Site icon ETHIO12.COM

በአማራና ትግራይ ክልል ያሉ የወሰን ይገባኛል ጥያቄ በህዝብ ውሳኔ እንዲቋጭ ስምምነት ተደረሰ

ተፈናቃዮችን ወደ ነበሩበት የመመለስ ሂደት በቅርቡ ይጀመራል

ትህነግ በበላይነት የሚመራው ኢህአዴግ ከፈርሰ በሁዋላ የተነሳውን ጦርነት ተከትሎ የአማራ ክልል ” ነጻ ወጡ” ባላቸው አካባቢዎች ለዓመታት የቆየ ውዝግብ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቋጨት ህገመንግስቱ በሚያዘው መሰረት በህዝበ ውሳኔ እንዲቋጭ በይፋ ስምምነት ላይ መደረሱ ተረጋገጠ። ተፈናቃዮች ወደቀያቸው መመለስ ይጀምራሉ።

በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ወልቃይት ጠገዴን ጨምሮ ” ነጻ ወጡ” የተባሉት አካባቢዎች ለትግራይ እንዲመለሱ ካልተደረገ ጦርነት እንደሚቀሰቅሱ ሲገልጹ የነበሩ የትህነግ ከፊል አመራሮች እስካሁን አቋማቸውን በይሁንታም ይሁን በተቃውሞ አላሰሙም። የአፍሪካ ህብረትና ሌሎች ታዛቢዎች ባሉበት፣ የትህነግ አመራሮችና የጊዜያዊ አስተዳደሩ መሪዎች በተገኙበት የፕሪቶሪያው ስምምነት ትግበራ ሲገመገም ቅድሚያ የተፈናቃዮችን ህይወት ወደነበረበት መመለስ፣ ሲቀጥልም ህዝብ እንዲወስን ስምምነት መደረሱ ተረጋግጧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አቶ ጌታቸው ረዳን አስቀምጠው ከትግራይ ህዝብ ወኪሎች ጋር ውይይት ባደረጉበት ወቅት ” በስምምነቱ መሰረት ክረምት ሳይገባ ተፈናቃዮች ወደ ቦታቸው እንዲመለሱ ይደረጋል” ማለታቸው ይታወሳል። አያይዘውም “ህዝቡ ከተረጋጋና ወደ ቀልቡ ከተመለሰ በሁዋላ ዓለም እያየ በድምጹ የፍለገውን ይወስናል” ብለዋል።

በዚሁ ንግግራቸው ላይ ” ንገሩዋቸው፣ በሁዋላ አልነገረንም እንዳትሉ” በማለት ደጋግመው ያስጠነቀቁት ዳግም ውጊያ የሚፈልጉ የትሀንግ አካላት ስለመኖራቸው ነው። “እኛ ገምገምና” በማለት ጦርነቱ እንዴት ተነሳ? ማን ጀመረው? ለምን ተጀመረ? አንደኛ፣ ሁለተኛውና ሶስተኛው ጦርነት ለምን እንደተነሳ መረዳት እንደሚገባ ሲያሳስቡ ” መርምሩት፣ ገምግሙት፣ እወነቱን እወቁት፣ ትማሩበታላቸሁ” በማለት ነበር። ይህን ካሉ በሁዋላ ያለፈው ጦርነት ብዙ ትምህርት እንደሰጠ ጠቅሰው ” ሌላ ውጊያ ከተነሳ ይበልጥ ጉዳት ይደርሳል” ሲል መነጋገርን ማስቀደም እንደሚበጅ አመልክተዋል።

በዚሁ ስብሰባ ላይ ከትግራይ ተወካዮች በኩል አንድ እናት ስለ ጦርነቱ አስከፊነት ካስረዱ በሁዋላ ” ካሁን በሁዋላ ልጆቻችንን አንሰጥም” ሲሉ ጦርነቱ ወላዶችን መና እንዳደረጋቸው ተናግረዋል። ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ ጦርነቱን እንደማይደግፉ ተሰብሳቢዎቹ አቀራረባቸው ቢለያይም አቋማቸው ተመሳሳይ መሆኑንን አመልክተዋል።

በጦርነቱ ወቅት ምድር ላይ ያሉ የስድብ ዓይነቶችን፣ በምድር ላይ ባሉ የመገነኛ ዘዴዎች ሁሉ በመጠቀም ሲያዘንብባቸው፣ አንጠልጥሎ እስር ቤት እንደሚከታቸው፣ የሚያድናቸው እንደሌለ ወዘተ እየዘረዘረ ቀኑንን ሙሉ ሲሰድባቸው የነበረውን አቶ ጌታቸው ረዳን ከጎናቸው አስቀምጠው ” ከዚህ ስብሰባ በሁዋላ የተቋቋመው ኮሚቴ ዝርዝር ጉዳዮችን ይመክራል” ሲሉ አብይ አሕመድ ባስታውቁት መሰረት ስራውን ያከናውነው ኮሚቴ ተፈናቃዮችን ወደነበሩበት የሚመለሱበትን አግባብ ማከናወኑን አስታውቋል።

በአማራና ትግራይ ክልሎች መካከል የሚገኙና የወሰን ይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸውን አካባቢዎች በህገ መንግስቱ እና በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ መሰረት በዘላቂነት እልባት ለመስጠት በብሔራዊ ደረጃ የተቋቋመው ኮሚቴ አፈጻጸም መገምገሙን ገልጾ ነው የተግባር እንቅስቃሴውን እንደጀመረ ያስታወቀው።

ኮሚቴውን ጠቅሰው የመንግስት ሚዲያዎች እንዳሉት፣ በአማራና ትግራይ ክልሎች መካከል የሚገኙና የወሰን ይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸውን አካባቢዎች በህገ መንግስቱ እና በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ መሰረት በዘላቂነት እልባት ለመስጠት በብሔራዊ ደረጃ የተቋቋመው ኮሚቴ አፈጻጸም መገምገሙን ከመግለሳቸው በቀር ዝርዝር ነጥቦችን አላካተቱም።

በአማራና ትግራይ ክልሎች መካከል የሚገኙና የወሰን ይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባቸውን አካባቢዎች በህገ መንግስቱ እና በህገ መንግስታዊ ስርዓቱ መሰረት በዘላቂነት እልባት ለመስጠት በብሔራዊ ደረጃ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሲሠራ እንደነበር የሚታወስ ነው። ኮሚቴው የህዝብ ውሳኔን አክብሮ እየሰራ ቢቆይም በተለያዩ ሚዲያዎች “ወልቃይትን አሳልፎ ሊሰጥ ነው” በሚል ያለ አንዳች ማስረጃ ሲወገዝ እንደነበር ይታወሳል።

ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አቶ ሬድዋን ሁሴንና የሁለቱ ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድሮች እንዲሁም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ተሳታፊዎች በተገኙበት የብሔራዊ ኮሚቴው የተፈፀሙና ሊፈፀሙ ሲገባቸው የዘገዩ ጉዳዮች በማንሳት ገምግሟል።

በግምገማው መሰረት በአፈፃፀም ሂደቱ የነበሩ ጠንካራና ደካማ ጎኖች የተለዩ ሲሆን የማንነትና የይገባኛል ጥያቄ ያለባቸውን አካባቢዎች ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በአፋጣኝና በዘላቂነት ሊፈታ እንደሚገባም ስምምነት ላይ ተደርሷል። በዚሁ መርሰረት ተፈናቃዮች ክረምት ሳይገባ ወደ ቀያቸው ተመልሰው፣ በሂደት የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ይከናወናል። ይህም የሚሆነው በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት በህገመንግስቱ አጋባብ ነው።

በዚሁ አግባብ መሰረት በአጭር ጊዜ ወደቀያቸው የመመለስ ጉዳይ ቅድሚያ ተሰጥቶት በሚፈፀምበት አግባብ ላይ መተማመን ላይ ተደርሷል። በተጨማሪም በብሔራዊ ደረጃ ይህን እንዲያስፈፅም የተቋቋመው ኮሚቴ በቋሚ የጊዜ ሰሌዳ እየተገናኘ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለጉዳዩ እልባት እንዲሰጥ በዛሬው ዕለት በተደረገው ስብሰባ መወሰኑን ከብሔራዊ ኮሚቴው የደረሳቸውን መረጃ ጠቅሰው ከዘገቡ የመንግስት ሚዲያዎች መረዳት ተችሏል።

Exit mobile version