Site icon ETHIO12.COM

ደንበኞች እንዴት የተጠቀሙበትን የፍጆታ ሂሳብ ማወቅ ይችላሉ?

በርካታ የድህረ ክፍያ ደንበኞች የተጠቀሙበትን የኤሌክትሪክ ፍጆታ ሂሳብ እንዴት እንደሚሰላ ባለማወቃቸደው የተጋነነ የፍጆታ ሂሳብ ተጠየቅን የሚል ተደጋጋሚ ቅሬታ ሲያቀርቡ ይስተዋላል፡፡ ይሁን እንጂ ቅሬታው የሚነሳው ደንበኞች የተጋነነ ሂሳብ እንዲከፍሉ በመደረጉ ሳይሆን የፍጆታ ሂሳብ እንዴት መሰላት እንዳለበት በቂ ግንዛቤ ስለሌላቸው ነው፡፡

ይህን ክፍተት ለመሙላት የሚከተለውን መረጃ አስቀምጠናል፡፡ ደንበኞች በመኖሪያ ቤታቸው የሚጠቀሙባቸውን የኤሌክትሪክ ቁሳቁሶችን የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን መነሻ በማድረግ ምንያህል ኪ.ዋ.ሰ እንደተጠቀሙና ምን ያህል የፍጆታ ሂሳብ እንደሚከፍሉ መረዳት ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ አንድ ደንበኛ በመኖሪያ ቤቱ 4 ባለ 60 ዋት አምፖሎች በቀን ለ6 ሰዓት ለ30 ቀናት ቢያበራ፣ 3000 ዋት ኤሌክትሪክ ሃይል የሚጠቀም ምጣድ በቀን ለ2 ሰዓት በወር ለ10 ቀናት ቢጠቀም እና 1000 ዋት ሰ የኤሌክትሪክ ሃይል የሚጠቀም ምድጃ በቀን ለ5 ሰዓት ለ30 ቀናት ቢጠቀምና ምን ያህል ኪ.ዋ.ሰ እንደሆነና ምን ያህል የፍጆታ ሂሳብ እንደሚከፍል ለማወቅ የተጠቀመበትን የኤሌክትሪክ ሃይል በመደመር ወደ ኪ.ዋ.ሰ መቀየር ይጠበቅበታል፡፡

• 4 አምፑል X 60 ዋት x 6 ሰዓት x 30 ቀናት = 43,200 ዋት ሰ ፣

• 3000 ዋት ኤሌክትሪክ ሃይል የሚጠቀም ምጣድ x 2 ሰዓት x 10 ቀናት=60,000 ዋት ሰ፣

•1000 ዋት ኤሌክትሪክ ሃይል የሚጠቀም ምድጃ x 5 ሰዓት x ለ30 ቀናት=150,000 ዋትሰ 43,200 ዋት ሰ+ 60,000 ዋት ሰ + 150,000 ዋት ሰ= ጠቅላላይ ድምር 253,200 ዋት ሰ ይሆናል፤ ይህ ወደ ኪሎ ዋት ሰዓት መቀየር አለበት፤ በመሆኑም 1 ኪሎ ዋት ሰዓት=1000 ዋት ሰዓት በመሆኑ 253,200 ዋት ሰዓት = 253.2 ኪሎ ዋት ሰዓት ይሆናል፡፡

የመኖሪያ ቤት የታሪፍ ስሌት 7 ደረጃዎች ያሉት ሲሆን አንድ የመኖሪያ ቤት ደንበኛ በወር የተጠቀመበት የኤሌክትሪክ ሃይል በሚያርፍበት የታሪፍ እርክን ተባዝቶ እንዲከፍል ይደረጋል፡፡ በዚህ ስሌት መሰረት አንድ ደንበኛ በወር 253.2 ኪ.ዋ.ሰ የኤሌክትሪክ ሃይል ቢጠቀም በቀጥታ 4ኛው እርከን ላይ የሚያርፍ በመሆኑ በ1.6375 ብር የሚባዛ ይሆናል፡፡ በዚህ መሰረት 253.2 x 1.6375 ብር= 414.615 ብር ይሆናል፤ የአገልግሎት ክፍያ ብር 42 ሲደመርበት በአጠቃላይ የደንበኛው የፍጆታ 456.615 ብር ይሆናል፡፡

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ከታህሳስ 2011 ዓ.ም ጀምሮ ለአራት ተከታታይ አመታት የሚተገበር የታሪፍ ማስተካከያ ማድረጉ የሚታወቅ ሲሆን ይህ ስሌት የተሰራው ከታህሳስ 1 ቀን 2013 ዓ.ም እስከ ህዳር 30 2014 ጀምሮ ተግባራዊ እየተደረገ በሚቆየው የታሪፍ እርከን በመሆኑ ክቡራን ደንበኞቻችን የተጠቀማችሁበትን የፍጆታ ሂሳብ ለማስላት ይረዳችሁ ዘንድ ከታች የተቀመጠውን የታሪፍ ማስተካከያ እርከን እና የአገልግሎት ክፍያ ሰንጠረዥ መመልከት ትችላላቸሁ፡፡


#የኢትዮጵያኤሌክትሪክአገልግሎት

Exit mobile version