Site icon ETHIO12.COM

ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በከፍተኛ የውስጥ ችግር ውስጥ ናት፤ በጾሙ ማቅ ለብሰው በንስሃ ችግራቸውን ይፍቱ

የኢትዮጵያ ታሪክ ቁንጮ እንደሆነች የሚመሰከርላትና እጅግ ውብ ስብዕና ያላቸው አባቶች የሚጠቀሱላት ዕድሜ ጠገብቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በከፍተኛ የውስጥ ችግር መተብተቧ እየተጠቆመ ነው። በተጀመረው የአብይ ጾም ማቅ ለብሰውና አመድ ነስንሰው ችግራቸውን ሊፈቱ እንደሚገባ ምክር እየተሰጠ ነው።

መንግስት በዋናነት ብቻ ባለው አስራ አንድ ጊዜ ስብሰባ የተቀመጠው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቅዱስ ሲኖዶስ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንዳለ የተጠቆመው አሁን ከቀናት በፊት ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ጋር ያደረጉት ውይይት ይፋ ከሆነ በሁዋላ ነው። ቀደም ሲል ራሳቸውን የኦሮሚያ ሲኖዶስ ብለው ለመገንጠል በሞከሩና “ቀኖና” ተጥሷል በሚል ዋናው ኦርቶዶክስ ግዝት ማስተላለፉን ተከትሎ ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር ያደረጉትን ይፋ ውይይት ያደመጡ እንደሚሉት ቤተ ክርስቲያኗ ከውጫዊ ችግር ይልቅ ውስጣዊ ችግሯ እንደሚታይ አመልክተዋል።

ጥሩ ገቢ ባለው ሃገረ ስብከት ለመመደብ በሚሊዮን የሚቆጠር ጉቦ እንደሚከፈል በይፋ በመናገር ቀደም ሲል ሲካሰሱ የተሰሙት አባቶች፣ በወቅቱ ያነሷቸው የልዩነት መነሻ ስልጣንና ገንዘብ ብቻ እንደሆነ የወቅቱ ስብሰባ ክርክር ፍንትው አድርጎ እንዳሳየ በጊዜው መረጃውን አስደግፈን ሪፖርት እንደወረደ መጻፋችን ይታወሳል።

ሰሞኑን በተካሄደው ውይይት ላይ የታየው ልዩነት ግን ነገሩን በጥሞና ለሚከታተሉ የሚያሳስብ ልዩነት ሆኖ ተወስዷል። በአንድ ሲኖዶስ ውስጥ የተለያየ አቋም የሚያራምዱ ስብስብ እንደሆነ ይፋ የሆነው አባቶቹ እርስ በርስ ሲወነጃጀሉ በመድመጡ ነው።

“የሲኖዶሱ ጥያቄ ነው” ተብሎ የባህርዳርና አካባቢው አገረ ስብከት፣ እንዲሁም የቅዱስ ሲኖዶሱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቡነ አብርሃም ያቀረቡት ጥያቄ በሌሎች የሲኖዶሱ አባላት በግልጽና በቀጥታ ተቃውሞ ሲነሳበት ታይቷል። አስገራሚ የሆነው አንዳቸው አንዳቸውን ሲተቹ በጭብጨባ የመደገፍ ሁኔታ መታየቱ ነው።

“ይህቺ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተከታይ ያላት ቤተክርስቲያን በዚህ የልዩነት ማዕበል ውስጥ ተዘፍቃ እስከመቼ ትቀጥላለች” ሲሉ በመጠየቅ ስጋት ያራዳቸው የዕምነቱ አባል ” ፈርቻለሁ። በውይይቱ ወቅት ያየሁትና የሰማሁት አስደንግጦኛል። በዚህ ደረጃ ተቧድነው እንዴት ነው መስቀል የሚሸከሙት? ለግል አጀንዳቸው ቤተክርስቲያኒቱን ወደ ተለያየ አቅጣጫ ከሚጎትቱት በመራቅ አባቶቹ በራቸውን ዘግተው በንስሃ ችግራቸውን እንዲፈቱ ያገባናል የሚሉ ሁሉ ነገ ዛሬ ሳይባል ፈጥነው እንዲንቀሳቀሱ መደረግ አለበት” ሲሉ የጽሁፍ አሳብ ልከዋል።

የዝግጅት ከፍሉ ምንም ዓይነት አስተያየት መስጠት ባይፈልግም የኦርቶዶክስ አመራሮ በከፍተኛ ልዩነት ውስጥ እንዳሉ፣ በዘርና በፖለቲካ እሳቤዎች የተጠለፉ መሆናቸውን ይረዳል።

ይህቺ ታላቅ የታሪክ ማህደር የሆነች ቤተክርስቲያን በአስቸኳይ ልዩነቷን ልትፈታ እንደሚገባ የጠቆሙትን ስጋት የገባቸው ወገኖችን ሃሳብ እንጋራለን። አሁን በታየው የልዩነት መጠን ሲኖዶሱ እንዴት አብሮ ሊዘልቅ ይችላል? የሚለው ስጋት ስለእውነት ከሆነ እንቅልፍ የሚነሳ ነው። በክርስቶስ ፍቅር የታነጸች ቤተክርስቲያንን የሚመሩ አባቶች ችግራቸውን በይቅርታ፣ በንስሃ፣ በኑዛዜና በጸጸት ፈተው አንድነታቸውን ሊጠብቁ ይገባል።

አጋጣሚው የአብይ ጾም በመሆኑ፣ ይህን አጋጣሚ በመውሰድ በራቸውን ዘግተው ልዩነታቸውን ካላስወገዱ፣ የልዩነት ደረጃው ለሚያስከትለው ጣጣና ምስቅልቅል በሰማይም ሆነ በምድር ተጠያቂ ያደርጋልና ይታሰብበት። መንግስትም ልክ በሚለው ደረጃ የሚጠበቅበትን ይወጣ።

ሚዲያውም ለእለት ፍጆታና ለፖለቲካዊ ግብዓት በሚል ልዩነቱን ከማራገብ ይልቅ፣ ልዩነቱ እንዲፈታ ልንሰራ ይገባል። ይህቺ ታላቅ ቤተክርስቲያን በውስጧ የታቀፈችው እሳት ነዶ የሚጸጽተን ጊዜ እንዳይመጣ ጥንቃቄ እንውሰድ። መፈረካከስ እንዳይፈጠር ቢያንስ ድንጋይ ከማቀበል እንቆጠብ። በራሳችን የጥንቃቄ ችግር ጣጣ እንዲመጣ ካደረግን በሁዋላ ሌላው ላይ ጣት የመቀሰር ሞራልም አይኖረንም።

ከራሳቸው ከአባቶቹ የሚወጣው ንግግር እጅግ ተስፋ የሚያስቆርጥና እረፍት የሚነሳ ነው። ይህ ሊሰመርበት ይገባል። የዚህ ችግርና አደጋ ቆስቋሽ ከመሆን ይልቅ ቤተክርስቲያን አንድነቷ ጸንቶ እንድትቀጥል መድከምና የበኩልን መወጣት ቅን ልቦና ካላቸው ሁሉ የሚጠበቅ ነው። ብዙ መጻፍ ይቻላል። ችግሩን ለማሳየት በርካታ መረጃ ማስፈር ይቻላል። ግን መፍትሄ አይሆንም። ሁሉም በሚችለው ሁሉ በጎውን ያድርግ።

Exit mobile version