በደብረ ኤልያስ ‘የዓለም ብርሃን’ የተሰኘ አዲስ እምነት መጀመሩ፣ በውጊያውም ተሳታፊ መሆናቸው ተሰማ

በጥንታዊው የደብረ ኤሊያስ ገዳም “የኣለም ብርሃን” የሚል ዕምነት የሚያራምዱ አካላት በውጊያ መሳተፋቸውን የደብረ ኤሊያስ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መልካሙ አስታውቀዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በውጊያው በንጹሃን ላይ የሞትና የአካል ጉዳት ደርሷል በሚል ሪፖርት ማቅረቡ ይታወሳል፡፡ ኮሚሽኑ በቁጥር ሳይስደግፍ ላሰራጨው መግለጫ የሚዛናዊነት ወቀሳ ቢሰነዘርበትም ተጨማሪ እስካሁን ያለው ነገር የለም፡፡

በውጊያው የተነሳ የአካባቢው አርሶ አደሮች ከግብርና ሥራቸው መስተጓጎላቸው እና የገዳማቱ መናኝ መነኮሳትም ላይ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየተፈጸመባቸው መሆኑን ኢሰመጉ አሰባሰብኳቸው ባለው መረጃ ቢገልጽም መረጃው አግባብነት የጎደለውና ስፍራው ድረስ በመሄድ በወጉ ያልተቀናበረ፣ የችግሩ አካላትና ዕምነትን ከለላ ያደረጉ ታጣቂዎችን ካደራጁ አካላት የተሰባሰበ መረጃ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

“ህጋዊ ሰነድ የሌላቸው ስደተኞች ለምን ይጠየቃሉ፣ ለምን ይያዛሉ” በሚል ኮሚሽኑ መንግስትን መክሰሱን ተከትሎ “የትኛው አገር ስደተርኞችን ያለ ህጋዊ ሰነድና ምዝገባ ነጻ ይለቃል” በሚል ጥያቄ አንስተው ተቋሙ እያደር ገለልተኛነት እየጎደለውና ያለ በቂ ጥናት የሚያቀርባቸው መረጃዎች ግምት ውስጥ እየጣሉት እንደሆነ ሰሞኑንን አስተያየት መሰጠቱ ይታወሳል፡፡ ቀደም ሲልም በማይካድራና አካባቢው የተፈጸመውን ጭፍጨፋ አንሸዋሮ በማቅረቡ ነቀፌታ ሲሰነዘርበት እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

የወረዳው አስተዳዳሪ ግን በግጭቱ ውስጥ ዋነኛ ተሳታፊ የነበሩት በገዳሙ ውስጥ ‘የዓለም ብርሃን’ የተባለ አዲስ አይነት የእምነት እንቅስቃሴ አራማጆች መሆናቸውን ለቢቢሲ ገልጸዋል።

“ሕዝቡ ለረዥም ጊዜ ሲገለገልበት የቆየው ገዳም፣ ከሦስት አራት ዓመታት ወዲህ ባሕሪውን ቀይሮ የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ያልሆነ ‘የዓለም ብርሃን’ የሚባል ሃይማኖት ሲያይ ማኅበረሰቡ ትክክል አይደለም በማለት ቁጣውን ገልጿል።”

ጨምረውም የዚህ እንቅስቃሴ አባላት ሰዎች ገድለው ወደ ገዳሙ ውስጥ በመግባት ሳይጠየቁ እንደሚሸሸጉ የተናገሩት አስተዳዳሪው “ወታደር ያሰለጥናሉ። በተደጋጋሚ እንዲህ ያለውን ድርጊት እንዲያቆሙ ነግረናቸዋል፣ ነገር ግን ሊቀበሉ አልቻሉም እንዲሁም ለኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ አይታዘዙም” ብለዋል።

ይህ ችግር በመመካከር መፍትሔ እንዲያገኝ የአካባቢው አስተዳደር “ወደ አስራ ሁለት ጊዜ ያህል ቢሞክሩም እንዳልተሳካ” አመልክተዋል።

በውይይቶቹ ወቅት ድርጊታቸውን “አንዴ ይክዳሉ፣ አንዴ ያምናሉ” ሲሉ የገለጹት አቶ መልካሙ “እኛን አትነኩንም” የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸውም አክለዋል።

See also  በ169 ታዳጊዎች ላይ ሊፈፀም የነበረ ያለ እድሜ ጋብቻ እንዲቋረጥ ተደረገ

ይህ ከወራት በፊት የተጀመረው ንግግር መፍትሄ ባለማስገኘቱ የክልሉ የፀጥታ ኃይሎች ወደ አካባቢው በተሰማሩበት ወቅት “የተኩስ ልውውጥ ተደርጎ ከፀጥታ ኃይሉ እና ከእነሱም ሰዎች ሞተዋል። በመጨረሻም የፀጥታ ኃይሎች አፈግፍገው ወጡ” ሲሉ ገልጸዋል።

ከዚያም በኋላ በጥር እና በካቲት ወር አካባቢ ሁኔታው እየተባባሰ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር ያሉት ያሉት አቶ መልካሙ፣ ነገሩ እየከበደ ሲመጣ የመከላከያ ሠራዊት ወደ አካባቢው ተሰማራ ሲሉ አክለዋል።

“መከላከያንም ገጠሙት። ከመከላከያ ጋር የሚገጥም ኃይል እዚያ [ገዳም] ውስጥ አለ” ያሉት የወረዳው አስተዳዳሪ፣ በገዳሙ ውስጥ ያሉት “መነኩሴ ነን የሚሉ፣ መነኩሴ ያልሆኑ” ናቸው ብለዋል።

ቢቢሲ ከገለልተኛ ወገን ማጣራት ባይችልም በገዳሙ ውስጥ ለቀናት በተካሄደው ግጭት መነኮሳት እና ምዕመናን ላይ ጉዳት መድረሱ ቢነገርም፣ አቶ መልካሙ ግን መነኮሳት አለመሆናቸውን ይናገራሉ።

መነኩሴ አለመሆናቸው እንዴት እንደተረጋገጠ ከቢቢሲ ተጠይቀው “ድርጊታቸው ይህንን ያመለክታል” ያሉት አቶ መልካሙ “መነኩሴ ሰው ይገድላል? መነኩሴ ወታደር ያሰለጥናል?” በማለት ጥያቄውን በጥያቄ መልሰዋል።

የወረዳው አስተዳዳሪ ችግሩ ያለው ከገዳሙ አስተዳዳሪዎች እንደሆነ ጠቅሰው ችግሩን የፈጠሩት “የሰው ሕይወት አጥፍተው የገቡ ናቸው። የሃይማኖት አባት ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመቀደስ ሲገባ ገድለው፣ አስተዳዳሪ እና ምክትል አስተዳዳሪን አቁስለዋል” ሲሉም ከሰዋል።

ቢቢሲ ከአካባቢው ባሰባሰበው መረጃ እንደተረዳው የመንግሥት ኃይሎች ይህንን ዘመቻ የጀመሩት ከግንቦት 18/2015 ዓ.ም. ሲሆን፣ ከአራት ቀናት በላይ ለሚሆን ጊዜ ከባድ ግጭት ሲካሄድ ቆይቶ በመቶዎች በሚቆጠሩ ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል።

የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ መልካሙ ባለፉት ቀናት በተካሄደው ከባድ ግጭት በሰው ላይ ስለደረሰው ጉዳት ከቢቢሲ ተጠይቀው “ምን ያህል ሰው እንደሞተ ለማወቅ እንደማይቻል” ጠቅሰው ነገር ግን“ሰላማዊ ሰው እንዳልተጎዳ” ተናግረዋል።

በገዳሙ አቅራቢያ ባሉ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ለቀናት በቆየው ግጭት የከባድ መሣሪያን ጨምሮ ከባድ ተኩስ ሲካሄድ ሲሰሙ እንደነበር፣ ነገር ግን ምክንያቱ ምን እንደሆነ ሳያውቁ መቆየታቸውን ያለፈው ሐሙስ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ባለፈው ሳምንት የደብረ ኤልያስ ወረዳ ሰላም እና ፀጥታ ጽሕፈት ቤት እንዳለው፣ በደጎልማ ቀበሌ የሚገኘው የሥላሴ አንድነት ገዳም “በሃይማኖት ሽፋን ገዳሙን መሸሸጊያ አድርገው የሃይማኖት አባቶችን፣ የአገር ሽማግሌዎችን እና የመንግሥት አመራሮችን እየገደሉ በሕግ ላለመጠየቅ የሚጥሩ የታጠቁ ሰዎች የሚኖሩበት ገዳም ሆኗል” ብሎ ነበር።

See also  " ፈርሷል" የተባለው የአገር መከላከያ በሁሉም ግንባሮች እያጠቃ ይዞታውን እያሰፋ ነው

የፀጥታ እና የደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ባወጣው መግለጫ ላይ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ወረዳ በሚገኘው የሥላሴ ገዳም “መንግሥትን በትጥቅ ትግል ለመጣል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ጽንፈኛ ኃይሎች” ባላቸው ላይ እርምጃ ተወስዷል ብሏል።

የወረዳው አስተዳዳሪ እንዳሉት በግጭቱ ዋነኛ ሚና ነበረው ያሉት ‘የዓለም ብርሃን’ የተባለው የእምነት እንቅስቃሴ “በአገር ውስጥ እና በተለያዩ አገራት የሚገኙ ምሁራን እና ባለሃብቶች” ጭምር እንዳሉበት አመልክተዋል።

ግጭቱ ከመከሰቱ ቀደም ብሎ አካባቢው ተጠንቶ ያለው ችግር በሰላም እንዲፈታ በሽምግልና ለመፍታት ቡድን ተዋቅሮ እየተዘጋጀ ሳለ “ተኩስ ከገዳሙ ውስጥ ተከፍቷል” ያሉት አቶ ምልካሙ፣ በቀጣዩ ቀንም “ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር አስታርቀናችሁ” ቢባሉም ተኩሱ መቀጠሉን ገልጸዋል።

ባለፈው ቅዳሜ የፀጥታ እና የደኅንነት ግብረ ኃይል ባወጣው መግለጫ ላይ እርምጃ ተወስዶበታል ያለው የታጣቂ ቡድን መሪ እና አስተባባሪው አስክንድር ነጋ መሆኑን እና እርምጃ በተወሰደበት ወቅት “እስክንድር ነጋ እና ጥቂት ግብረ አበሮቹ ከአካባቢው መሰወራቸውን” ጠቅሷል።

የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ መልካሙ አዲስ አቶ እስክንድር በቦታው ነበሩ የሚለውን በተመለከተ “የሚያውቁት ነገር እንደሌለ” ምላሽ ሰጥተዋል።

መንግሥት ባወጣው መረጃ መሠረት 200 ታጣቂዎች ተደምስሰውበታል የተባለው ግጭት የተቀሰቀሰበት የደብረ ኤልያስ ሥላሴ ገዳም፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በምሥራቅ ጎጃም ዞን አገረ ስብከት ስር የሚገኝ ነው።

የአገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ መላዕከ ሰላም ቀሲስ ግዛቸው ስለወንድም፣ አገረ ስብከቱ “ሰሞኑን የተፈጠረውን ገና ወርዶ አላጠራውም” ሲሉ ተጨማሪ ማብራሪያ ለመስጠት እንደሚቸገሩ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በገዳሙ ውስጥ ስለተከሰተው ነገር ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጋር “በጋራ በሚደረግ ማጣራት” ከሚገኘው መረጃ ውጪ በአሁኑ ወቅት ዝርዝር ነገር እንደሌላቸው ተናግረዋል።

አክለውም ቦታው “ገዳም መሆኑን” ከማረጋገጥ በዘለለ አሁን ላይ “በውስጡ ማን ነበር?” የሚለውን ለመመለስ እንደማይቻላቸው አምልከተዋል።

መንግሥት የመከላከያ ሠራዊት እና የአማራ ክልል የፀጥታ ኃይሎች “መንግሥትን በኃይል ለመጣል የተንቀሳቀሱ ጽንፈኛ” ያላቸው እና የወረዳው አስተዳዳሪ “አዲስ አይነት የእምነት እንቅስቃሴ ቡድን አባላትም አሉበት” ካሉት ቡድን ጋር ለቀናት ግጭት ከተካሄደ በኋላ አሁን አካባቢው ሰላም መሆኑ ተገልጿል።

See also  መንግስት ለሰብዓዊነት ሲባል ግጭት ለማቆም መወሰኑን አስታወቀ

“አካባቢው አሁን ሰላም ነው። ምንም የለም። ሁሉም ወደ የዕለት ከዕለት ሥራውን ተመልሶ ተረጋግቶ እየሠራ ነው” ሲሉ የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ መልካሙ አዲስ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከሳምንት በፊት ተጀምሮ ለቀናት የመከላከያ እና የአማራ ክልል የፀጥታ ኃይሎች ወሰዱት በተባለው እርምጃ “በእስክንድር ነጋ እና በግብረ አበሮቹ ለውጊያ ሲውል የነበረ ምሽግ መሰበሩን እና 200 ታጣቂዎች መደምሰሳቸው” ተገልጿል።

ለቀናት የቆየ ግጭት የተካሄደበት እና መንግሥት እንዳስታወቀው በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተጎዱበት የምሥራቅ ጎጃም የደብረ ኤልያስ ብሔረ ብፁዓን መልክዓ ሥላሴ አንድነት ገዳም ባለቤት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስለክስተቱ የሰጠችው ዝርዝር መረጃ የለም።

ነገር ግን የቤተ ክርስቲያኗ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽሕፈት ቤት የገዳማት አስተዳደር መምሪያ ከአገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት ጋር በመገናኘት የተከሰተውን ችግር በተመለከተ የማጣራት ሥራ እያከናወነ እንደሆነ እና ተጣርቶ የተደረሰበት ውጤት የሚገለጽ መሆኑን አሳውቋል።

ቢቢሲ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ደብረ ኤልያስ ወረዳ የተከሰተውን ሁኔታ ለማጣራት ካለፈው ሰኞ ጀምሮ ከሚመለከታቸው የአካባቢው እና የአማራ ክልል ኃላፊዎች ዝርዝር መረጃ ለማግኘት ጥረት ቢያደርግም ሳይሳካለት ቆይቷል።

Leave a Reply