Site icon ETHIO12.COM

በትግራይ የዕለት ደራሽ እርዳታ የማድረስና ተጎጂዎችን መልሶ የማቋቋም ስራዎች ቀጥለዋል – የሠላም ሚኒስቴር

በትግራይ ክልልና ሰብዓዊ ድጋፍ በሚያስፈልጋቸው አካባቢዎች የዕለት ደራሽ እርዳታና የመልሶ ማቋቋም ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን የሠላም ሚኒስቴር ገለፀ።

በክልሉ 26 መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የዕለት ደራሽ እርዳታ በመስጠቱ ተግባር በቅንጅት እየሰሩ መሆኑንም አስታውቋል።

የሠላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል በትግራይ ክልልና በመተከል ዞን  እየተካሔደ ያለውን የሠብዓዊ ድጋፍና የመልሶ ማቋቋም ስራ የተመለከተ መግለጫ ሰጥተዋል።

በትግራይ ክልል የህግ ማስከበሩን ስራ ተከትሎ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ዜጎች የዕለት ደራሽ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው በመጀመሪያ ዙር በተካሔደ የዳሰሳ ጥናት መለየቱን አስታውሰዋል።

በዚሁ መሰረት ለእነዚህ ዜጎች ድጋፍ ለማዳረስ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

እስካሁን ለ1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ያህል ዜጎች ከ305 ሺህ  ኩንታል በላይ እህል ድጋፍ መደረጉንና መንግስታዊ አገልግሎት የማስጀመር ስራውም ተጠናክሮ መቀጠሉን አብራርተዋል።

በክልሉ የእህል አቅርቦት ስራን ለማሳለጥም ከ17 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ እህል ከጅቡቲ ቀጥታ ተጓጉዞ መቀሌ ወደ ሚገኙ የማሰራጫ ማዕከላት እንዲደርስ እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለሴፍቲኔት ተረጅዎች 69 ሺህ ሜትሪክ ቶን እህል ለማድረስ በሂደት ላይ ሲሆን እህል ነክ ያልሆኑ ድጋፎችን በስፋት የማዳረስ ተግባርም እየተከናወነ ነው ብለዋል።


የጤና አገልግሎትን በተመለከተም 71 ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገባቸው መድሃኒቶች ወደ ተለያዩ አካባቢዎች ለማድረስ ጥረት መደረጉን አክለዋል።

አካባቢውን መልሶ ለማቋቋም ከሚደረጉ ድጋፎች አንዱ ሕዝቡ የውሃ አገልግሎት እንዲያገኝ ማድረግ ነው ያሉት ሚኒስትር ሙፈሪያት የውሃ መስመሮች ተጠግነው አገልግሎት መስጠት እስከሚጀምሩ በቦቴ ውሃ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በክልሉ ትምህርት ለማስጀመር በትምህርት ሚኒስቴር በኩል ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን የአካባቢውን ሠላምና ፀጥታ አስተማማኝ ለማድረግም ለፀጥታ አካላት የተሐድሶ ስልጠና ተሰጥቷል ብለዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ በትግራይ ክልል ያለው የፀጥታ ሁኔታ የተሻለ ለውጥ እያሳየ በመሆኑ ሕብረተሰቡን በዘላቂነት ለማቋቋም በትኩረት እየተሰራ ነው።

በተመሳሳይ በመተከል ዞን ስድስት ከሚሆኑ ወረዳዎች ከ104 ሺህ በላይ ዜጎች ወይም ከ17 ሺህ በላይ አባወራዎች በታጣቂ ሃይሎች ጥቃት ተፈናቅለዋል ነው ያሉት።

ለእነዚህ ወገኖች የዕለት ደራሽ እርዳታ ለማድረስ ጥረት የተደረገ ሲሆን በተለይ ለእናቶችና ሕፃናት የአልሚ ምግብና ሌሎች ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ድጋፎች እየተደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

በዞኑ ከሚገኙ 183 ቀበሌዎች ከ32ቱ በስተቀር አብዛኞቹን ከታጣቂዎች የማጽዳት ስራ የተሰራ ሲሆን በቀሪዎቹም መቀጠሉን ገልፀዋል፡፡

ጎን ለጎንም የአካባቢውን ሕብረተሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም የተለያዩ የስራ ዕድሎች የማመቻቸት ተግባራት እንደሚከናወኑ ገልፀዋል።

ሚኒስትር ሙፈሪያት የአካባቢውን ሠላም በዘላቂነት ለማስጠበቅ ከማኅበረሰቡ የተውጣጣ ሚሊሻ አደራጅቶ ስልጠና ለመስጠት እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

(ኢዜአ)

Exit mobile version