ቤተክርስቲያን – ካለፈው ጦርነት ተማሩ ስትል የሰላም ጥሪ አስተላለፈች

• የግጭት ተሳታፊዎች ካለፈው የጦርነት ውጤት ተማሩ።

• የተፈጠረውን ችግር በጥበብና በማስተዋል ፤ በሰለጠነ አካሄድና በሰላማዊ መንገድ ተወያይታችሁ ፍቱ።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዛሬ ሐምሌ 27 ቀን 2015 ዓ.ም ስብሰባ በማድረግ ወቅታዊ ሀገራዊ ሰላምን በተመለከተ አጀንዳ በመቅረጽ በጉዳዩ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ፤ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን በተለያዩ ቦታዎች እየተከሰተ ባለው የሰላም መደፍረስና የእርስ በርስ ግጭቶች ምክንያት የበርካታ ወገኖቻችን ውድ ሕይወት እያለፈ እና በርካታ የሀገርና የሕዝብ ሀብትና ንብረት እየወደመ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያናችን የተሰማትን ጥልቅ ሐዘን ትገልጻለች ” ብሏል።

” ሰላም ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ፍጡራን መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡ ” ያለው ቅዱስ ሲኖዶስ ” ሰላም ከሌለ ቀድሶ ማቁረብ፣ ነግዶ ማትረፍ፣ አርሶ ማምረት፣ ተምሮ ማስተማር ወልዶ ማሳደግ፣ ወጥቶ መግባት፣ አገር መምራትና ማስተዳደር አይቻልም ። በጥቅሉ ሰላም ሲጠፋ አብረው የሚጠፉ መልካም እሴቶቻችን ብዙ ናቸው፡፡ ” ሲል አስገንዝቧል።

ቅዱስ ሲኖዶስ ፤ በቅርብ ጊዜ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል የነበረው ጦርነት የበርካታ ወገኖቻችንን ሕይወት የቀጠፈ ከመሆኑም በላይ ከሞት የተረፉት ወገኖቻችንም ለስደትና ለረሀብ የዳረገ ፣ ለአካልና ለእእምሮ ስብራት ያጋለጠ ከመሆኑም በተጨማሪ በርካታ አድባራትና ገዳማትን እንዲሁም አብያተ ክርስቲያናትን ያፈረሰ እና መተኪያ የሌላቸውን ውድ ቅርሶቻችንን ያወደመ እጅግ በጣም አስከፊ ተግባር መሆኑን አስታውሷል።

በመሆኑም ፡-

በሀገራችን በኢትዮጵያ የተከሰተው የእርስ በርስ ጦርነትና ግጭት ተወግዶ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን ከሁሉም በላይ እግዚአብሔርን በጾምና በጸሎት ልንማጸን ይገባል ብሏል።

በሀገራችን በኢትዮጵያ አሁን ያለው የሰላም እጦትና የእርስ በርስ ግጭት ወደፊት ሊያስከትል የሚችለው ችግር ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ለአገራዊ ሰላም የበኩላቸውን ጥረት እንዱያደርጉ መልእክቱን አስተላልፏል።

ቅዱስ ሲኖዶስ ፤ በየትኛውም የሀገራችን ክፍል እየተደረጉ ባሉ ግጭቶች ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች ካለፈው የጦርነት ውጤት በመማር የተፈጠረውን ችግር በጥበብና በማስተዋል እንዲሁም በሰለጠነ አካሄድና በሰላማዊ መንገድ ተወያይተው እንዲፈቱ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የሰላም ጥሪዋን ከአደራ ጋር ታስተላልፋለች ብሏል።

See also  Amid war and instability, why the Ethiopian election matters

@tikvahethiopia

Leave a Reply