Site icon ETHIO12.COM

“ህወሃት በሚያኮርፍባቸው የሶማሊያ ‹አሸባሪ› ድርጅቶች ይጠረጠራል”

ሰሞኑን በከፍተኛ ደረጃ የዓለም መገናኛዎች ርዕስ የኢትዮጵያ ሰራዊት ከሶማሊያ ለቆ የመውጣቱ ጉዳይ ነው። የሶማሊያ ባለሥልጣናት ስለጉዳዩ የተነገራቸው አንዳችም ነገር እንደሌለ መግለጻቸው፣ አልሸባብም የሠራዊቱን እግር እግር እየተከተለ የተነጠቃቸውን ወረዳዎች መቆጣጠሩና ኢህአዴግ ጉዳዩን ያስተባበለበት አግባብ ጎልጉል የመረጃ አቀባዮቹን እንዲያነጋግር መነሻ ሆኗል። እንደ መረጃ ሰዎቹ ከሆነ በስም ተለይቶ ባይገለጽም ህወሃት በሶማሊያ ከሚንቀሳቀሰው አሸባሪ ድርጅት ጋር ግንኙነት አለው ተብሎ በጥርጣሬ መዝገብ ውስጥ ከገባ ሰነባብቷል።

ሟቹ የኢህአዴግ ሊቀመንበር መለስ ዜናዊ ሠራዊቱ ወደ ሶማሊያ ሲንቀሳቀስ ፓርላማው ሳይወስን በመሆኑ ይህንን ለማብራራት በተጠራ ስብሰባ ላይ በዋናነት ያሰመረበት ጉዳይ የደህንነት ስጋትን ነበር። “የደህንነታችን ስጋት የሆኑትን አሸባሪዎች ከምንጫቸው ማድረቅ” በሚል አብይ ምክንያት ጦሩ ሶማሊያ እንዲገባ መታዘዙን መለስ ሲያስረዳ “የአሸባሪ ድርጅቶቹ ስጋት ሊሆኑብን በማይችሉበት ደረጃ ሲደርሱ ጦሩ ሶማሊያን ለቆ ይወጣል” ነበር ያለው። በወቅቱ “ይህንን ጉዳይ አንቀበለም” ያሉ የተቀናቃኝ ፓርቲዎች ተወካዮች ተቃውሟቸው ለታሪክ እንዲመዘገብላቸው አስደርገው ነበር።

የዘመቻው ዥጉርጉርነት

ኢህአዴግ ጦሩን ወደ ሶማሊያ ሲያስገባ በወቅቱ የተነሳው የወደፊት የደህንነት ስጋትን ለማስወገድና ችግሩን ምንጩ ካለበት ዘልቆ ማድረቅ ቢሆንም ይህ ሲሆን አልታየም። የወገኖቻችን አስከሬን መሬት ላይ እየተጎተተና ክቡር የሆነው ነፍስ እየተገበረ የሚቆጣጠሩትን ቦታ በተደጋጋሚ ለቀው እንዲወጡ ሲታዘዝ ቆይቷል። ለዚህ ሁሉ ነፍስ ላይ የሚቆመር ቁማር ተጠያቂ አልቀረበም።

ሌላውና ትልቁ መከራከሪያ ኢህአዴግ በሶማሊያ ያሰማራው ሁለት ዓይነት መልክ ያለው ሃይል መሆኑ ነው። ጌታቸው ረዳ ሰሞኑን እንደገለጸው በሶማሊያ አራት ሺህ ሰራዊት የሚገኝ ሲሆን፣ ሁለት ሺህ የሚሆኑት ከአሚሶም /በሶማሊያ የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ/ ጋር በጥምረት ሲሰሩ ቀሪዎቹ ሁለት ሺህ የሚሆኑት ከሰላም አስከባሪው ዕዝ ውጪ ኢህአዴግ አዲስ አበባ ሆኖ የሚያዛቸው ናቸው። አሁን ከየአቅጣጫው የሚወጡ መረጃዎችና ራሱ ህወሃት እንዳረጋገጠው ሶማሊያን ለቆ የወጣው ይኽው ከዕዙ ማዕቀፍ ውጪ ያለውና በህወሃት የጦር አዛዦች የሚመራው ጦር ነው። ይህ አሚሶም የማያዘው ሰራዊት በተደጋጋሚ የዕዝ ሰንሰለት እንደማይጠብቅና በሰላም ማስከበሩ ስራ ላይ ችግር መፍጠሩ በዩጋንዳና በኬኒያ በኩል ቅሬታ ሲሰነዘርበት ነበር።

ከሰላም አስከባሪው ዕዝ ወጪ የሚመራ ሃይል ለምን?

ህወሃት ብቻ መልሱን የሚያውቀው ይህ ጉዳይ ውስጡ ጊዜ ጠብቆ ገሃድ መሆኑ የማይቀር ቢሆንም ለምን? የሚሉት ክፍሎች የሚያነሷቸው እውነታዎች አሉ። “የአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ሃይል ሶማሊያ የገባው የፈረሰችውን አገር መልሶ ቅርጽ ያለው መንግስት ለማድረግ በሚል ከሆነ ህወሃት ተደራቢና አሚሶም የማያዘው ሃይል ያስገባው ምን የተለየ ፍላጎት ቢኖረው ነው?” ሲሉ የሚጠይቁት ክፍሎች ህወሃት ስውር አጀንዳ እንዳለው ይስማማሉ።

እነዚክ ክፍሎች ወደኋላ ሄደው የህወሃት ፊትአውራሪዎች በሽፍትነት ዘመናቸው ሶማሊያን መጠቀማቸውን ያስታውሳሉ። ተቀማጭነቱ ሎንደን የሆነ የሶማሌ ዜጋ አንጋፋ ስደተኛ “በሶማሊያ በጎሳ የመደራጀት ሃሳብ ብቅ ያለው የእነ መለስን እግር ተከትሎ ስለመሆኑ አውቃለሁ” ይላል። አያይዞም እነ መለስ ሙሉ ምስራቅ አፍሪቃ ጎሳን መሠረት ያደረግ አስተዳደር እንዲኖር ፍላጎታቸው እንደነበር ከእነሱ ጋር ቅርብ የነበረ አጎቱ እንዳጫወተው ይገልጻል። እንደሱ አባባል ህወሃቶች በሶማሊያ የጎሳ ንቅናቄ መሪዎችን ሙሉ በሙሉ ያውቋቸዋል። ለዚህም ነው ሶማሊያ በሚደረግ ጦርነት ውስጥ እንዳሻቸው መረጃ የሚያገኙት።

ይህ የሶማሌ ዜግነት ያለው ሰው ከሚሰጠው ፍንጭ በመነሳት ጉዳዩን የሚመረምሩ፣ መለስ ለወዳጆቹና ለአንጋሾቹ ኃያላን አገሮች “የሶማሊያን ጉዳይ ለኛ ተውት” ይል የነበረው በሶማሊያ የጎሳ ግጭት ውስጥ ያሉትን አመራሮች በደንብ ስለሚያውቃቸውና ግንኙነት ስለነበረው መሆኑንን መረዳት ቀላል ነው ባይ ናቸው። አልሸባብ ወደ ሶማሊያ ሲገባ ወይም የጎሳና የጎበዝ አለቆች ትግል በአልሸባብ ተጠልፎ የሶማሊያ ቀውስ ዓለም ዓቀፍ እውቅና ሲያገኝ ህወሃት “የጦርነት ንግድ ፈቃድ ወሰደ” ሲሉም ያክላሉ።

በፈረሰች አገርና ረሃብ በሚጠብሰው ህዝብ ስም የተቋቋመው ንግድ

ሶማሊያ ከፈራረሰችና ህዝቧም በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ችግር በረሃብ ከተጠበሰ በኋላ ማንም ጣልቃ እንዳይገባባት የመመከት ጉልብት አልነበራትም። የቻሉ ባህር ተሻግረው ሲሰደዱ፣ ያልቻሉ ጎረቤት ሃገር ኬኒያን መጠለያ አደረጉ። ወደ ተለያዩ አገራት ተሰደዱ። አዲስ አበባም በብዛት ገቡ። ህወሃት የጦርነት ንግድ ኮንትራት ፈርሞ ለሶማሊያ መድኅን ሆነ። አሸባሪን ለማንጠፍና የሶማሊያን ቅርጽ ያለው መንግስት ለመገንባት ምሎ ሃብታሞቹን አገሮች ያስደገድግ ጀመር። በዚህ የንግድ ዓለም የህወሃት የጦር መኮንኖች ዶላር ዛቁ። እየተፈራረቁ ኪሳቸውን ሞሉ። ደሃው ወታደር በቀን 50 ብር አበለ እየተከፈለው በማያውቀው ጉዳይ ሞተ። አስከሬኑ ተጎተተ። ከውሻም ባነሰ ክብር ሃሩር ውስጥ ተጠበሰ።

ከሁሉም በላይ ግን ሶማሊያ ለህወሃት አምባገነን አገዛዝ መባ የመሆኗ ቁማር አዋጪ ሆነ። የዴሞክራሲ፣ የፕሬስ፣ የፍትህና የርትዕ ጉዳይ ሲነሳበት ህወሃት “ከሶማሊያ እወጣለሁ” በሚል ያስፈራራ ገባ። በምርጫ 97 ህዝብ ድምጽ የከለከለው ህወሃት “ድምጽ ሰርቀሃል፣ ውረድ” ሲባል “ጦሬን ይዤ ወደ ትግራይ አፈገፍጋለሁ” /በወቅቱ ኢንዲያን ኦሽን የዘገበው ጉዳይ ነበር/ ማለቱ የቀደመው ማሳያ ሲሆን፣ ከ97 በኋላም በተደጋጋሚ አገር ቤት በሚፈጽመው ኢሰብዓዊ ጉዳይ ውግዘት ሲደርስበት ይህንኑ የተለመደ “ከሶማሊያ እወጣለሁ” ማስፈራሪያ እንደሚጠቀምበት አሁን አሁን ዓለም ያወቀው እውነት ሆኗል። ለዚህም ይመስላል የአሜሪካው እንደራሴ ክሪስ ስሚዝ “አንድ አገር ገና ለገና ሽብርተኛነትን ለመዋጋት ከአሜሪካ ጎን ስለቆመ ብቻ የህዝብ ሰብአዊ መብቶችና የዴሞክራሲ አተገባበር ላይ ዝም ሊባል አይገባም፤ ከአሜሪካ ጋር በአሸባሪ ጉዳይ ላይ ተባበሮ መስራት ሰብአዊ መብትን ለመርገጥ እውቅና አያስገኝም” ሲሉ የተናገሩት።

ከ2004 ጀምሮ እስላማዊ ፍርድቤቶች ኅብረት /ICU/ የመንግስት ቅርጽ ይዞ ሶማሊያን ማስተዳደር ሲጀምር ህወሃት ባላንጣዎቹን በመርዳት ቆይቶ በ2006 ጦሩን በማስገባት በዲሰምበር 28 አይሲዩን በማስወገድ ለሶማሊያ የሽግግር አስተዳደር ወገንተኛነቱን አረጋገጠ። ከዚያ ቀጥሎም ነገሮች በሶማሊያ ዳግም መልክ ወደ መያዝ ሲሄዱ ህወሃት ጦሬን አስወጣለሁ አለ። ከአንዳንድ ቦታዎችም ለቀቀ። ይህንን ታሪክ የሚያስታውሱ እንደሚሉት ህወሃት በፍጹም በሶማሊያ ሰላም እንዲሰፈን አለመፈለጉን የሚያሳይ፣ የዶላር ሸመታና የፖለቲካ የበላይነቱን በአገር ቤትና በቀጠናው የሚያስጠብቅበት አይነተኛ መሳሪያ ስለመሆኑ ነው። እነዚህ ክፍሎች ዛሬ ይህ ታሪክ መቀየሩን ነው የሚጠቁሙት። በጅምላ ግን ዋናው ጉዳይ ሶማሊያ የንግድ አውድማ፣ የዶላር ምንጭ ከመሆኗ በላይ የህወሃት መንታ ዓላማና ፍላጎቶች ማስፈጸሚያ የኩነኔ ምድር መሆኗን ነው።

ውስጣዊ ፍትጊያ

ሶማሊያ የከተተው በህወሃት የሚመራው ሰራዊት ዋጋ ከፍሎ የተቆጣጠራቸውን ከተሞች በአንድ ፊሽካ ቀጭን ትዕዛዝ በተደጋጋሚ እንዲለቅ ሲበየንበት ቅሬታ ማቅረብ መጀመሩ የውስጥ ፍትጊያ አስነስቷል። “ለምንድን” የሚል መከራከሪያም ቀርቦበታል። ውስጥ አዋቂዎች እንደሚሉት ይህንን በማለታቸው “የተሰወሩ” አሉ። በተመሳሳይ የከፋቸው ርምጃ የወሰዱባቸው ሃላፊዎች አሉ። ይህም ቢሆን አመራሩ የተጠረነፈው በራሱ በህወሃት ታማኞች በመሆኑ ፍትጊያው ከኩርፊያ የሚያልፍ አልሆነም።

ዋናው ፍትጊያ ግን ከሃብታሞቹ አንጋሾቻቸው ጋር እንደሆነ ከግምት በላይ ይታወቃል። ለጎልጉል መረጃ የሚያቀብሉ እንደሚሉት፣ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ሁኔታ አደገኛ በመሆኑ ጫና የበዛበት የትግራይ ሕዝብ ነጻአውጪ ግምባር ተገንጣይ ቡድን የክፉ ጊዜ ካርዱን በመጠቀም የተነሳበትን ውጫዊ ጫና ለመቀነስ የለመደውን ጦር የማስወጣት አጅንዳ እውን አድርጓል። እዚህ ላይ የሚነሳው ትልቁ ጉዳይ “ራሱን ችሎ ተደራጅቷል” የሚባለው የሶማሊያ ብሔራዊ ጦር ለሰዓታት እንኳን ከተሞቹን ሊቆጣጠር በማይችልበት ሁኔታ አልሸባብ የተለቀቁትን ከተሞች መልሶ መቆጣጠሩ ነው። ቢያንስ አሁን ሶማሊያን ለሚመራው አስተዳደርና ለአሚሶም የዕዝ አካል እንኳን ትንፍሽ ሳይባል የተከናወነው ማፈግፈግ፣ ከአልሸባብ ጋር በመናበብ የተከናወነ ያስመስለዋል የሚል የሃሳብ ፍትጊያ አስነስቷል።

ህወሃት ራሱ አሸባሪ ተቋም ይሆናል ተብሎ መጠርጠሩ

በቅርቡ ለሚዲያ ራሳቸውን ያቀረቡት አቶ ጁነዲን ሳዶ “አሸባሪ የሚባል ነገር የለም። ፈጠራ ነው” ማለታቸው አሁን ለተነሳው አስኳል ጉዳይ መደገፊያ ይሆናል። ምክንያቱም አሸባሪ ከሌለ የሽብር ተገባር ከቶውንም ሊከናወን አይችልም። ከዚህ ሃሳብ ጋር በተዛማጅ ዌኪሊክስ በተለያዩ ጊዜያት አዲስ አበባ በህዝብ ትራንስፖርትና መገልገያ ስፍራዎች ላይ ቦንብ በማፈንዳት “አሸባሪዎች ፈጸሙት” የሚል ታቤላ ሲቀርብባቸው የነበሩትን አደጋዎች ሙሉ በሙሉ ህወሃት ራሱ ያከናወናቸው እንደነበሩ ማጋለጡ ሌላው ቁልፍ ጉዳይ ነው። ጎልጉል ያነጋገራቸው የአሜሪካ ዲፕሎማት በበኩላቸው “ራሱ ህወሃት ይጠረጠራል” ይላሉ። እንዴት?

“ለኢትዮጵያም ሆነ ለማንኛውም አገር ህዝብ ጥቃትን አልመኝም። ግን እኛ አሁን የምናስበው ኢትዮጵያ ጦሯን ልካ አልሸባብን ደብድባለች፣ አላማውን አክሽፋለች፣ ብዙ ኪሳራ አድርሳበታለች። ቂም ተያይዛለች፤ ግን ጎረቤት ኬንያ፣ ዩጋንዳና ታላላቅ በሚባሉ አገሮች እንደታየው አይነት ጥፋት በኢትዮጵያ ተሰምቶ አያውቅም” ሲሉ እንዴት የሚለውን ጥያቄ ከመለሱ በኋላ ጠልቆ መመርመር የዜጎች ድርሻ መሆኑን ይጠቁማሉ። አሁን ሶማሊያን ለቅቀው ስለመውጣታቸው ዝርዝር አስተያየት ባይሰጡም “አርባ ምንጭ የነበረው የአሜሪካ የጦር ቤዝ መዘጋቱን አታውቁም?” በማለት ይጨርሳሉ።

በጃንዋሪ 2016 አሜሪካ አርባምንጭ ላይ የነበራትን የጦር መሰረት መንቀሏን በስምምነት የተደረገ፣ ሲጀምርም በቋሚነት ያልተቋቋመ እንደነበር ለቢቢሲ ብትነግርም፣ የጦር ቤዙ አላማ በምስራቅ አፍሪካ ከአልቃይዳ ጋር ግንኙነት ያላቸውን የሽብርተኝነትን እንቀስቃሴዎች ለመቆጣጠርና ልክ ለማስገባት ነበር። የአሜሪካ ሰው አልባ ድሮንና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚመራው የጦር መሰረት መዘጋቱ በተንታኞች ዘንድ “አሜሪካ በቀጣናው ከሽብር ጋር ያላትን ስራ ማጠቃለሏን ያሳያል” የሚል እምነት አሳድሯል። አስፈላጊም ከሆነ ጅቡቲ ያላት የጦር ወረዳ ከበቂ በላይ እንደሆነ ያመላክታሉ።

የሶማሊያን ጉዳይ ከአሚሶም ውጪ የግል መደራደሪያው ለማድረግ በህወሃት ሃይል ብቻ የሚመራ ሰራዊት ማዝመቱ “ህወሃት ሲያሻው የሚያበራው፣ ሲያሻው የሚያጠፋው ባልቦላ እንዳለው የሚያሳይ ነው” ሲሉ የሚናገሩ፣ “ገና ከመነሻው አሸባሪ የሆነው ህወሃት ከአሚሶም ውጪ ሰራዊት ያዘመተበት ምክንያትና ከጋራ ሃይሉ ተለይቶ የምስኪን ወገኖችን ህይወት እየገበረ በረሃ ለበረሃ የሚርመጠመጥበት ሌላ ጉዳይ ሊኖረው አይችልም” ሲሉ የቀድሞ ታሪኩን በመጥቀስ የ“ሽብር ሃይል” ከሚባሉት ጋር ይደምሩታል። እናም ከላይ እንደተባለው ጦርነትና ረሃብ ያነፈራት ሶማሊያ ለህወሃት ሲሳይ ሆና ቆይታለች። ሕዝቧም በሞትና በህይወት መካከል ሆኖ ይቆመርበታል

ምንጭ ጎልጉል

Exit mobile version