ቅዱስ ፓትርያርኩ ” የሃይማኖት አባቶች ከፓለቲካ ገለልተኛ በመሆን ሁሉን በፍቅርና በእኩልነት ማቀራረብ ይገባቸዋል ” ሲሉ በ11ኛ ዓመት በዓለ ሢመታቸው ተናገሩ።
ፓለቲከኞቾም ባልዋሉበት እና ባልተፈቀደላቸው ቦታ በቤተክርስቲያን ጉዳይ ጣልቃ ከመግባት እንዲቆጠቡ አሳስበዋል። ቅዱስነታቸው ” የዘመናችን ትውልድ ከተግባር ይልቅ አስመሳይ ሆኖ መታየትን ከቅድስና ይልቅ ነውረ ኃጢአትን፤ ከትሕትና ይልቅ ትዕቢትን የተለማመደ ለሃይማኖትም ሆነ ለማኅበረ ሰብ ጤና ያልተመቸ ትውልድ እንደሆነ በግልጽ ይታያል ሲሉ ተግሳጽ አሰምተዋል።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቀነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት 11ኛ ዓመት በዓለ ሢመታቸውን አስመልክቶ ምን አሉ ?
- ያለንበት ዘመን ለእግዚአብሔር ክብርን የነሣ፤ ከፍቅርና ከአንድነት የራቀ ራስ ወዳድነትና በቃኝ አለማለትን የወረረው፤ በዘመን አመጣሽ ቴክኖሎጂ የተዋጠ ትውልድ የታየበት ዘመን ነው።
- የዘመናችን ትውልድ ከተግባር ይልቅ አስመሳይ ሆኖ መታየትን ከቅድስና ይልቅ ነውረ ኃጢአትን፤ ከትሕትና ይልቅ ትዕቢትን የተለማመደ ለሃይማኖትም ሆነ ለማኅበረሰብ ጤና ያልተመቸ ትውልድ እንደሆነ በግልጽ የሚታይ ነው፤ ይህን አደገኛ አዝማሚያ በማስተዋል ካልታረመ ሂዶ ሂዶ የእግዚአብሔርን ቁጣ ማስከተሉ አይቀርምና እንደ እግዚአብሔር ጥሪ ወደ እሱ ብንመለስ ይሻላል።
- እኛ የሃይማኖት አባቶችም አልጫ የሆነውን የዘመናችንን ትውልድ በትጋት አስተምረን በቈራጥነት ገሥጸንና መክረን ወደ እግዚአብሔር ካልመለስነው ከቁጣው አንድንም። ቅዱስ መጽሐፍ እንዳስተማረን አስተምረነው የማይመለስ ከሆነ ደሙ በራሱ ላይ ይሆናል! እኛ ባለማስተማራችን የሚጎዳ ትውልድ ካለ ግን እኛ የደሙ ተጠያቂዎች መሆናችንን በማያሻማ ሁኔታ ተገልጾአልና ነው፤ የእኛ ኃላፊነት እስከዚህ ድረስ ከባድ መሆኑን ባንዘነጋውም እንደ ዓለሙ በልዩ ልዩ ደካማ አስተሳሰቦችና ተግባራት እየተሰናከልን መሆናችን የአደባባይ ምሥጢር ከሆነ ውሎ አድሮአል።
- እኛ የሃይማኖት አባቶች ዓለም ሲሳሳት ከመገሠጽ ይልቅ አብሮ ማጨብጨብ ተለማምደናል፤ ባናጨበጭብም ዝምታን መርጠናል ነገር ግን ኃላፊነቱን የተረከብነው ጥፋት ሲፈጸም ዝም ብሎ ለማየት አልነበረም፤ ከዓለሙ ጋር አብሮ ለማጨብጨብ ወይም አድማቂ ለመሆንም አልነበረም፤ ከቅዱስ ወንጌሉ መሠረተ ሐሳብ ፍንክች ሳንል ፦
- የእውነት፥
- የፍትሕ የሰላም፥
- የፍቅር፥
- የዕርቅ የይቅርታ የአንድነት፥
- የስምምነት ጠበቃ መሆናችንን ማሳየት ነበረብን፣ ሰውን ሁሉ በእኩልነት በመቀበልና የሁሉም እኩል አባቶች መሆናችንን በተግባር ማስመስከር ይገባን ነበር፤ የተዛባውን በማረም ትውልዱን ለማዳን ያደረግነው ጥረት የሚያረካ እንዳልሆነ ታዛቢው ሁሉ አይቶብናል፡፡
- ለፈተና የተጋለጡ ልጆቻችን ሁሉ የዜግነት የሃይማኖትና የሰብአዊ መብታቸው እንዲከበር ሰላም ፍቅር፥ ፍትሕ አንድነት በሀገር እንዲነግሥ ሁሉም ድንበሩን ጠብቆ ሕዝቡን የሚያገለግልበት ዓመት እንዲሆን ከመቼውም ጊዜ በላይ በርትተን መሥራት አለብን። ይህንን ብናደርግ በእውነትም ወደ እግዚአብሔር ተመልሰናል ማለት ነው፤ እኛ ከተመለስን እሱም ወደ እኛ መመለሱ አይጠረጠርም፤ ስለዚህ አሁንም ወደእሱ እንመለስ፡፡