Site icon ETHIO12.COM

“ህንፃ ከሌላቸው ባለሃብቶች ውስጥ አንዱ ነኝ… ለሀገሬ ምን አደረግሁላት ብዬ ሳስብ እደሰታለሁ”አቶ በላይነህ ክንዴ

“የታታሪዋ ኢትዮጵያ ምልክት ነን ብለን እናስባለን፤ ላለፉት 29 ዓመታት ያለመታከት ሰርተናል”፤ “ለሀገሬ ምን አደረግሁላት ብዬ ሳስብ እደሰታለሁ” ሲሉ ስራዎቻቸውን አብራርተው ተናግረዋል

👉አዲስ አበባ ውስጥ ህንፃ ከሌላቸው ባለሃብቶች ውስጥ አንዱ ነኝ፤ ኢትዮጵያ ሆቴልን ብቻ በጨረታ ገዝቻለሁ፤ አንድ ፎቅ ብሰራ የሥራ ዕድል የምፈጥረው ለሁለት ሰው ነው፤ ለዚህ መሰል ነገር ዕድል አልሰጥም፤

👉 እኔ ወጣ ብዬ ሀገሪቱን ሊያሳድግ የሚችልና ብዙ ሰዎችን ሊቀጥር የሚችል የሥራ ዕድል የሚፈጥር ዘርፍ ላይ ነው ኢንቨስት ማድረግ የምፈልገው፤

👉 ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 33 ሚሊዮን ብር ቦንድ ገዝተናል በቀጣይም እንገዛለን፤ ኮሚቴ ሆኜ ባለሃብቶችን ሳስተባብር ነበር በቀጣይም አስተባብራለሁ፤

👉 ለሀገራችን ሞራል፣ አንድነትና ማንነት ወሳኝ ስለሆኑ ገና በስፋት እሳተፋለሁ፤ ለዚህ ፕሮጀክት የሕይወት መስዋዕትም ቢሆን ለመክፈል ዝግጁ ነኝ፤

👉 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የቱሪዝም መስህብን ለማሳደግ በማሰብ በተዘጋጀው ገበታ ለሀገር ፕሮጀክት እውን ለማድረግም 35 ሚሊዮን ብር ወጪ አድርገናል፤

👉 ለሀገሬ ምን አደረግሁላት ብዬ ሳስብ እደሰታለሁ፤ ለልጆቼ እነግራቸዋለሁ፤ እነርሱም ሚዲያ ላይ ያያሉ፤ ህብረተሰቡም ክብር ሲሰጠው ደስ ይለኛል፤ እኔም ማህበራዊ ኃላፊነቴን እንደተወጣሁ ያሳየኛል፤ ግን ብዙ እንደሚቀረኝ እገምታለሁ፤

👉 የእኛ መፈክር የታታሪዋ ኢትዮጵያ ምልክት ነን ብለን እናስባለን፤ ላለፉት 29 ዓመታት ያለመታከት ሰርተናል፤ የእኔ ባህል ድርጅቱና የማኔጅመንት አባላት ተላብሰውታል፤

👉 ዱሮ መኪና አስመጥተን እንሸጥ ነበር፤ አሁን በኮንቴነር መጥቶ እዚህ እንገጣጥማለን፤ ሰሊጥ ጥሬ መላክ ትተን እየቆላን እንልካለን። ዘይት የታሸገ እናመጣ ነበር አሁን እዚሁ አምርተን አሽገን እንሸጣለን፤

👉 በኢትዮጵያ ታሪክ ወደ ውጭ የግብርና ምርት በብዛት የሸጥነው እኛ ነን፤ በ2005 ዓ.ም አንድ ሚሊዮን ኩንታል በቆሎ ለጣሊያን ገበያ አቅርበናል፤

👉 የውጭ ሰዎች የሚመጡት ትርፍ ይዘው ለመሄድ እንጂ ለኢትዮጵያ ሕዝብ አስተዋፅዖ ለማድረግ አይደለም።ከዚህ አስተሳሰብ በመነሳት ሁላችንም ተደጋግፈን ፋብሪካው እንዲሰራ አድርገናል፤

👉 በኢትዮጵያ 110 ሚሊዮን ይዘን በቀን 50 ቶን ዘይት ብቻ የሚያጣራ ፋብሪካ ነበር ያለን፤ ከጎረቤት ሀገራት አኳያ ሲታይ ምንም እንደሌለን ነው፤ የምንጠቀመው 99 ከመቶ ከውጭ በሚመጣ ግብአት ነበር፤

👉 በሀገር ውስጥ ያለው ደግሞ በአግባቡ አሲድ እና ስብ ሳይቀንስ ኑግ እና ጎመንዘር እየተፈጨ በደንብ ሳይጣራ ለገበያ ይቀርብ ነበር፤ እኛም ከ10 ዘይት አስመጪዎች መካከል ነበርንበት። በዚህ ሥራ ላይ ስለቆየን የሕዝብ ችግርም ይገባን ነበር፤

👉 የቡሬው የዘይት ፋብሪካ ግንባታ 4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ወስዷል።በአሰራሩ መሰረት መሰል ፕሮጀክቶች ባንክ 70 ከመቶ ድርጅታችን ደግሞ 30 ከመቶ መሸፈን ነበረበት።እኛ ግን 70 ከመቶ ሸፍነን 30 ከመቶ ከባንክ ብድር ወስደናል፤

👉 እዛ ያወጣነውን ገንዘብ ወደ ሕንፃ እንቀይረው ብለን ብናስብ ህንፃ ሰርቶ 60 ሰው ቀጥሮ ያለጭንቀት መኖር ይቻላል።፤

👉 ካምፓኒዎች ረጅም እድሜ እንዲኖራቸው ከተፈለገ ከህብረተሰቡ ጋር መኖርና መናበብ አለባቸው። እኔ እዛ ስሄድ ዋናው ዓላማዬ ፋብሪካ ከፍቼ ሰዎችን እጠቅማለሁ፣ እኔም እጠቀማለሁ ሀገሬንም እለውጣለሁ ብዬ ነው።ከአስተሳሰቡ ስትነሳ ይህ ነው መሆን ያለበት።

👉ፋብሪካው በቀን 1ሺ500 ቶን ወይንም 1ነጥብ5 ሚሊዮን ሊትር እና ከዚያ በላይ ዘይት ያመረታል።በዓመት 20 ሚሊዮን ኩንታል የቅባት እህሎች ይፈልጋል።ሀገሪቱ በዓመት የምታመርተው በአማካይ ከሦስት ሚሊዮን አይበልጥም፤

👉 ባለሃብቱ መሬት ወስዶ ብድር ካገኘ በኋላ አያለማም፤ አላግባብ መሬት ይዞ መቀመጥ አለ፤ በማህረሰቡ ዘንድ የዚህ ብሄር ነኝ ይህ መሬት የእኔ ነው የሚል አስተሳሰብ አለ።በእኔ አስተሳሰብ መሬት ለሚያለማ ሰው መሆን አለባት።አጭበርባሪዎችም ከጨዋታ ውጭ መሆን አለባቸው፤

👉 አንዳንዱ ለራሱና ለቤተሰቡ ከሠራ በኋላ ሌላው ገደል ይግባ የሚል አስተሳሰብ አለው፤ ይህም ስህተት በመሆኑ መቆም አለበት። ይህ በፖሊሲ መመለስ አለበት፤

👉 አንዳንዱ ደግሞ ለብዙዎች ፋይዳ በሌለው ሴክተር ላይ ይሰማራል፤ ይህ እንደ ሀገር መስተካከል አለበት፤

👉ዛሬ ሕንፃ ቢገነባ ድሃው የሚበላውን ካጣ ነገ ያፈርሰዋል፤ እያየነው ነው፤ ብዙ ተሞክሮም አልፈናል፤ ስለዚህ ለብዙ ሰዎች የሥራ ዕድል በሚፈጥረው ላይ ማተኮር አለበት የሚል ሃሳብ አለኝ፤

ከአቶ በላይነህ ክንዴ ጋር የተደረገውን ቃለ ምልልስ ሙሉውን ለማግኘት ሊንኩን ይጫኑ
https://www.press.et/Ama/?p=40858

ባለሀብቱ አቶ በላይነህ ክንዴ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣጋር

Exit mobile version