Site icon ETHIO12.COM

የውጭ ኦዲት ድግግሞሽን የሚያስቀር አዋጅ ተዘጋጅቷል

የውጭ ኦዲት ድግግሞሽን ማስቀረት የሚያስችል አዋጅ መዘጋጀቱን የፌዴራል ዋና ኦዲተር አስታወቀ።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የውጭ ኦዲት ድግግሞሽን ለማስቀረት የወጣ የነጠላ ኦዲት ረቂቅ አዋጅ ላይ ተወያይቷል። የሂሳብ ምርመራ አገልግሎት ኮርፖሬሽንን እንደገና ለማቋቋም በተዘጋጀ ረቂቅ ደንብ ላይም መክሯል።

ረቂቅ አዋጁ የፌዴራል መንግስት ለክልሎች የሚሰጠውን የበጀት ድጎማና ድጋፍ አስመልክቶ የሚደረግ ኦዲትና ቁጥጥር ከህገ መንግስቱ ህግና አሰራር ውጪ ስለመሆናቸው በጥያቄ ተነስቷል።

ረቂቁን በአዋጅ መልክ ከማውጣት ይልቅ በአዋጁ የተመለከቱት ድንጋጌዎች በመመሪያ መልክ ቢወጡ የተሻለ እንደሆነም ሃሳብ ተነስቷል።

የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ ለጥያቄዎችና አስተያየቶች በሰጡት ምላሽ በፌዴራል መንግስት የሚደረግ ማንኛውም አይነት ድጋፍም ሆነ ድጎማ ኦዲተር መስሪያ ቤቱ ኦዲት ማድረግ እንደሚችል በአዋጅ መደንገጉን ተናግረዋል፡፡

መንግስት ለክልልና ለግል ድርጅቶች የሚደርገውን ድጋፍና ድጎማ የፌዴራል ዋና ኦዲተር ኦዲት ማድረግ እንደሚችል በህገ መንግስቱ አንቀፅ 94/2 በግልፅ መቀመጡን ገልፀዋል።

ዓላማው ክልሎችን ወይም የልማት ተቋማትና የግል ድርጅቶችን ኦዲት ለማድረግ ሳይሆን ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ የሚደረግላቸው የግል ድርጅቶች ኦዲት መደረግ ስላለባቸው አሰራር ለመዘርጋት ነው ብለዋል፡፡

የረቂቅ ሰነዱ ዋና ዓላማም የፌዴራል መንግስት ድጋፍና ድጎማ አስተዳደር በቂ የቁጥጥር ስርዓት እንዲዘረጋለት በመሆኑ ከመመሪያ ይልቅ በአዋጅ መልክ መውጣቱ የተሻለ መሆኑን ዋና ኦዲተሩ ጠቁመዋል፡፡

የፋይናንስ አስተዳደሩ እንዲጠናከር፣ የፌዴራል ድጋፍና ድጎማ ሂሳብ ኦዲት አንድ ወጥ የሆነ ስርዓት እንዲከተል ማስቻልና የኦዲት ድግግሞሽን ለማስቀረትም ያግዛል ብለዋል፡፡

በመንግስት የሚደረግ ድጋፍና ድጎማ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት፣ በክልሎችና በግል ኦዲተሮች ኦዲት ሲደረግ ድግግሞሽ በመፈጠሩ ኦዲት የሚደረገው ተቋም ላይ ጫና መፍጠሩን አንስተዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ መሃመድ የሱፍ በበኩላቸው በግብዓትነት የተወሰዱትን ነጥቦች በማሟላት ለቀጣይ ውይይት ዝግጁ እንዲያደርጉ አሳስበዋል፡፡

Via -ENA

Exit mobile version