Site icon ETHIO12.COM

ስለ ልጆች እና ኮቪድ-19 ሳይንዊ ጥናቶች ምን ይላሉ?

የኮቪድ-19 በሽታ ምንም እንኳ በአፍሪቃ ብሎም በኢትዮጵያ  ቸል የተባለ ቢሆንም፤ የሚያስከትለው ጉዳት መቀጠሉን ግን መረጃዎች ያሳያሉ። በሽታው በዓለም ላይ ሚሊዮኖችን ለሞትና በርካቶችን ለከፍተኛ ጉዳት እየዳረገም ይገኛል።ይህንን ጉዳት ለመቀነስ ታዲያ የኮቪድ-19 በሽታ ከተከሰተ ወዲህ ስለበሽታው ባህሪያትና መከላከያ  የሚደረገው ሳይንሳዊ ምርምር ቀጥሏል። ቀደም ብለው ይወጡ በነበሩ ጥናቶች አዋቂዎች የበሽታው ተጠቂና ከፍተኛ አስተላላፊ ተደርገው ይታዩ ስለነበር በሽታው ለልጆች ያን ያህል አደገኛ ነው የሚል ነገር አልነበረም። በቅርብ ጊዜ በሚወጡ ጥናቶችና ዘገባዎች ግን በሽታው በልጆች ላይ የሚያደርሰው ጉዳት  በትኩረት እንዲታይ የሚያደርግ ነው።

በሌላ በኩል  ከስድስት ዓመት ዕድሜ ጀምሮ  ባሉ ልጆች የክትባትን ውጤታማነት ለመፈተሽ የሙከራ እቅዶች መኖራቸው እየተገለፀ ነው። ከክትባት ሙከራው በስተጀርባ ያለው አመክንዮ ምንድነው? ልጆችስ መከተብ አለባቸው ወይ? ከሆነስ ምን አይነት ጥንቃቄ መደረግ አለበት? በሚሉትና በአጠቃላይ ስለ  ልጆች እና ኮቪድ-19 የተደረጉ ሳይንዊ ጥናቶች ምን ይላሉ? 
የኮሮና ወረርሽኝ ከአንድ አመት በኋላም በሰዎች የዕለት ተዕለት ሕይወት ላይ ተፅዕኖው ቀጥሏል። አሁንም ድረስ አሜሪካና አብዛኛዎቹ የአውሮፓ ሃገራት በጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ ውስጥ ይገኛሉ። ትምህርት ቤቶችና መዋዕለ ሕጻናት ዝግ ናቸው። ልጆች መማርና ወደ ትምህርት ቤት መሄድ ቢኖርባቸውም ደህንነታቸው ግን የተጠበቀ መሆን አለበት። በምን ሁኔታ የሚለውም የብዙዎች  ጥያቄ ነው። 
ቀደም ሲል ኮቪድ-19ን በተመለከተ በልጆች ላይ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት አብዛኛዎቹ ኮቪድ-19 የሚያዙ ሕፃናት ልጆች መለስተኛ ምልክቶች ወይም በጭራሽ ምንም ምልክቶች ላይታይባቸው ይችላል። በኮሎምቢያ ዩንቨርሲቲ የበሽታ መከላከል ባለሙያ ፕሮፌሰር ዶና ፋርበር ልጆች ተዋህሲው በደማቸው እያለ  ምልክት ላያሳዩ የሚችሉባቸውን  ሁለት ምክንያቶችን ያቀርባሉ። 


«ለዚያ ሁለት ዋና ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። አንደኛው ህዋሳትን በተመለከተ የተለዬ ነገር ሊኖር ይችላል። በልጆች የመተንፈሻ አካል ውስጥ ተዋህሲው  የተለዩ ህዋሳት ሊኖሩ ይችላሉ። ምናልባት ያ ሊሆን ይችላል። ሁለተኛው ልጆች ከፍተኛ የመከላከል አቅም ስላላቸው ከመታመማቸውና ምልክት ከማሳየታቸው በፊት ሊከላከሉትና ሊድኑ ይችላሉ።»
ያ በመሆኑ በአብዛኛው ለልጆች  የኮሮና ተዋህሲ ምርመራ አይደረግም። ልጆች እንደ ተጋላጭ የኅብረተሰብ ክፍል ተደርገውም አይታዩም ነበር። ይሁን እንጅ የቅርብ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የልጆች የመጋለጥና ተዋህሲውን የማሰራጨት  አደጋ  ከፍተኛ ነው። በቅርቡ በጀርመን ሙኒክ ተመራማሪዎች በ12 ሺህ ሕፃናት ላይ ያደረጉት የደም ምርመራ ይህንኑ ያሳያል። የጥናት ቡድኑ መሪ ፕሮፌሰር አኒተ ገብርኤል  ሲግለር እንደሚሉት ከሚጠበቀው ስድስት እጥፍ  ልጆች በተዋህሲው መያዛቸውን በጥናቱ ተመልክተዋል። 
«በልጆች ላይ ምርመራ አደረግን። ምርመራው የኮሮና ተዋህሲን የሚከላከለውን ፀረ-በሽታ ንጥረ ነገር ላይ ነበር። እናም ልጆቹ ከሚጠበቀው ስድስት እጥፍ በበሽታው ተይዘዋል። ጥናቱ ልጆች በትክክልም በበሽታው ይጠቃሉ። ወደ ቤትም ይወስዱታል የሚለውን አሳይቶናል። ነገር ግን ለልጆች ምርመራ አይደረግም። ስለዚህ የሚሰጠው ግምት ዝቅተኛ ነው።»
 በኮቪድ -19 የተያዙ ልጆች በአብዛኛው ቀላል ምልክት  ያሳያሉ ቢባልምም፤ ከበሽታው ካገገሙና ከተዋህሲው ነጻ ከሆኑ በኋላ ሳይቀር ለከባድ የመተንፈሻ አካል በሽታ የመጋለጥ ዕድል እንዳለም ጥናቶች ያሳያሉ። ሰሞኑን በእንግሊዝ የወጣው መረጃ ይህንን የሚያረጋግጥ ነው። መረጃው እንደሚያሳየው በየሳምንቱ 100 ሕፃናት ልጆች ለድህረ-ኮቢድ-19 የመተንፈሻ አካል በሽታ በመጋለጥ ወደ ሆስፒታል ይመጣሉ። በሽታው የላቲንና የአፍሪካ ዝርያ ባላቸው ሕፃናት ልጆች ላይ መበርታቱም ተገልጿል። ለዚህም የዘረ-መል ድርሻ ይኖር ይሆን ለሚለው በሳይንስ የተረጋገጠ መልስ ባይኖርም ከአኗኗር ዘይቤ ጋር ሊገናኝ ይችላል ተብሏል። ከዚህ በተጨማሪ ልጆች በሽታው ሊፀናባቸውና ወደ ፅኑ ህሙማን መርጃ እስከመግባት ሊደርሱ ይችላሉ። አልፎ አልፎም  ለሞት ይዳረጋሉ፡፡ ወይም ደግሞ ለከባድ የልብ ህመምና የደም ዝውውር  እንዲሁም ሌሎች ጉዳቶች ሊጋለጡ ይችላሉ። ፕሮፌሰር ዶና ፈርበርም  ይህንኑ ያረጋግጣሉ።

 
 «እናውቃለን ሆስፒታል በገቡ አዋቂዎች ላይ ኮቪድ-19 የተወሰነ የደም መርጋት ችግር  እንደሚያስከትል። ምናልባት ሰውነት ከሚሰጠው  ጠንካራ ምላሽ  ሊሆን ይችላል። በልጆች ላይም አደገኛ በሽታዎችን  ሊያስከትል እንደሚችል እናውቃለን። ከነዚህም ውስጥ የመተንፈሻ አካል ችግር አንዱ ነው። የረዥም ጊዜ ተፅኖ ያለው ጉዳት ሊያደርስ ይችላል።»  
ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት መስከረም ወር   ዘ ላንሴት በተባለ የህክምና መጽሔት  ላይ የወጣ  አንድ ጥናት እንደሚያሳየው የአሜሪካ የሀኪሞች ቡድን  ከ39 ጥናቶች  የተውጣጡ  662 ጉዳዮችን  ገምግመዋል። በዚህም አብዛኛዎቹ ልጆች የመተንፈሻ አካል በሽታ ተጠቅተው እንደነበርም አመልክተዋል። ጥናቱ ከጥር 1 እስከ ሐምሌ 25 ቀን 2020 ባለው ጊዜ ውስጥ በመላው ዓለም ሪፖርት የተደረጉ ጉዳዮችን የተመለከተ ሲሆን፤ 71 በመቶ የሚሆኑት ሕፃናት በከፍተኛ እንክብካቤ  በጽኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ህክምና ሲያደርጉ፤ 60 በመቶ የሚሆኑት ከባድ የደም ዝውውር ችግር አጋጥሟቸዋል። የልብ ምርመራ ከተደረገላቸው 90 በመቶ ገደማ ከሚሆኑት ልጆች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የልብ  መታወክ ገጥሟቸዋል። 
በሽታው በልጆች ላይ የሚያደርሰው ይህ መሰሉ ጉዳት ተመራማሪዎችን ስለልጆች ክትባት እንዲታሰቡ አድርጓቸዋል። ስለ ልጆችና ኮቪድ-19  የመከላከያ ክትባት ሲነሳ  እስካሁን ማረጋገጫ ያገኙት የባዮንቴክና የፋይዘር እንዲሁም የሞደርና ክትባቶች ዕድሚያቸው ከ16 ዓመት በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ ብቻ ሙከራ እየተደረገ ነው። የኦክስፎርዱ-አስትራዜኔካ  ግን ክትባቱ ምን ያህል ውጤታማ ነው የሚለውን ለማረጋገጥ ከስድስት  እስከ 17 ዓመት ዕድሜ ባላቸው ልጆች ላይ  ለመጀመሪያ ጊዜ ሙከራ ለማድረግ መዘጋጀቱን ገልጿል። የካቲት መጨረሻ በሚከናወነው በዚህ ሙከራ 300 የሚሆኑ በጎ ፈቃደኞች ይሳተፋሉ ተብሏል። ከበርሊን የቻሪቴ ሆስፒታል የክትባት ባለሙያ ላይፍ ኤሪክ አንደርሰን የልጆችን የኮቪድ-19 ክትባትና ውጤት በተመለከተ እስካሁን መረጃ አለመኖሩን ጠቅሰው  ክትባቱ በጥንቃቄ መሞከር አለበት ይላሉ። 


«እስከማውቀው ድረስ ስካሁን በይፋ የሚገኝ መረጃ  የለም። የባዮቴክ ፋይዘር ክትባት ከ 12 እስከ 15 ዓመት ባለው ዕድሜ ውስጥ ሙከራ እንደተደረገበት አውቃለሁ። ስለዚህ በጉርምስና ዕድሜ ላይ ባሉና  በትንንሽ ልጆች  የሚደረጉ ሙከራዎች ቀጣይ ናቸው ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ እነዚህ ክትባቶች በልጆች ላይ በጥንቃቄ መሞከር አለባቸው። ለልጆች ተስማሚ፣ ደህንነታቸው የተጠበቀና  ውጤታማ መሆናቸውም እንዲሁ።» 
ባለሙያው ላይፍ ኤሪክ አንደርሰን የኮቪድ-19 ክትባት በተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ባለው ውጤትና ተፅዕኖ ላይ ምርምር ያደርጋሉ። ልጆች መከተብ አለባቸው ወይ? የሚለው ጥያቄ ተደጋግሞ እንደሚነሳ  ገልፀው፤  ክትባቱ ለልጆች መስጠቱ ተገቢ መሆኑን ያስረዳሉ። ነገር ግን እንደ ባለሙያው የክትባቱ የጎንዮሽ ጉዳትና የሚያስገኘው ጥቅም በወጉ መታየት አለበት። 
«ያ ለማንኛውም ክትባት ፈቃድ ለመስጠት ዋናው ጥያቄ ነው። ማንኛውም ክትባት የሚያስገኘው ጥቅምና በክትባቱ ሊከሰቱ የሚችሉ ትክክለኛ አደጋዎችን የማነፃፀሪያ መንገድ ነው። በእርግጥ ስለ ልጆች በምንናገርበትም ጊዜም ቢሆን። እዚያ ባለው የአደጋና የጥቅም ጥምርታ ላይ  በጥንቃቄና በጥልቀት መመልከት አለብን።» 
 ኢትዮጵያን ጨምሮ በታዳጊ ሃገራት የሚገኙ ልጆች በምግብ እጥረትና ሌሎች ከድህነት ጋር ተያይዘው ከሚመጡ ችግሮች ጋር ተዳምሮ ኮቪድ-19 የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ በልጆችም ይሁን በአዋቂዎች ላይ ጥንቃቄ አስፈላጊ መሆኑን ተመራማሪዎቹ መክረዋል። 

ፀሐይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሠ – ጀርመን ሬዲዮ


Exit mobile version