Site icon ETHIO12.COM

“ ትግራይ ወደ ሰላማዊ ሁኔታ እየተመለሰ በመሆኑ የመቐለ የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ግንባታ ይቀጥላል”ዶ/ር ኢንጂር

በትግራይ ክልል ሲካሄድ የነበረው ሕግን የማስከበር ዘመቻ የተጠናቀቀ በመሆኑ እና አካባቢው ወደ ሰላማዊ ሁኔታ እየተመለሰ በመሆኑ የመቐለ ከተማ የንፁህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ግንባታ እንደሚቀጥል የውኃ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ አስታወቁ፡፡

ሚኒስትሩ ዛሬ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር በትብብር የሚከናወኑ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ ከባንኩ ዋና ዳይሬክተር ቼፕቶ አሞስ ኪፕሮኖህ ጋር ተወያይተዋል::

ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ከዋና ዳይሬክተሩ ጋር ባደረጉት ውይይት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤታቸው እያከናወናቸው ስለሚገኙ ዋና ዋና የልማት እንቅስቃሴዎች በዝርዝር ገለጻ አድርገውላቸዋል::

በተለይም ደግሞ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር በትብብር ስለሚከናወኑ የልማት ፕሮጀክቶች መምከራቸው ነው የተገለጸው::

ዋና ዳይሬክተሩም በግንባታ ላይ የሚገኘውን የመቐለ የንፁህ መጠጥ ውኃን እና ሌሎች የኢነርጂ ፕሮጀክቶችን የግንባታ ሂደት በተመለከተም ማብራሪያ ጠይቀው ከሚኒስትሩ እና ከሌሎች የሥራ ኃላፊዎች ምላሽ አግኝተዋል፡፡

በዚህም መሠረት በልማት ባንኩ የገንዘብ በትብብር እየተገነቡ ያሉ ፕሮጀክቶችን በታቅዷላቸው ጊዜ ለማጠናቀቀ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስፈላጊውን ሁሉ እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ መከሰትም ግንባታውን በሚፈለገው ፍጥነት ለማድረግ እክል መፍጠሩንም አንስተውላቸዋል፡፡

በተጨማሪም የአፍሪካ ልማት ባንክና የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በትብብር ሊሰሯቸው የሚችሉባቸው መስኮች በመለየት ሚኒስትሩ ገለጻ እንዳደረጉላቸው ነው የተገለጸው፡፡

በተለይም በኢነርጂው ዘርፍ መንግሥት ያካሄደው ሪፎርም በዘርፉ ለማልማት ምቹ ሁኔታ የፈጠረ በመሆኑ ባንኩ በገጠራማው የኢትዮጵያ ክፍል ኃይል ለማቅረብ መንግሥት የሚያደርገውን ጥረት እንዲያግዝም ሚኒስትሩ ጠይቀዋል፡፡

የሕዳሴውን ግድብ የግንባታ ሂደት እና በሦስቱ ሀገራት መካከል ሲደረግ የነበረውን ድርድር አስመልክቶ ለዋና ዳይሬክተሩ ማስረዳታቸውም ተገልጿል፡፡

አለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማት ለግድቡ ግንባታ የሚውል ገንዘብ ለማበደር ፍቃደኞች አለመሆናቸውን አንስተው፣ሆኖም ኢትዮጵያውያን በራሳቸው ገንዘብ ገንብተው ግድቡን 78 ነጥብ 3 በመቶ ማድረስ መቻላቸውን ገልጸውላቸዋል፡

ኢትዮጵያም ግድቡን አጠናቅቃ የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራትን በኃይል ታስተሳስራለች ብለዋል ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፡፡

ከዚህም አኳያ ባንኩ ለኢትዮጵያ እና ኬንያ ትስስር ስላደረገው የገንዘብ ብድርም አመስግነዋል::

ምንጭ: ከውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር

Exit mobile version