Site icon ETHIO12.COM

ለጃዋር የሞባይል ሲም ካርድ ሊያቀብሉ ሲሉ ተያዙ የተባሉ ተጠርጣሪ ዋስትና ጠየቁ

ለአቶ ጃዋር መሃመድ አራት የሞባይል ሲም ካርዶችን ሊያቀብሉ ሲሉ በቁጥጥር ስር ውለዋል ተብለው ፍርድ ቤት የቀረቡት ሃምዛ ጀማል በቦሌ ክፍለ ከተማ ቋሚ አድራሻ ስላላቸውና የሚተዳደሩት ቨጪሮ ጫት ንግድ በመሆኑ በዋስ እንዲለቀቁ ጠየቁ። ፍርድ ቤት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ፈቀደ።

በቃሊቲ ማረሚያ ቤት በሚገኙት ለአቶ ጃዋር መሃመድ አራት የሞባይል ሲም ካርዶችን ሊያቀብሉ ሲሉ በቁጥጥር ስር ውለዋል ተብለው ፍርድ ቤት የቀረቡት ሃምዛ ጀማል ጉዳያቸው ታይቷል፡፡ተጠርጣሪው በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ የጊዜ ቀጠሮ ችሎት ዛሬ የቀረቡ ሲሆን ከሁለት ጊዜ በላይ ቀርበው ጉዳያቸው ታይቷል፡፡

ተጠርጣሪው አንድ በኦ .ኤም.ኤን ድርጅት ስም የወጣ እና ሶስት በግለሰብ ስም የወጣ የሞባይል ሲም ካርድ ማረሚያ ቤት በመሄድ ለአቶ ጃዋር ሊያቀብሉ ነበር ተብለው በተደረገባቸው ምርመራ፥ ከአቶ ጃዋር እና ከኦ .ኤም.ኤን ሚዲያ ጋር በተያይዘ የተለዋወጧቸው የስልክ መልዕክቶች ከብሄራዊ መረጃ እና ደህንነት ተቋም ማምጣቱንም መርማሪ ፖሊስ ለችሎቱ አብራርቷል፡፡

የምርመራ መዝገቡንም ለዐቃቤ ህግ ልኮ እየተመለከተ መሆኑን የገለፀው መርማሪ የሰው ማስረጃ ከማረሚያ ቤት አስተዳደር አመራሮች እና በእለቱ ጥበቃ ላይ ከነበሩ የጥበቃ ሰራተኞች ቃል የመቀበል ስራ መስራቱን ገልፆ ከእርሳቸው ጋር በትብብር ሲሰሩ ነበር የተባሉ ግብረ አበሮችን በቁጥጥር ስር ለማዋል እና ቀሪ የምስክር ቃል ለመቀበል ተጨማሪ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ገልጿል፡፡ተጠርጣሪው ከጠበቃቸው ጋር የቀረቡ ሲሆን እስካሁን ለፖሊስ የተሰጠው የምርመራ ጊዜ በቂ መሆኑን ጠቁመው የሚያዙት ግብረ አበሮች ማንነታቸው ሳይገለፅ ለመያዝ ተብሎ ተጠርጣሪውን አስሮ ማስቀመጥ ተገቢ አይደለም ሲሉ ተቃውመዋል፡፡

ተጠርጣሪው ጭሮ ከተማ የሚኖሩ እና በጫት ንግድ መሰማራታቸውን ጠቅሰው አሁን በሚኖሩበት አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ ቦሌ ክፍለ ከተማ ቋሚ አድራሻ ስላለኝ ዋስትና ይሠጠኝ ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ፍርድ ቤቱም የምርመራ መዝገቡን አስቀርቦ መርምሮ ትዕዛዝ ለመስጠት ለየካቲት 3 ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መሰጠቱንበታሪክ አዱኛ የተዘጋጀው የፋና የፍርድቤት ዘገባ ያመለክታል።

Exit mobile version