Site icon ETHIO12.COM

የራያ አባቶች የረገሙት በሕይወት አይኖርም፣ ልጆቹ አያድጉለትም፣ ያረሰው ሰብል አይሰጥም ተብሎ

የራያ አባቶች የረገሙት በሕይወት አይኖርም፣ ልጆቹ አያድጉለትም፣ ያረሰው ሰብል አይሰጥም ተብሎ ይታመናል፤ ይሄን የሚጥስም የሚያረክስም የለም፡፡ እኒያ ታላላቅ የሰላም አባቶች ዳኛ ሊያደርጉት የሚፈልጉትን ችሎት እያሳዩ እንደሚያሳድጉትም ይነገርላቸዋል፡፡ ሰው ገድሎ በዘወልድ፣ በመዛርድ፣ በክፍሎ ወይም በስንየ ስገድ አምላክ ከተባለ አይሮጥም፣ ቤተክርስቲያን ከተጠለለ አይነካም፣ ከራያ አባቶች ቤት ውስጥ ከተጠለለ ለጥል እጅ አይነሳበትም፡፡

‹‹ተለመነኝ መዛርድ፣ ተለመነኝ ዘወልድ ባክህ ስንየ ስገድ እሺ በለኝ ክፍሎራያና ቆቦ ዋጃና አላማጣ መሆኒና ጨርጨር ከደጋጎች ሀገር ልቤ ይርጋ ወሎ›› የደግነት ማዕከል፣ የፍቅር ማዕበል፣ የአንድነት መሰላል፣ የመቻቻል ሚዛን፣ የመልካም ንግግር ልሳን፤ የፍቅር ሸማ እያለበሱ፣ በአንድነት ሞሶብ እያጎረሱ፣ አምላካቸውን እያወደሱ መኖር መገለጫቸው ነው፡፡ ወሎ ውስጥ ከምንም ነገር በፊት ሰውነት ይቀድማል፡፡

‹‹አብሽር አቦ›› በሚለው የመፅናኛ ቃላቸው የተጨነቀን ሲያረጋጉ ምነው ከእናንተ ባይለየኝ ያስብላሉ፡፡ ‹‹ መራርጠህ መራርጠህ ከዲቡ አኑራቸው፣ ሀገር የሚያናውጥ ወጀብ የመጣ ለት መመከቻ ናቸው››የሚባልላቸው ራያዎች ጀግንነት፣ አንድነት፣ ኢትዮጵያዊነትና አርቆ አሳቢነትን ያውቁበታል፡፡ ራያዎች ወዳጅን በፍቅር፣ ጠላትን በጦር መመለስ ይችሉበታል፡፡ የራያዎች አለባበሳቸው፣ የንግግር ቃናቸው፣ መውዜርና ዝናራቸው ሲታይ ያማልላል፡፡

ራያዎች የአያሌ ባሕል፣ ወግ፣ ታሪክ፣ ትውፊትና እሴት ባለቤት ናቸው፡፡ ከዘመን ዘመን ተሻግሮ ሕዝብን አስተባብሮ፣ በፍቅር አኑሮ፣ ለፍቅር፣ ለሰላምና ለአንድነት የሚተጋ አንድ ውብ ባሕል አላቸው ራያዎች፤ ውብ የሽምግለና ሥርዓት፡፡እኒህን አባቶች የራያ አባቶች ወይም የወንዝ አባቶች ይሏቸዋል፡፡ የእነርሱ ዘንግ ከተዘረጋች፣ አንደበታቸው ንግግር ከጀመረች፣ ስለ ፍቅር ተው ካለች ጀምሮ ለጥል የሚነሳ አይገኝም፡፡

የወንዝ አባቶች የተከበረ ሀሳብ ያላቸው ናቸውና ክቡሮች ናቸው፡፡ የራያ አባቶች የገጭት አፈፋት ስርዓት ዘመንን የተሻገረ፣ ባለው መልካም እሴት ልክ ግን ያልታወቀ ነው፡፡ የባሕላዊ ሽምግልና ሥርዓቱ ከአራት ወንድማማቾች ስም የጀመረ መሆኑ ይነገራል፡፡ ዘወልድ፣ ስንዬ ስገድ፣ ክፍሎና መዛርድ ናቸው ወንድማማቾቹ፡፡

መልካም ፍሬ ሲያፈራ መታደል ነውና እነዚህ ወንድማማቾች አካባቢ ተከፋፍለው የሽምግልና ሥርዓታቸውን ይከውናሉ፡፡ የተከፋፈሉትም አቦሆይ ጋራ ሥር እንደሆነ ይነገራል፡፡ አቦሃይ ጋራ ከራያ በስተ ምዕራብ በኩል የሚገኝ ታሪካዊ ሥፍራ ነው፡፡ ቦታው በውኃ ማማነት ይታወቃል ይባላል፡፡ መዛርድ በምስራቅ ሁሞ፣ በምዕራብ አፅብ፣ በሰሜን አሮሮሻ ወንዝ፣ በደቡብ ማርሳ ወንዝ እያዋሰኑት ያስታድራል፡፡

ስንየ ስገድ በምስራቅ ሆርማትና ጎሊና የሚገናኙበት መገናኛ የሚባለው ቦታ፣ በምዕራብ ወደ ላይ ዲኖ ድረስ ፣ በሰሜን ሆርማት በደቡብ ጎሊና ወንዝ ድረስ ያስተዳድራል፡፡ ክፍሎ በምስራቅ አፋር ሐገር ሀሸንቶ ጎሳ ጋር፤ በሰሜን ምስራቅ በዞብል ወጥቶ ወይሩ ቀርጨማን ሚካኤልን አድርጎ ጨፈቃ ውሐ ይገባል፣ በምእራብ አንጎትት ደጋ ጋር ይገናኛል፣ በሰሜን አላውሐ ጋር ይገናኛል፡፡

ዘወልድ ደግሞ ከሰሜን ጎቡ ወንዝ፤ ከደቡብ ሆርማት፣ ከምስራቅ ሐገር ብሩ ጎራ፤ ከምዕራብ አቦሆይ ጋሪያ ድረስ በዘወልድ የሚታደደር መሆኑን የባሕል አጥኚው ምስጋን ደስዬ ነግረውኛል ፡፡ በመልካም ሥነ ምግባራቸው የሚታወቁት እዚህ ታላላቅ ሰዎች ሰው ከሰው ጋር ሲጋጭ በማስታረቅ፣ ሰላምና ፍቅር በሀገር እንዲነግስ ሲሰሩ የነበሩ ናቸው፡፡ አሁንም የእነርሱ ልጆች መልካም ሥራቸውን አስቀጥለውታል፡፡

አራቱ አባቶች ያልተፃፈ ነገር ግን የማይሻር የተከበረ ሕግ ይዘው ሲያስተዳድሩ እንደነበር ይነገርላቸዋል፡፡የራያ አባቶች በሽምግልና ሥርዓቱ አይዋሹም፣ በሀሳት አይመሰክሩም፣ አንደኛውን ተጠቃሚ ሌላኛውን ተጎጂ የሚያደርግ ፍርድ አይፈርዱም፡፡ እውነት፣ ታማኝነት፣ አርቆ አሳቢነትና የሁሉም አባትነት መለያቸው ነው፡፡ የራያ የወንዝ አባቶች ሕዝቡ የሚያምናቸው፣ ፍርድ አዋቂ፣ ለሁሉም እኩል ተመልካች፣ ተከባሪና ቅቡል ናቸው፡፡

በራያ የባሕላዊ እርቅ ስርዓት መሠረት ቀይ ደምና ጥቁር ደም የሚከፈል አለ፡፡ ቀይ ደም ማለት በደንገተኛ፣ ሳይታሰብ፣ በእለታዊ ግጭት፣ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት፣ በመቀላለድ፣ የሚፈፀም የግድያ አይነት ነው፡፡ ጥቁር ደም ደግሞ ታስቦበት፣ በቂም በቀል፣ አባሪ ተባባሪ በመሆን የሚፈፀም ግድያ ነው፡፡ የጥቁር ደም የካሳው መጠን ከቀይ ደም ከፍ ያለ ነው፡፡ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በራያ አባቶች ሥም እየተጠራ ሀገርና ሕዝብ የሚያስታርቅ ከአራቱ ወንድማማቾች የዘር ግንድ መመዘዝ ያስፈልግ እንደነበር ይነገራል፡፡

ከዚያ ወዲህ ግን አባቶቹ በሁሉም ዘንድ ቅቡል በመሆናቸው የዘር ግንድ መቆጠር ቀርቶ መልካም ሰው የሆነ የራያ የሽምግልና አባት መሆን ይችላል፡፡ ለወንዝ አባትነት የሚመረጡት በሥነ ምግባራቸው የተመሰገኑ፣ ቤታቸውንና ሕይወታቸውን በሥርዓት የሚመሩ፣ ሐቀኛ የሆኑ፣ አንደበተ ርቱዕ የሆኑ፣ ሙስናን የሚፀየፉ፣ የማስታረቅ አቅማቸው ከፍ ያለ፣ ሰውን በዘርና በሃይማኖት የማይለዩ ናቸው፡፡ የዛፍ ጥላ፣ አሸዋማ ቦታና የቤተክርስቲያን ማርገጃ ለእርቅ የሚመረጡ ቦታዎች ናቸው፡፡

በተለይም ደረቅ አሸዋ ይመረጣል ይባላል፡፡ ለምን ካሉ እርቁም በአሸዋው አምሳያ ደርቆ እንዲቀር ስለሚፈለግ ነው፡፡ በራያ ባሕል በዳይ ሲበድል ለሀገር ሽማግሌዎች ጋር ሄዶ ‹‹እጄ ስቷል እባካችሁን›› ብሎ ይጠይቃል፡፡ የሀገር ሽማግሌዎችም ጉዳዩን እንደሰሙ የበዳይ ቤተሰብን የመጠበቅና የተበዳይ ወገኖችን የመማለድ ሥራ ይሰራሉ፡፡ተበዳዮች በስሜት የበዳዩን ወገን ጉዳት እንዳያደርሱና ጥሉ እንዳይሰፋ ቀድሞ በመድረስ የማረጋጋትና የከለላ ሥራ ይሰራል፡፡ በመቀጠል ተበዳዩ እንዲታረቅና ይቅር እንዲል የማግባባት ሥራ ይሠራል፡፡

በዳይና ተበዳይ ተገናኝተው እርቅ ሊፈፀም ሲል ካሕናት ይመጣሉ፣ እናቶች እርፎ መረባ ይላሉ፣ ሼሆችም ይቀርባሉ፡፡ ካህናቱና ሼሆቹ እርቁ እንዲሰምር በየኃይማኖታቸው ለፈጣሪያቸው ምልጃ ሲያቀርቡ እርፎ መረባ የሚሉት እናቶች ደግሞ ፡-

‹‹ እርፎ መረባ …. መረባ

የሞተው ጀነት ይግባ…. መረባ

ያሉት ልጆች ይደጉለት…….መረባ

ለሞተው ነብሱ ይማርለት……መረባ

ጀመረ አቡየ መጀን………መረባዘለወድ መጀን…….መረባከፍሎ አባችን መጀን…..መረባስንየ ስገድ መጀን……………መረባ

ደም መቃባትስ አይበጀን……….መረባ እያሉ ይማፀናሉ፡፡

እርቅ ሲሆን ባላንጣ የነበሩ ሰዎች እየተጎራሱ በጋራ ይመገባሉ፡፡ ‹‹ይቅር ስለ እግዚአብሔር›› ይባባላሉ፡፡ ጥሉ ይሽራል፡፡ ፍቅር ይወርዳል፡፡ እነኚህ ወንድማማቾች በዘመነ ትህነግ ተከፋፍለው ነበር፡፡ ትህነግ ራያን ከፍሎ ሲወስድ መዛርድን ከወንድሞቹ ነጥሎ ወስዶት ነበር፡፡ ትህነግ መዛርድን አንቀበልም ጎጅ ልምድ ነው በማለት ለማጥፋት ሞክሮ እንደነበርም የመዛርድ ምክትል ሊቀመንበር ካሳው ከበደ ነግረውኛል፡፡ ወያኔ ባሕሉ እንዳያድግ፣ እንዳይሰፋ፣ ሰው እንዲፋጅ ይፈልግ ነበር፤ ሰውና ሰው ተገናኝቶ እንዲመካከር አይፈልግም፡፡

በተለይ ደግሞ ስለ ራያ አባቶች ባሕል የሚያውቁትን ሰዎችን ትኩረት ያደርግ እንደነበርም ነግረውኛል፡፡በራያ ወንድማማቾች ሕግ መሠረት አንደኛው የወሰነውን ሌላኛው አይቃወመውም፡፡ አንደኛው የሠራውን ሌላኛው ያፀድቃል፡፡ ለምን ካሉ የራያ አባቶች መልካም ነገር ስለሚወስኑና ቅቡል ስለሆነ ነው ይላሉ አበው፡፡

የራያ አባቶች ከፊቱ ቆመው አሻፈረኝ የሚል ደንዳና ልብ የለም፤ መጎዳት ልቡን ቢሰብረውም፣ መበቀል ቢከጅለውም የራያ አባቶች ተው ካሉ ይተዋል፡፡ በአባቶች አልገዛም ያለ ካለ ‹‹እምበደዴ›› ይባላል፡፡ ከማኅበረሰቡ ይገለላል፤ ከማኅበራዊ ሕይወት ይወጣል፤ እቃ መዋዋስ አይችልም፤ እርሱ ብቻ ሳይሆን ከእርሱ ጋር የተወዳጄ ሁሉ ከማኅበረሰቡ ይገለላል፡፡

ከዚህ ሁሉ ቅጣት ላለመድረስና ለአባቶች ያለውን ፍቅር ለማሳዬት ‹‹ታረቅ›› የተባለው ሁሉ እሺ ይላል፡፡ አንደበታቸው የተከፋችን ልብ ይጠግናል፣ ለበቀል የተነሳን ልብ ለፍቅር እጁን እንዲሰጥ ያደርጋል፣ የጋለውን ያበርዳል፣ የተለያየውን ያገናኛል፣ የተራራቀውን ያቀራርባል፣ የተጣለውን ያፋቅራል፡፡እኒያ የፍቅርና የሰላም አባቶች በዘንጋቸው ሀገርን ያዋድዳሉ፣ ሕዝብን ያፋቅራሉ፡፡

ራያ ፍቅር ነው፣ በአባቶቹ ይመከራል፣ አባቶቹን ያከብራል፤ እምቢ ያለው ‹‹ሀገር እንዳታስረግም፣ ከአባት ወግ እንዳትወጣ›› ሲባል እሺ ይላል፡፡ ራያ በአንድ የፍቅር ዘንግ ይመራል፡፡ የራያ አባቶች ህግጋት በወረቀት ሳይረቁ ገና አስገራሚ ህግጋት ነበሯቸው፡፡ በቀደመው ዘመን ሀገር ሲደፈር መንግሥት ወደ ጦርነት ሲገባ የራያ አባቶችን ሳያማክር ወደ ጦርነት እንደማይገባ የባሕል አጥኚው ምስጋን ደስዬ ነግረውኛል፡፡

የሕጻናት፣ የሴቶችና የአቅመ ደካሞችን መብት አስከባሪ፣ የጦር መሪና በርካታ ስርዓት እንደነበራቸውም ነግረውኛል፡፡ የራያ ሕዝብ አኗኗሩ አብዓዊ ስርዓት ነው፣ እርቅ በዳይ ሲክስ፣ ተበዳይ ሲካስና የተበዳይን ሕመም ሌላው ሲያውቁለት ይደርቃል ይላሉ፡፡ የራያ አባቶችም እርቅን ያደርቃሉ፣ ቂምን ይሽራሉ፤ በራያ እንኳን ለገደለ ለሰደበም መቀጫ ሕግ እንዳለው ይነገራል፡፡

የራያ አባቶች የረገሙት በሕይወት አይኖርም፣ ልጆቹ አያድጉለትም፣ ያረሰው ሰብል አይሰጥም ተብሎ ይታመናል፤ ይሄን የሚጥስም የሚያረክስም የለም፡፡ እኒያ ታላላቅ የሰላም አባቶች ዳኛ ሊያደርጉት የሚፈልጉትን ችሎት እያሳዩ እንደሚያሳድጉትም ይነገርላቸዋል፡፡ ሰው ገድሎ በዘወልድ፣ በመዛርድ፣ በክፍሎ ወይም በስንየ ስገድ አምላክ ከተባለ አይሮጥም፣ ቤተክርስቲያን ከተጠለለ አይነካም፣ ከራያ አባቶች ቤት ውስጥ ከተጠለለ ለጥል እጅ አይነሳበትም፡፡

የራያ አባቶች ያልታዬው ውብ ባሕል እንዲታይ ይሻል፡፡ የራያ የፍቅር ዘንግ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊያን ታስፈልጋለችና፡፡ኢትዮጵያ ድንቅ ናት ሁሉም ነገር ያላት፡፡ ኢትዮጵያ ቀደምት ናት ሁሉም የተከተላት፡፡ ኢትዮጵያ መሪ ናት ሁሉም የሚገዛላት፣ ኢትዮጵያ አሸናፊ ናት ማይታጠፍ ክንድ ያላት፣ ኢትዮጵያ ምስጢር ናት ያልተመረመረ ታሪክ ያላት፡፡ ኢትዮጵያ የቀደመች፣ የታደለች፣ የተመረጠችና የተከበረች ሀገር ናት፡፡

ስለ እርሷ የሚያስብ መልካም አዕምሮ፣ የሚሠራ እጅ፣ እርሷን በጥልቀት የሚያይ መልካም ዓይንና ልቦና ያስፈልጋል፡፡ ያን ጊዜ ውበቷ ይታያል፣ ሚስጥሯም ይገለጣል፡፡ ‹‹አባት ይሙት ብሎ እንዴት ይምላል ሰውአሞተ መራሩን ራያን ሳይቀምሰውእንገናኝ እንጂ ማን ሊቀር ማን መቶየእነ ልባ አውቃ ሀገር አማያ ተጠርቶ›› በታርቆ ክንዴ

(አብመድ)

Exit mobile version