለትም መጽሐፈ ብሉያትን፣ ሀዲሳትን፣ ሊቃውንትን እና መነኮሳትን በብቃት አስተማሩ።

በ1900 ዓ.ም ልክ እንደርሳቸው ሁሉ እውቀትን እና ጥበብን ፍለጋ የገቡትን ደቀ መዛሙርት ለማስተማር ወሎ ውስጥ አማራ ሳይንት በተባለው ቦታ ወደሚገኘው ምስካበ ቅዱሳን ገዳም በመሄድ ወንበር ዘረጉ። በዚያም ለዘጠኝ ዓመታት ያህል ቅኔን እና መጽሐፍትን አስተማሩ። ከዚያም በኋላ ወደ ደብረ ሊባኖስ በመሄድ ሥርዓተ ምንኩስናን ፈጸሙ።

በ1910 ዓ.ም ወላይታ ለሚገኘው ደብረ መንክራት ምሑር ኢየሱስ ገዳም በመምህርነት ተሾሙ። በዚያም ለስድስት ዓመታት ያክል ካገለገሉ በኋላ በ1916 ዓ.ም ወደ ዝዋይ ተሻግረው የመምህርነት ተግባራቸውን ለሦስት ዓመታት ያህል አከናውነዋል። በ1919 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ እንዲመጡ ተደርጎ የመንበረ ልዑል ቅዱስ ማርቆስ መምህር እና በቤተ መንግሥት የንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የንስሐ አባት ኾኑ፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያውያን የሃይማኖት አባቶች እንድትመራ ከግብጽ እስክንድርያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጋር ስምምነት ላይ ሲደረስ በትምህርታቸው እና በሥነ ምግባራቸው የተመሰከረላቸው አምስት ኢትዮጵያውያን የሃይማኖት አባቶች ተመርጠው ነበር። አቡነ ጴጥሮስ ከነዚህ አባቶች አንዱ ለመኾን በቁ። በ1921 ዓ.ም ከግብጽ እስክንድርያ መንበረ ማርቆስ ቤተ ክርስቲያን መዓረገ ጵጵስና ተቀብለው “አቡነ ጴጥሮስ ጳጳስ ዘምሥራቀ ኢትዮጵያ ተላዌ አሰሩ ለአቡነ ኢየሱስ ሞዓ” ተብለው በመንዝና ወሎ ሀገረ ስብከት ተሾሙ።

አቡነ ጴጥሮስ በመንዝና ወሎ ሀገረ ስብከት ከተሾሙ ከሰባት ዓመታት በኋላ በ1928 ዓ.ም ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ወረረች። አቡነ ጴጥሮስም ወራሪው የጣሊያን ጦር በኢትዮጵያውያን ላይ የሚያደርሰውን ግፍ ሲመለከቱ ልባቸው በከፍተኛ የሀዘን ጦር ተወጋ።

አቡነ ጴጥሮስ የኢትዮጵያ እና የኢትዮጵያውያን መከራ ለሀዘን እና ለቁጭት ዳርጓቸው ይህንን ግፍ አይተው ማለፍ አልፈለጉም፤ ይልቁንም ከአርበኞች ጋር በመሰለፍ አርበኞችን ያበረታቱ እና ይደግፉ ጀመር።

ቀዳማዊ አጼ ኃይለሥላሴ የፋሺስት ጣሊያን ወራሪ ኃይል የሚፈጽመውን ግፍ ለዓለም መንግሥታት ማኅበር ለማሳወቅ ባሕር አቋርጠው ከሄዱ በኋላ ኢትዮጵያውያን አርበኞች ኃይላቸውን አሰባስበው በአዲስ አበባ የሚገኘውን የፋሺስት ጣሊያን ጦር ሠራዊት ለመውጋት በወሰኑበት ወቅት አቡኑ የአርበኞቹን ኅብረት ለመባረክ እና ሞራላቸውን ለማጠንከር ወደ አዲስ አበባ ሄደው ነበር።

በወቅቱ በነበረው የመረጃ እጥረት እና የቅንጅት ጉድለት ምክንያት የታሰበው ጥቃት ባይሳካም “የመጣሁበትን ሳልፈጽም ወደኋላ አልመለስም፤ ብችል በአዲስ አበባም ጠላት በኢትዮጵያውያን ላይ እያደረሰ ስላለው ጉዳት ሕዝቡን በማትጋት በጠላት ላይ እንዲነሳ አደርገዋለሁ፤ ካልሆነም እዚሁ እሞታለሁ” በማለት ሕዝቡ ለፋሺስት እንዳይገዛ እና አሥተዳደሩንም እንዳይቀበል ያስተምሩ ጀመር።

ዳሩ ግን ጠላት በመላ ከተማው ያሰማራቸው በርካታ ባንዳዎች አወኳቸው። በዚህም ምክንያት ጳጳሱ እንዳሰቡት ሊንቀሳቀሱ ባለመቻላቸው በወቅቱ የኢጣሊያ እንደራሴ ለነበሩት ለራስ ኃይሉ እጃቸውን ሰጡ። ራስ ኃይሉም ለፋሺስቱ አሥተዳደር የበላይ ለነበረው ለሮዶልፎ ግራዚያኒ አሳልፈው ሰጧቸውና የፋሺስት ጦር ቤተ መንግሥት ውስጥ አስገብቶ አሠራቸው።

ከዚያም ጳጳሱ የኢጣሊያን ገናናነት አምነው እንዲኹም የንጉሥ ኢማኑኤልን እና የቤኒቶ ሙሶሎኒን ገዢነት ተቀብለው በሃይማኖታዊ ተልዕኳቸው እንዲሰብኩ ተጠየቁ። ጥቂት ኢትዮጵያውን ሀገራቸውን ከድተው በአድርባይነትና በጥቅም ለግፈኛው ጠላት ድጋፍ እንደሰጡ ሁሉ ጳጳሱም ጣሊያኖች የነገሯቸውን ተግባራዊ ቢያደርጉ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መሪነትን እና ለስብከት ማስፋፊያ የሚኾን በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እና የተንጣለለ መኖሪያ እንደሚሰጣቸው የሚያረጋግጥ መደለያ ተንቆረቆረላቸው። ለጥቅም ያደሩ የእምነት አባቶችም ጣሊያውያን የሰጧቸውን እድል እንዲጠቀሙ ጳጳሱን ይማጸኑ ጀመር።

አቡኑም “ለመሆኑ የኢጣሊያንን ገናናነት እንዳምን፣ የኢማኑኤልን እና የሙሶሎኒን ገዢነት እንድቀበል ነው የፈለጋችሁት?” ብለው መስቀላቸውን ጠበቅ ላላ እያደረጉ ጠየቁ። “በትክክል!” አሉ ጣሊያኖች።

ይህን ጊዜ ጳጳሱ ገሰጿቸው። “በቃችሁ! በቃችሁ! ይህቺ ክብሯን የደፈራችኋት ሀገር ለመኾኑ ‹መኳንንት ከግብጽ ይወጣሉ፤ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ፈጣሪ ትዘረጋለች› የተባለላት ቅድስት ሀገር መኾኗን ታውቃላችሁ? ይህቺ የቆማችሁባት ምድር ለእብሪተኞች ረመጥ፣ እንደ እሳት የምታቃጥል መኾኗን ብታውቁ ኖሮ ምን ያህል ጥርሳችሁ በኃዘን እየተፋጨ በተንገጫገጨ ነበር። ግን ግብዝ ኾናችኋል፣ በኃይላችሁ ተማምናችኋል። እኔ የምፈራው የሰው ሰይፍ አይደለም። የእናንተ እብሪት፣ የእናንተ ጉልበት ትንሽ ጉም ነው፤ ነፋስ የሚበትነው። እና የፋሺስት ኢጣሊያን የበላይነት ከምቀበል ሞቴን እመርጣለሁ። ወደ እግዚአብሔር እጆቿን የዘረጋችውን ቅድስት ሀገሬን እብሪተኛ ሲደቀድቃት እንዲኖር አልፈቅድም፤ እምነቴም በፍፁም አይፈቅድልኝም!” አሉ ጳጳሱ አምርረው። ቀጥለውም “የኢጣሊያን ገዢነት የተቀበላችሁ ሁሉ አወግዛችኋለሁ! የኢጣሊያን ገዢነት ከተቀበለ እንኳን ሰው ምድሯ የተረገመች ትሁን!” አሉ ጣታቸውን ወደላይ ቀስረው ሰማይ ሰማይ እየተመለከቱ።

እንዲፈጽሙ የተጠየቁትን ፍርጥም ብለው “እምቢ!” ያሉት አቡነ ጴጥሮስ ወደ ችሎት ቀረቡ። ለፍርድም የተሰየሙት ዳኞች ሦስት ነበሩ። አቡነ ጴጥሮስ የቀረበባቸው ወንጀል “ሕዝብ ቀስቅሰዋል፤ ራሳቸውም አምጸዋል፤ ሌሎችም እንዲያምጹ አድርገዋል” የሚል ነበር፡፡

ፋሺስቱ ዳኛም “ካህናቱም ኾኑ የቤተ ክህነት ባለሥልጣኖች እንዲኹም ሊቀ ጳጳሱ አቡነ ቄርሎስም የጣሊያን መንግሥት ገዢነት አምነው ‹አሜን› ብለው ሲቀበሉ እርስዎ ለምን አመጹ? ለምን ብቻዎን አፈንጋጭ ሆኑ?” ሲል ጠየቃቸው። አቡነ ጴጥሮስም እንዲህ ብለው መልስ ሰጡ። “አቡነ ቄርሎስ ግብጻዊ ናቸው፤ ስለ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን የሚገዳቸው ነገር የለም፤ እኔ ግን ኢትዮጵያዊ ነኝ … እኔን ለመግደል እንደወሰናችሁ አውቃለሁ። ስለዚህ በእኔ ላይ የፈለጋችሁትን አድርጉ፤ ተከታዮቼን ግን አትንኩ! …” አሉ። ዳኞቹም ጳጳሱ በጥይት ተደብድበው እንዲገደሉ ፈረዱ።

ከፍርዱ በኋላም ተመልሰው ወደ እስር ቤት ተወሰዱ እና ተዘጋባቸው። ሌሊትም ዶፍ ዝናብ ሲዘንብ፣ ጎርፉ ሲጋልብ እና ነጎድጓዱ ብልጭ ድርግም ሲል በግፍ የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው አቡነ ጴጥሮስ “ሰዓሊለነ ቅድስት ኢትዮጵያን ጠብቂያት እመብርሃን … ሕዝበ ኢትዮጵያን ጠብቂ …” እያሉ ጸሎታቸውን ያደርሳሉ።

ሐምሌ 22 ቀን 1928 ዓ.ም ከጠዋቱ አራት ሰዓት ጥሩምባ ተነፍቶ ሕዝቡ ግድያው ከሚፈጸምበት ቦታ አራዳ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በታች ከአትክልት ተራ ፊት ካለው ቦታ ላይ ተሰበሰበ። አቡነ ጴጥሮስ በፋሺስት ወታደሮች ታጅበው መጡ። ሞት አይፈሬው የነፃነት አርበኛም “ዓይንዎን በጥቁር ጨርቅ እንዲሸፈኑ ይፈልጋሉ?” ተብለው ተጠየቁ። “እናንተ እንደፈለጋችሁ አድርጉት፤ እንደ እኔ ምርጫ ግን የወራሪን፣ የእብሪተኛን ሞት ፊት ለፊት ገጥሜ ድል አድርጌ መሞት ስለምፈልግ ባትሸፍኑኝ ደስ ይለኛል፤ ሞቴ አያሳፍረኝም። የምሞተው ለሀገር እና ለትልቅ ሕዝብ ነው” በማለት የዓይናቸውን መሸፈን ተከላከሉ።

ጳጳሱም ፊታቸውን ወደ ምዕራብ እንዳዞሩ ስምንት ወታደሮች የመሣሪያቸውን አፈ ሙዝ አነጣጠሩባቸው። ሕዝቡ እና ሰማዩ እኩል አጉረመረሙ። ኮማንደሩ “ተኩስ” የሚል ትዕዛዝ የሚሰጥ የግፍ ቃታዎች ተሳቡ። “ሥልጡን ነን፤ ሰብዓውያን ነን” የሚሉት ነጮች አረመኔያዊ ድርጊት ፈጸሙ። አቡነ ጴጥሮስ በስምንት ጥይቶች ተደበደቡ፤ ከአንገታቸው በታች ሰውነታቸው ቢበሳሳም ነፍሳቸው አልወጣችም ነበር። ኮማንደሩ ሽጉጡን ከክሳዱ በመምዘዝ በሦስት ጥይቶች ጭንቅላቸውን ሲመታቸው ሕይወታቸው አለፈች። በሚወዱት የኢትዮጵያ አፈር ላይ ወደቁ። የኢትዮጵያ መወረር የእሳት አሎሎ ኾኖ ሲቃጠል የነበረው አንጀታቸው ተሰብስቦ ተኛ፡፡

አቡነ ጴጥሮስ ስለ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን ክብር እና ነፃነት ራሳቸውን አሳልፈው ሰጡ።

———————–//—————-

ሰንደቅ ዓላማውን ወራሪዋ ሀገር ወስጥ ያውለበለበ ጀግና!

ኮሎኔል አብዲሳ አጋ የተወለደው 1912 ዓ.ም ነበር። አብዲሳ በ14 ዓመቱ የኢትዮጵያን ጦር በመቀላቀል ሀገሩን ማገልገል ጀመረ። አብዲሳ ጦሩን ከተቀላቀለ ከሁለት ዓመት በኋላ የዓድዋን ሽንፈት ላለመበቀል የዛተው ፋሺስት ሙሶሎኒ በድጋሚ ኢትዮጵያን ሲወር ሀገሩን ለመከላከል በ16 ዓመቱ ወራሪውን ጦር መዋጋት ጀመረ። ይህም በዚህ ባሳለፍነው ሳምንት ነበር፡፡

ውጊያ ላይ ባጋጠመው የመቁሰል አደጋ ህክምና ላይ ከቆየ በኋላ አዲስ አበባ ውስጥ ፒያሳ አካባቢ በሚገኝ ቤት በቁም እስር ላይ ነበር። በኋላ ጣልያን ኢትዮጵያን እንዲያስተዳድር በሾመችው ግራዚያኒ ላይ የመግደል ሙከራ ከተደረገ በኋላ አብዲሳ አጋ እና ሌሎች 37 የሚኾኑ የቁም እስረኞች ተጠርጣሪ ተብለው በከባድ ስቃይ እስር ቤት ከቆዩ በኋላ በወቅቱ የጣልያን ግዛት በነበረችው በሶማሊያ በኩል ወደ ጣልያን ተወስዶ በሲሲሊ ደሴት በሚገኝ እስር ቤት ታሠረ፡፡

አብዲሳ አጋ ከእስር ቤት በጥበብ ካመለጠ ከጥቂት ቀናት በኋላ አብረውት ያመለጡትን እስረኞች አስከትሎ ታስረው የነበሩበትን እስር ቤት ላይ በወሰዱት እርምጃ እስረኞችን አስለቅቀዋል፡፡ አብዲሳ አጋ ከዛ ጊዜ ጀምሮ ከጣሊያን ጦር ጋር ይዋጉ ጀመር፤ ለጣልያን ጦርም ራስ ምታት ኾነዉባቸዉ ነበር፤ ጦርነቱ እየገፋ ሲሄድ የተባበሩት ኃይላት አሜሪካ፣ እንግሊዝ ራሽያ እና ፈረንሳይ ለአብዲሳ አጋ እውቅና ሰጥተውታል፡፡

ጣሊያን ሲዳከም መጀመሪያ ሮም የገባው ወጣቱ አብዲሳ አጋ ነበር። ሮም ሲገባም የኢትዮጵያን ባንዲራ እያውለበለበ ነበር፤ ከዛም እንግሊዝ የወታደራዊ ፓሊስ አዛዥ አድርጎ ሾሞ ወደ ጀርመን ልኮት ከናዚ ጋር ባደረገው ጦርነት ታላቅ ጀብዱ ፈጽሟል። ጦርነቱ ካከተመ በኋላም እነዚሁ ሀገራት ከነሱ ጋር እንዲቆይ ሥልጣንም እንደሚሰጡት ጠይቀውት ነበር። ወጣቱ አብዲሳ አጋ ግን ሀገሬ ድሃ ነች ነገር ግን ሀገሬ እና መንግሥቴ ናፍቀውኛልና ሀገሬ እገባለሁ ብሎ ወደ ሀገሩ መጣ።

ቀዳማዊ ኃይለሥላሴም ይህን ጀግና የኮሎኔልነት ማዕረግ ሰጥተው የክብር ዘበኛ አድርገዉ ሾመውትም ነበር።

ኮሎኔል አብዲሳ አጋ ኢትዮጵያን ለዓለም ያስተዋወቀ፣ ባልተወለደበት እና ባላደገበት ምድር ጠላትን ያስጨነቀ፣ ያሸበረ፣ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ወራሪዋ ሀገር ሮም ወስጥ ያውለበለበ ጀግና ነበር።

ምንጭ፦ ፍቅሬ ቶሎሳ (ዶ.ር) “አብዲሳ አጋ” (አሚኮ)

Exit mobile version