Site icon ETHIO12.COM

የትግራይ ክልልን መልሶ የመገንባትና የሰብዓዊ ድጋፍ ስራው ተጠናክሮ ቀጥሏል- አቶ ደመቀ መኮንን

የትግራይ ክልልን መልሶ የመገንባትና የሰብዓዊ ድጋፍ ስራው ተጠናክሮ መቀጠሉን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ገለጹ።

አቶ ደመቀ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት አዲስ አበባ የሚገኙትን የእንግሊዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶሚኒክ ራብን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

በትግራይ ክልል የህግ ማስከበር ዘመቻ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁንና በአሁን ወቅት ክልሉን መልሶ የማቋቋምና የሰብዓዊ ድጋፍ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አቶ ደመቀ አብራርተውላቸዋል ።
ውይይቱን የተከታተሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ እንደገለጹት አቶ ደመቀ በአሁኑ ጊዜ በትግራይ ክልል ለሚደረጉ የሰብአዊ ድጋፎች መንገዶች ሁሉ ክፍት መሆናቸውን አስረድተዋል።

በክልሉ 85 በመቶ በሚሸፍነው አካባቢም የምግብ እና የመድኃኒት አቅርቦት እየተዳረሰ መሆኑን ገልጸዋል ነው ያሉት።

ከሱዳን ጋር በድንበር አካባቢ የተፈጠረው ያልተገባ ችግር በሰለጠነ መንገድ እንዲፈታ ኢትዮጵያ ጥረቷን አጠናክራ እንደምትቀጥልም አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ እና ሱዳን ስርታቴጂክ አጋር እንደመሆናቸው ችግሩን በሰለጠነ እና በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ፅኑ አቋም አንዳላትም ለእንግሊዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ማብራራታቸውን ነው የገለጹት።

የህዳሴ ግድቡ የሦስትዮሽ ድርድር በጋራ መግባባት ላይ ተመስርቶ እንዲካሄድና የታችኞቹ ተፋሰስ አገሮች ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ኢትዮጵያ ከፍተኛ ጥንቃቄ እያደረገች መሆኑንም በእዚህ ወቅት ተመላክቷል።

የሦስቱ አገሮች ድርድር በአፍሪካ ሕብረት በኩል መካሄዱም ሀገራቱ የጋራ መግባባት ላይ ለመድረስ ያስችላቸዋል የሚል እምነት መኖሩንም እንዲሁ።

ኢትዮጵያ ለአረንጓዴ ልማትና አካባቢ ጥበቃ ቁርጠኛ አቋም ይዛ የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነች ስለመሆኗም አቶ ደመቀ ማብራራታቸውን አምባዳሰር ዲና ጠቁመዋል።

የእንግሊዙ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶሚኒክ ራብ በበኩላቸው፤ የሁለቱ አገሮች ጥልቅ ግንኙነት በጠንካራ ትብብር ላይ የተመሰረተ መሆኑን ነው ያነሱት።
Via ENA

Exit mobile version