Site icon ETHIO12.COM

ሚድሮክ ከመንግስት ሚዲያዎች ጋር የሚፈጽመው የ”አብረን አንስራ” ውል አነጋጋሪ ሆኗል

“ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እና ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አብሮ ለመስራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ፡” የሚለው ዜና መሰማቱን ተከትሎ “ቀደም ብሎ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ አሁን ደግሞ ከፋና “ሲሉ ውሉ ያስገረማቸው አስተያየት አየሰጡ ነው፤ ሚድሮክ የመንግስት ሚዲያዎችን በኮንትራት መተሳሰር የፈለገበት ምክንያት ግልጽ አንዳልሆነላቸው የሚናገሩ “ድርጅቱ ከመንግስት ሚዲያዎች ጋር ውል ገብቶ ከፍተኛ ብር ሲከፍል በሌላ መልኩ ሚዲያዎቹን አፍ ያዘጋል”
ሚድሮክ በተከታታይ የሚያሰራጨው ከማስታወቂያ ያለፈ አቅድ ካለው የአየር ሰዓት ገዝቶ ሊሰራ አንደሚገባው ያመለከቱ “አንዲህ ያለው መታከክ አድሮ ችግር መፍጠሩ ኣይቀርም” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል። አያይዘውም አጀንዳውን በፓርቲ ደረጃ አየተወያዩበት አንደሆነ አመልክተዋል፤ የፓርቲያቸውን ስም ግን ለጊዜው አልገለጹም።

ሚድሮክ ወርቅ በድጋሚ ማምረት ሲጀመር አነዚህ የመንግስት ሚዲያዎች የቀድሞው ችግር የተፈታበትን አግባብ ያድበሰበሱትም ከዚሁ አንጻር ሊሆን አንደሚችል ግምታቸውን አስቀምጠዋል። ይህን ሲሉ ፓርቲያቸው ድርጅቱ ወርቅ ማምረቱን ይቃወማል ለማለት ሳይሆን በዚህ ዙሪያ አየሰሩ ያሉት ስራ መኖሩን ለመጠቆም መሆኑንን ተናግረዋል።

ሚድሮክ ለኢትዮጵያ ሞዴል የሚሆን ዘመናዊ ሚዲያ የመግንባትና የማደራጀት አቅም እንዳለው የጠቀሱት አስተያየት ሰጪ፣ አካሄዱ ፍጹም ተቀባይነት እንደሌለው ጠቁመዋል። “ኢቲቪና ፋና ከሚድሮክ ገንዘብ እየተቀበሉ እንዴት ሚድሮክን የተመለከተ የነጠረ ዘገባ ሊያሰራጩ ይችላሉ” ሲሉም ሚዲያዎቹ ነጻነታቸውን እንደሚያጡ አስታውቀዋል።

የፋና ዘገባ ከስር ያለው ነው

የፋና ብሮድካስቲን ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው እና የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ

የፊርማ ስነ ስርዓቱን የፋና ብሮድካስቲን ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው እና የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ ተፈራርመዋል፡

በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የፋና ብርድካስቲንግ ኮርፖሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው ፋና የህዝብ ሚዲያ እንደመሆኑ እለታዊ እቅስቃሴዎችን ከመዘገብ ባለፈ ለሃገርና ለህዝብ የሚጠቅሙ ስራዎችን የሚሰሩ ተቋማትን ከህዝብ ጋር የማስተሳሰር ስራዎች እየሰራ ነው ብለዋል፡፡

ፋና ሰፊ የማህበረሰብ መሰረት ካላቸው ተቋማት ጋር ለመስራት ምርጫው ሲያደርግ ህብረተሰቡን በቀላሉ ለማገልገል ያለውን ፍላጎቱን ባለሃብቱንና ህብረተሰቡን እንዲሁም አገልግሎቱንና አገልግሎት ፈላጊውን ለማገናኘት ብሎም በውጤቱ የማቀራርብ የማደግ እንዲሁም የሃገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎችን የማሳደግ አላማን ይዞ ነው፡፡

በዚህም እንደ ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ያሉ ለህብረተሰቡ ለውጥና ለሃገር እድገት ዘርፈ ብዙ ስራዎችን የሚሰሩ በመሆናቸው በጋራ ለመስራት መስማማታቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡

ፋና ብሮድካስቲን ኮርፖሬት በሬዲዮ በሁሉም የሃገሪቱ አካባቢዎች በ11 ኤፍ ኤም ጣቢያዎች ፣ በ7 የሃገር ውስጥ እና በአንድ የውጭ ቋንቋ በመድረስ ብሎም የተወደዱ የዜና ትምህርታዊና መዝናኛ ፕሮግራሞቹን በተሻለ ጥራት በቴሌቪዝን አማራጭ ይዞ በመምጣቱ በህዝብ ዘንድ ተመራጭ አድርጎታል ብሏል፡፡

ከዚህ ባለፈም በአቀራረቡ የተለየ በመሆኑ፣ የሃገርን ልማት ለማፋጠን እንዲሁም የህዝብ የሆኑ ስራዎችን በመስራት ተወዳጅ ጣቢያ በመሆኑ፤ ከሚድሮክ ጋር አብሮ መስራቱ  የሃገርን እድገት በማሳለጥ በኩል ብሎም ለተቋማቱ አስተዋጽዖ የጎላ መሆኑ ተነስቷል፡፡

በግብርናና አግሮ ኢንዱስትሪ፣ በማዕድን፣ በንግድና ቢዝነስ እንዲሁም በማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪው ዘርፎች 35 ኩባንያዎችን የሚያንቀሳቅሰው የሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ፤ ባሳለፍነው ዓመት መጨረሻ ባካሄደው የተቋም የለውጥ ስራዎች ውስጥ የሚዲያ አጠቃቀሙ አነስተኛ መሆኑን በመገምገም ከሁለት ተቋማት ጋር አብሮ ለመስራት መወሰኑን የኢንቨስትመንት ግሩፑ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አህመድ ተናግረዋል፡፡

በዚህ መሰረትም ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ የሃገርን ልማት ለማፋጠንና የሃሪቱን እድገትን ለማሳደግ እየሰራ ያለ ተቋም እንደመሆኑ የድርጅቱን አላማ የሚጋሩ አካላትን ተመራጭ በማድረግ ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን መምረጡን ስራ አስፈጻሚው አንስተዋል፡፡

ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በሃገር ውስጥና የውጭ ቋንቋዎች፣ በተለያዩ አማራጮች እንዲሁም በሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች ተደራሽ በመሆኑ ሌላው ተመራጭ የሆነበት ምክንያት ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ ባለፈም ፋና የሚሰራቸው ዘገባዎች፣ ዜናዎችና ፕሮግራሞች የህዝብ የሆኑ እንዲሁም በስራዎቹም ሃላፊነት የሚሰማው ተቋም  በመሆኑ ተቋሙን ተመራጭ እንዳደረገው አቶ ጀማል አህመድ ጠቁሟል፡፡

በሃይማኖት ኢያሱ

Exit mobile version