Site icon ETHIO12.COM

ጎንደር- የመገጭ የመስኖና የመጠጥ ውሃ ግድብ ፕሮጀክት በመጪው ነሃሴ ይጠናቀቃል

የመገጭ የመስኖና የመጠጥ ውሃ ግድብ ፕሮጀክትን በመጪው ነሃሴ ወር ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የፕሮጀክቱ ስራ አስኪያጅ አስታወቁ። 6 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ በጀት የተመደበለትን የግድብ ግንባታ እንቅስቃሴ የፌደራል ከተማ ልማትና ኮንስራክሽን ሚኒስትሯ ኢንጂነር አይሻ መሃመድ ዛሬ ጎብኝተውታል፡፡

ስራ እስኪያጁ ኢንጂነር ጸጋዬ መኮንን በዚህ ወቅት እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት የግድቡ ግንባታ 69 በመቶ ደርሷል፡፡ባለፉት አመታት ፕሮጀክቱ ገጥሞት የቆየው የግንባታ ቁሳቁሶች እጥረት አሁን ላይ በመፈታቱ የግንባታ ስራው 24 ሰአት በመከናወን ላይ እንደሚገኝም አስረድተዋል፡፡ ግድቡ 77 ነጥብ አንድ ሜትር ከፍታና 890 ሜትር ደግሞ እርዝመት ሲኖረው 187 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ የመያዝ አቅም እንዳለውም ተናግረዋል፡፡

ግድቡ ከሚይዘው ውሃ 30 በመቶው ለጎንደር ከተማ የመጠጥ ውሃ አገልግሎት እንደሚውል የተናገሩት ኢንጅነሩ 17ሺ ሄክታር መሬት በመስኖ በማልማት 45ሺህ አባወራ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ፕሮጀክቱን በአራት አመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እቅድ ተይዞ ወደ ስራ ቢገባም በግንባታ ሂደት ተጨማሪ ስራዎች በማጋጠማቸው ግንባታው 7 አመት እንደፈጀም ተናግረዋል፡፡

በጉብኝቱ ወቅት የከተማው ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ እንደገለጹት ግድቡ ሲጠናቀቅ ለከተማው የመጠጥ ውሃ አቅርቦት የሚውለውን 30 በመቶ የውሃ ድርሻ ጥቅም ላይ ለማዋል ከተማ አስተዳደሩ እየሰራ ነው፡፡አዲስ የውሃ ማጣሪያ ለመገንባትና የከተማውን የውስጥ መስመሮች ለማሻሻልም ከኢትዮጵያ ዲዛይንና ጥናት ድርጅት ጋር የ21 ሚሊዮን ብር የዲዛይን ጥናት ስምምነት መፈረሙንም ተናግረዋል፡፡

የግድቡን ውሃ ለከተማው ነዋሪዎች ለመጠጥነት ለማዋል በግማሽ ቢሊዮን ብር ወጪ ዘመናዊ የውሃ ማጣሪያ ለመገንባት አለም አቀፍ ጨረታ በቅርቡ እንደሚወጣም አስረድተዋል፡፡ግንባታውን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተደረገ ያለውን ርብርብ ሚኒስትሯን ጨምሮ የፌደራል የክልልና የከተማው አመራሮች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡

(ኤዜአ)

Exit mobile version