ETHIO12.COM

የአዴፓ በረራዊ ጋዜጣዊ መግለጫ

በላይ ባይሳ

አዴፓ አዲስ አበባን አስመልክቶ በየካቲት 16/2011 ዓ.ም ያወጣው ጋዜጣዊ መግለጫ የዓላማና የጭብጥ፤ የይዘትና የቅርፅ መሰረታዊ ችግር ያለበት በበረራ የተሰጠ መግለጫ ነው።ከተፈቀደው ፍጥነት በላይ መብረር ደግሞ ለአደጋ ያጋልጣል። 30 የሆነውም በዚህ ምክንያት ነውና።በመግለጫው “አዴፓ በአዲስ አበባ የባለቤትነት ጉዳይ ላይ ጠንካራ አቋም እንዳለው አስታወቀ፡፡” ካለ በኃላ አቋሙን በአመክኗዊነት ሊገልፅ አልቻለም። እንዲሁ በጥቅሉ ግን ሃሳቡ ከአብን አስተሰሰብ ጋር የተጃመለና አንድምታ እንዳለው ያስረዳል።

ታድያ ዝም ብሎ ከመሬት ብድግ ብሎ ጠንካራ አቋም አለኝ ብሎ መፍነን አለ እንዴ?በመቀጠል በመግለጫው “አዲስ አበባ የነዋሪዎቿ እንድትሆን እና አግላይ አመለካከቶች እንዲወገዱ በትኩረት እንደሚሠራ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) አስታውቋል፡፡” ይላል።የሃሳቡ ድምፀት ባለቤትም ነኝ የሚል አይነት ይመስላል። ይህ በአንድ ቤት ሁለት አባወራ ሊኖር እንደማይችል ሁሉ በአንድ ጊዜ ከአንድ በላይ ባለቤት ሊኖር አይችልም።

አዴፓ ተጠቅሶ የተሰራው ዜና

በከተማዋ ውስጥ በጋራ የመጠቀም (መኖር፣ መስራት፣ መምረጥና መመረጥ…) መብትንም አይገታም። ይህ መሆን የሚችለው ደግሞ ባለቤትነትን በመካድ ሳይሆን ለባለቤቱ እውቅና በመስጠት ነው።በመግለጫው “አዲስ አበባ የነዋሪዎቿ እና የኢትዮጵያ መዲና እንጅ የማንም አይደለችም፡፡” ይላል። ሃሳቡ ግልፅነት ይጎድለዋል። እሺ! ታድያ የማን ትሁን? የዘፈን ዳርዳሩ … እንደሚባለው ይህ አባባል በቀጥታ ከፍ ባለ ድምፅ አዲስ አበባ የኦሮሚያ አይደለችም! ለማለት ነው። ይህ ሁኔታ ደግሞ በየትኛውም አግባብ አያስኬድም። ተቀባይነትም የለውም።

ይልቁንም ቅሬታን እና ግጭትን ይፈጥራል እንጂ።በመቀጠልም “አጀንዳውም ለውጡን የማይደግፉ ኃይሎች የሚጠነስሱት የፖለቲካ ሤራ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡” ይላል። እኮ ወዴት! ወዴት? የፓለቲካ ቀለም በመስጠት ማደናገር እና ከለውጡ ጋር ማላተም የሾቀ የፓለቲካ ስሌት ነው። አይቻልም!። ሲጀምርም ለውጡን ማን እንዳመጣው ቄሮ፣ ቲም ለማ፣ ጃዋር … ወዘተ ናቸው ብዬ አልናገርም እንጂ ይታወቃል።ምክንያቱ ደግሞ የኦሮሞ ህዝብ የታገለለት አንዱ እና ዋንኛ አላማ የአዲስ አበባ ጉዳይ መሆኑ መረሳትም የለበትም። ታድያ የምን ዳር ዳር ማለት ነው? ጥንስስም ሆነ ሴራ የለም ግልፅ የትግል አጀንዳ ነው ያለው። ግን ሊሰርቋት ያሰቧትን ከተማ በረራ ይሏታል ይባል የለ። ደሞ ለተረት? እንደጉድ እንተረትረዋለን።

ሌላኛው አስገራሚው የመግለጫው ክፍል ደግሞ ምክትል ከንቲባው እና የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊው “አዲስ አበባ የራሷ መዋቀር እና አስተዳደር ያላት የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ከተማ እንጅ የማንም አይደለችም” ያሉት ነው። ይህ መሰረታዊ የይዘት ችግር አለበት። ከንቲባው ይሁነኝ ብለው ያጎደሉት ነገር አለ። አዲስ አበባ የኦሮሚያ ዋና ከተማ መሆንዋን ሆን ብለው አልገለፁም፡፡ ይሄ አሁንም ሆን ተብሎ የተደረገ የጠባጫሪ መግለጫ ነው።በመቀጠልም መግለጫው “በዚህ ጉዳይ ላይ ችግር ካለም በዉይይት እንደሚፈታ…” ይላል ይህ እራሱ በድሎ እራሱ አለቀሰ አይነት ፉከራና ቀረርቶ ናት።

ጠብ በዳቦ ያለህ ብሎ ሲያበቃ ደግሞ በውይይት እንፈታለን ይላል።ይሄ ከመግለጫው አነሳስ ጋር አብሮ የማይሄድና የሚጣረስ ሃሳብ ነው። እውነት በውይይት ካመኑ ከሚመለከተው አካል ጋር መወያየት ነው የሚቀድመው? ወይንስ ሚዲያላይ ፊጥ ብሎ መጣድና ማቅራራት? አግራሞትን የሚያጭረው ሌላኛው ጉዳይ ደግሞ ” ችግር ፈጣሪዎችም እንደሚጠየቁ አረጋግጠዋል፡፡” ይላል። በእርግጥ እራሳቸውን ከሆነ ያስኬዳል።

ሌላን አካል ከሆነ ግን ችግር ፈጣሪ እነ እገሌ ናቸው ብለው መናገር ነበረባቸው። ያኔ ግልፅ ይሆን ነበር።ይሄንንም አልፎ በመግለጫው ሊባል የተፈለገው የኦሮሞ ማህበረሰብ የፊንፊኔን ባለቤትነት ለምን ጠየቀ? የሚል ጥምዝ ሃሳብ በውስጡ የያዘ ከሆነ ደግሞ እሱ ሌላ ጉዳይ ነው። “ኧረ ተውነ ወረሞ ነነ” እንዳይሆን ነገሩ ለማለት ነው።ስለዚህ በጥቅሉ መግለጫው ሃገር ከሚመራ ዴሞክራሲያዊ ነኝ ከሚል ድርጅት የተሰጠ የማይመስል እጅግ የተጃመለ እና ሃላፊነት የጎደለው ብቻ ሳይሆን ዓላማው ግልፅ ያልሆነ፣ ጭብጡ የማይገባ፣ የይዘትም ሆነ የቅርፅ ችግር ያለበት የተምታታ የበረራ ሃተታ ነው። በዚህ መልኩ ሃገር አይገነባምና የቃልና የተግባር ውህደት ይኑር!። አዴፓ ስሙና ተግባሩም አልተገናኝቶም!።

በላይ ባይሳ የካቲት 17/2011 ዓ.ም

ዝግጅት ክፍሉ – ይህ ነጻ አስተያየት ነው። በጽሁፉ የቀረበው ሃሳብ የጸሃፊው አቋም ብቻ ነው


Exit mobile version